የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 9

9
የኢዩ በእስራኤል ላይ ተቀብቶ መንገሥ
1በዚያን ጊዜ ነቢዩ ኤልሳዕ ደቀ መዛሙርቱ ከሆኑት ነቢያት አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “በገለዓድ ወደምትገኘው ወደ ራሞት ለመሄድ ተዘጋጅ፤ ይህንንም የዘይት ማሰሮ ያዝ፤ 2እዚያም በደረስህ ጊዜ የኢዮሣፍጥ ልጅ፥ የኒምሺ የልጅ ልጅ የሆነውን ኢዩን ፈልግ፤ እርሱንም ከጓደኞቹ በማስገለል ወደ ጓዳ አስገባው፤ 3ይህን የወይራ ዘይት በራሱ ላይ አፍስስበት፤ ‘አንተ ተቀብተህ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥ እግዚአብሔር አዞአል’ ብለህም ንገረው፤ ከዚህም በኋላ በሩን በመክፈት በተቻለ ፍጥነት ከዚያ ስፍራ ተነሥተህ ሽሽ።”
4ስለዚህም ወጣቱ ነቢይ ወደ ራሞት ሄደ፤ 5እዚያም እንደ ደረሰ የጦር መኰንኖች ተቀምጠው ሲወያዩ አግኝቶ “ጌታዬ ለአንተ የምሰጥህ መልእክት አለኝ” አለው።
ኢዩም “ከእኛ መካከል ለማንኛችን ነው የምትናገረው?” ሲል ጠየቀው።
ነቢዩም “የምናገረው ለአንተው ነው” ሲል መለሰ። 6ከዚህ በኋላ ሁለቱ ወደ ቤት ውስጥ ገብተው ወጣቱ ነቢይ የወይራውን ዘይት በኢዩ ራስ ላይ አፈሰሰበትና እንዲህ አለው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚናገረው ይህ ነው፤ ‘በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ተቀብተህ እንድትነግሥ አድርጌሃለሁ፤ #1ነገ. 19፥16። 7አንተም የአክዓብ ልጅ የሆነውን ጌታህን ንጉሡን መግደል አለብህ፤ በዚህም ዐይነት የእኔን ነቢያትና ሌሎችንም አገልጋዮቼን የገደለችውን ኤልዛቤልን እበቀላታለሁ፤ 8መላው የአክዓብ ቤተሰብና ትውልዱ ሁሉ መሞት አለባቸው፤ እኔ ከእርሱ ቤተሰብ ወንድ የሆነውን ማንኛውንም ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው አስወግዳለሁ። 9የእስራኤል ነገሥታት በነበሩት በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓምና በአኪያል ልጅ በበዕሻ ቤተሰቦች ላይ ያደረግኹትን፥ ሁሉ በአክዓብ ቤተሰብ ላይ እፈጽማለሁ። 10ኤልዛቤል የመቀበር ዕድል እንኳ አታገኝም፤ የእርስዋም ሬሳ በኢይዝራኤል ግዛት ውሾች ይበሉታል፤’ ” ይህን ሁሉ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ወጣቱ ነቢይ በሩን በመክፈት ከዚያ ክፍል ወጥቶ ሸሸ። #1ነገ. 21፥23።
11ኢዩም፦ ጓደኞቹ ወደሆኑት ወደ ጦር መኰንኖቹ በመጣ ጊዜ “ሁሉ ነገር ሰላም ነውን? ለመሆኑ ይህ እብድ ከአንተ ምን ይፈልጋል?” ሲሉ ጠየቁት።
ኢዩም “ሰውየውንም ሆነ እርሱ የሚናገረውን እናንተ ታውቁታላችሁ” አላቸው።
12እነርሱም “ኧረ እኛ አናውቅም፤ ምን እንደ ተናገረ አስረዳን!” ሲሉ መለሱለት።
ኢዩም፦ “ ‘በእስራኤል ላይ ተቀብተህ እንድትነግሥ እግዚአብሔር አዞአል’ አለኝ” ሲል አስረዳቸው።
