ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 8
8
የሱነም ከተማ ነዋሪ የነበረችው ሴት ከስደት መመለስ
1ልጅዋን ከሞት ያስነሣላትን፥ በሱነም ትኖር የነበረችውን ሴት እነሆ፥ ኤልሳዕ አስቀድሞ እንዲህ ሲል ነግሮአት ነበር፥ “እግዚአብሔር እስከ ሰባት ዓመት የሚቈይ ራብ በዚህች ምድር ላይ ልኮአል፤ ከቤተሰብሽ ጋር በሕይወት ለመትረፍ ከዚህ ተነሥተሽ ወደ ሌላ ስፍራ ሂጂ።” #2ነገ. 4፥8-37። 2ስለዚህም የኤልሳዕን ምክር ሰምታ ከነቤተሰብዋ ወደ ፍልስጥኤም አገር በመሰደድ እስከ ሰባት ዓመት ቈየች።
3ከሰባቱም የራብ ዓመቶች ፍጻሜ በኋላ ወደ እስራኤል ተመለሰች፤ መኖሪያ ቤትዋና የእርሻ መሬትዋ እንዲመለስላት ለመጠየቅ ወደ ንጉሡ ቀረበች። 4ንጉሡንም የኤልሳዕ አገልጋይ ከሆነው ከግያዝ ጋር ሲነጋገር አገኘችው፤ ንጉሡ ከግያዝ ጋር የሚነጋገረውም ኤልሳዕ ስላደረጋቸው ተአምራት ለማወቅ ፈልጎ ነበር፤ 5ኤልሳዕ የሞተ ሰው ማስነሣቱን ግያዝ ለንጉሡ በሚነግርበት ጊዜ ሴቲቱ መጥታ አቤቱታዋን ለንጉሡ አቀረበች፤ ግያዝ “ንጉሥ ሆይ! ሴትዮዋ እነሆ፥ ይህች ናት፤ ኤልሳዕ ከሞት ያስነሣውም ልጅዋ ይሄ ነው!” በማለት ለንጉሡ አስረዳ። 6ግያዝ ለንጉሡ የሰጠውን መልስ ሴትዮዋ ለንጉሡ እውነት መሆኑን አረጋገጠችለት፤ ስለዚህም ንጉሡ አንድ ባለሥልጣን ጠርቶ፥ የእርስዋ የሆነው ማናቸውም ነገርና እንዲሁም የእርሻ መሬትዋ በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ ያስገኘው የእህል ሰብል ጭምር እንዲመለስላት ትእዛዝ ሰጠላት።
ኤልሳዕና የሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ
7የሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ በታመመ ጊዜ ኤልሳዕ ወደ ደማስቆ ሄደ፤ ንጉሡም የኤልሳዕን መምጣት ሰማ፤ 8ባለሟሎቹ ከሆኑት ባለሥልጣኖች አንዱ የሆነውን አዛሄልን ጠርቶ፥ “ለነቢዩ ስጦታ ይዘህ ሂድና እኔ ከዚህ በሽታ እድን ወይም አልድን እንደ ሆነ እግዚአብሔርን እንዲጠይቅልኝ ለምነው” አለው። 9ስለዚህም አዛሄል በደማስቆ ከሚገኘው ምርጥ የምድር በረከት ሁሉ በአርባ ግመሎች ጭኖ ወደ ኤልሳዕ ሄደ፤ አዛሄልም ኤልሳዕን ባገኘው ጊዜ “ልጅህ ንጉሥ ቤንሀዳድ ከሕመሙ ይድን ወይም አይድን እንደ ሆነ እንድትነግረው እጠይቅህ ዘንድ ልኮኛል” አለው።
10ኤልሳዕም “ቤንሀዳድ እንደሚሞት እግዚአብሔር ገልጦልኛል፤ አንተ ግን ትድናለህ ብለህ ንገረው” አለው፤ 11ከዚህ በኋላ ኤልሳዕ ፊቱን በማጥቈር በሚያስፈራ ሁኔታ አዛሄልን ተመለከተው፤ ከዚህም የተነሣ አዛሄል ተጨነቀ፤ ወዲያውም ኤልሳዕ እንባውን ማፍሰስ ጀመረ፤ 12አዛሄልም “ጌታዬ ስለምን ታለቅሳለህ?” ሲል ጠየቀው።
ኤልሳዕም “በእስራኤል ሕዝብ ላይ የምትፈጽመውን አሠቃቂ ነገር ስለማውቅ ነው፤ ምሽጎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ምርጥ የሆኑ ወጣቶቻቸውን ታርዳለህ፤ ሕፃናታቸውን በድንጋይ ላይ ትፈጠፍጣለህ፤ እርጉዞች የሆኑ ሴቶቻቸውንም ሆድ ትሰነጥቃለህ” ሲል መለሰለት።
13አዛሄልም “እኔ ለምንም የማልጠቅም ኢምንት ነኝ! ታዲያ ይህን ሁሉ ለማድረግ የሚያስችለውን ኀይል ከቶ ከየት አገኛለሁ?” ሲል ጠየቀ። #1ነገ. 19፥15።
ኤልሳዕም “አንተ የሶርያ ንጉሥ እንደምትሆን እግዚአብሔር ገልጦልኛል” ሲል መለሰለት።
14ከዚህም በኋላ አዛሄል ተመልሶ ሲመጣ “ኤልሳዕ ምን አለህ?” ሲል ቤንሀዳድ ጠየቀው።
አዛሄልም “አንተ በእርግጥ እንደምትድን ነግሮኛል” ሲል መለሰለት። 15ነገር ግን በማግስቱ አዛሄል ብርድልብስ ወስዶ ውሃ ውስጥ ነከረ፤ በዚያም ንጉሡን አፍኖ ገደለው።