13ወዲያውኑ የኢዩ ጓደኞች የነበሩት የጦር መኰንኖች ልብሳቸውን እያወለቁ ኢዩ በሚራመድበት ደረጃ ላይ አነጠፉ፤ በዚያም ላይ እንዲቆም አድርገው እምቢልታ ነፉ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው “ኢዩ ነግሦአል!” ሲሉ ጮኹ።
የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራም መገደል
14-15ከዚያም በኋላ የኢዮሣፍጥ ልጅ የኒምሺ ልጅ ኢዩ በንጉሥ ኢዮራም ላይ ሤራ ማካሄድ ጀመረ፤ ኢዮራም ከሶርያ ንጉሥ አዛሄል ጋር በራሞት በተደረገው ጦርነት ላይ ስለ ቈሰለ በዚያን ጊዜ በኢይዝራኤል ውስጥ በማገገም ላይ ነበር፤ ስለዚህም ኢዩ ጓደኞቹ የሆኑትን የጦር መኰንኖች “እናንተ በእርግጥ ከእኔ ጋር ከሆናችሁ በኢይዝራኤል የሚኖረውን ሕዝብ ለማስጠንቀቅ አንድ ወሬ ነጋሪ እንኳ ከራሞት ወጥቶ እንዳያመልጥ አድርጉ” አላቸው። 16ከዚህም በኋላ ኢዩ በሠረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ገሠገሠ፤ በዚህ ጊዜ ኢዮራም ገና ከቊስሉ አልዳነም ነበር፤ የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስም ሊጠይቀው መጥቶ በዚያ ይገኝ ነበር።
17በኢይዝራኤል ከተማ መጠበቂያ ግንብ ላይ የነበረው ቃፊር ኢዩና ተከታዩ ጭፍራ ሲመጡ መቃረባቸውን አይቶ፥ “ሰዎች እየጋለቡ ሲመጡ አያለሁ!” ሲል የጥሪ ድምፅ አሰማ።
ኢዮራምም “አንድ ፈረሰኛ ልከህ የሚመጡትን ሰዎች ሰላም ነውን? ብሎ እንዲጠይቅ አድርግ” አለው።
18መልእክተኛውም ጋልቦ ሄዶ ኢዩን “ንጉሡ አመጣጥህ በወዳጅነት እንደ ሆነ ማወቅ ይፈልጋል” ሲል ጠየቀው።
ኢዩም “አንተ ከሰላም ጋር ምን ግንኙነት አለህ? ይልቅስ ወደ ኋላ አልፈህ ተከተለኝ!” ሲል መለሰለት።
በከተማይቱም መጠበቂያ ግንብ ላይ የነበረው ዘብ “መልእክተኛው በመምጣት ላይ ወዳለው ጭፍራ ደርሶአል፤ ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም” ሲል አስረዳ፤ 19ሌላም መልእክተኛ ተልኮ ያንኑ ተመሳሳይ ጥያቄ ለኢዩ አቀረበለት፤ ኢዩም “አንተ ከሰላም ጋር ምን ግንኙነት አለህ? ይልቅስ ወደ ኋላ አልፈህ ተከተለኝ!” ሲል መለሰለት።
20“ዘበኛውም እንደገና መልእክተኛው በመምጣት ላይ ወዳለው ጭፍራ ደርሶአል፤ ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም” ካለ በኋላ “የጭፍራው መሪ ሠረገላ አነዳዱ እንደ እብድ ሰው ነው! እንዲያውም ልክ ኢዩን ይመስላል!” ሲል ተናገረ። 21ከዚህ በኋላ ንጉሥ ኢዮራም “ሠረገላዬን አዘጋጅልኝ” ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ ሠረገላውም ተዘጋጅቶለት እርሱና ንጉሥ አካዝያስ በየግል ሠረገላቸው እየጋለቡ ኢዩን ሊገናኙት ወጡ፤ እነርሱም ኢዩን ቀድሞ የናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ አገኙት። 22ኢዮራምም “ኢዩ ሆይ፥ አመጣጥህ በሰላም ነውን?” ሲል ጠየቀ።
ኢዩም፦ “እናትህ ኤልዛቤል ባመጣችው አስማትና የጣዖት አምልኮ ውስጥ ተነክረን እስካለን ድረስ ምን ሰላም አለ?” ሲል መለሰለት።