አዛሄልም በቤንሀዳድ እግር ተተክቶ የሶርያ ንጉሥ ሆነ።
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮራም
(2ዜ.መ. 21፥1-20)
16የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም በይሁዳ ላይ ነገሠ፤ 17እርሱም በነገሠ ጊዜ ሠላሳ ሁለት ዓመቱ ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ስምንት ዓመት ገዛ። 18ሚስቱም የአክዓብ ልጅ ስለ ነበረች እንደ አክዓብ ቤተሰብ የእስራኤል ነገሥታት ይፈጽሙት የነበረውን የክፋት መንገድ ተከተለ፤ በደል በመሥራትም እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ 19እግዚአብሔር ግን ከዘሩ መንግሥትን እንደማያጠፋ ለአገልጋዩ ለዳዊት ተስፋ ሰጥቶት ስለ ነበር ይሁዳን መደምሰስ አልፈለገም። #1ነገ. 11፥36።
20በኢዮራም ዘመነ መንግሥት ኤዶም በይሁዳ ላይ ዐመፀ፤ የራሱንም ነጻ መንግሥት ዐወጀ፤ #ዘፍ. 27፥40። 21ስለዚህም ኢዮራም ሠረገሎቹን በመላ አሰልፎ ወደ ጻዒር ዘመተ፤ የኤዶም ሠራዊትም ከበባቸው፤ በሌሊትም እርሱና የሠረገላዎቹ አዛዦች ከበባውን ጥሰው ሲያመልጡ፥ ወታደሮቹ ወደየቤታቸው ተበታተኑ፤ 22ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ኤዶም ከይሁዳ ተገዢነት ነጻ ወጣች፤ በዚያኑ ጊዜም የልብና ከተማ ዐመፀች።
23ኢዮራም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ 24ኢዮራም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ ውስጥ በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አካዝያስ ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ
(2ዜ.መ. 22፥1-6)
25የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት የኢዮራም ልጅ አካዝያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ 26በነገሠም ጊዜ የኻያ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ አንድ ዓመት ብቻ ገዛ፤ እናቱ ዐታልያ ተብላ የምትጠራው የአክዓብ ልጅ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው የዖምሪ የልጅ ልጅ ነበረች። 27አካዝያስ የንጉሥ አክዓብ ዐማች ከመሆኑ የተነሣ ልክ እንደ አክዓብ ቤተሰብ ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ።
28በሶርያው ንጉሥ አዛሄል ላይ በታወጀው ጦርነት፥ ንጉሥ አካዝያስ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራም ተባባሪ በመሆን ዘመተ፤ የሁለቱም ነገሥታት ሠራዊት ከሶርያውያን ሠራዊት ጋር በገለዓድ በምትገኘው በራሞት ጦርነት በገጠመ ጊዜ ኢዮራም በውጊያው ላይ ቈሰለ፤ 29ኢዮራምም ከንጉሥ ኣዛሄል ጋር ሆኖ በሬማት በተደረገው ጦርነት የደረሰበትን ቊስል ለመፈወስ ወደ ኢይዝራኤል ከተማ ተመለሰ። የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በደረሰበት ጒዳት እርሱን ለመጠየቅ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ሊጠይቀው ወደ ኢይዝራኤል ከተማ ሄደ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 8: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997