23ኢዮራምም ድምፁን ከፍ በማድረግ “አካዝያስ ሆይ! ይህ እኮ ክሕደት ነው!” እያለ ሠረገላውን መልሶ ሸሸ። 24ኢዩ ቀስቱን ስቦ ባለው ኀይል በመጠቀም ፍላጻውን ባስፈነጠረ ጊዜ ኢዮራምን ወግቶ በትከሻዎቹ መካከል እስከ ልቡ ዘለቀ፤ ኢዮራምም ሞቶ በሠረገላው ውስጥ ወደቀ። 25ኢዩ ቢድቃር ተብሎ የሚጠራውን የቅርብ ረዳቱን “ሬሳውን አንሥተህ የናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ ወርውረህ ጣለው፤ እኔና አንተ የንጉሥ ኢዮራም አባት ከነበረው ከአክዓብ በስተኋላ እየጋለብን ስንሄድ እግዚአብሔር በአክዓብ ላይ የተናገረውን ቃል አስታውስ፤ 26‘ትናንትና የናቡቴንና የልጆቹን መገደል አየሁ፤ በዚሁ እርሻ ላይ እንደምቀጣህ እምላለሁ’ የሚል ነበር።” ስለዚህ ኢዩ “እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ የኢዮራምን ሬሳ አንሥተህ የናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ በመወርወር ጣለው” ሲል የቅርብ ረዳቱን አዘዘ። #1ነገ. 21፥19።
የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ መገደል
27ንጉሥ አካዝያስ የሆነውን ነገር ሁሉ በተመለከተ ጊዜ በሠረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ቤትሀጋን ከተማ ሸሽቶ ሄደ፤ ኢዩ ተከታትሎ እያሳደደው “እርሱንም ግደሉት!” ሲል ለወታደሮቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም አካዝያስን ተከታትለው በዪብለዓም ከተማ አጠገብ በምትገኘው በጉር የአቀበት መንገድ ላይ በሠረገላው ሲበር መትተው አቈሰሉት፤ እርሱ ግን እንደምንም ጨክኖ መጊዶ ከተማ እስኪደርስ ተጓዘ፤ በዚያም ሞተ፤ 28ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖችም ሬሳውን በሠረገላ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው በዳዊት ከተማ በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብር ቀበሩት።
29አካዝያስ የይሁዳ ንጉሥ የሆነው የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ አንደኛው ዓመት ነበር።
የንግሥት ኤልዛቤል መገደል
30በዚህም ጊዜ ኢዩ ወደ ኢይዝራኤል ደረሰ፤ ኤልዛቤልም ይህን የሆነውን ነገር ሰምታ ዐይንዋን ተኳለች፤ ጠጒርዋንም ተሠርታ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ በመስኮት አዘንብላ ቊልቊል መንገዱን ትመለከት ነበር። 31ኢዩ የቅጽሩን በር አልፎ ሲገባ “አንተ ዚምሪ! አንተ የጌታህ ገዳይ ደግሞ እዚህ ምን አመጣህ?” ስትል ጮኸችበት።
32ኢዩ ቀና ብሎ ወደ ላይ በመመልከት ድምፁን ከፍ አድርጎ “ከእኔ ጋር የሚተባበር ማን ነው?” ሲል ጮኸ፤ ቊጥራቸው ከሁለት እስከ ሦስት የሆነ የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣኖች በመስኮት ብቅ ብለው ወደ እርሱ ተመለከቱ፤ #9፥32 ዚምሪ፦ ከም 16፥8-12 ሌላ ንጉሥ የገደለ የጦር አዛዥ ነው። 33ኢዩም “ኤልዛቤልን ወደታች ወርውሩአት!” አላቸው፤ እነርሱም አንሥተው በወረወሩአት ጊዜ ደምዋ በግንቡና በፈረሶች ላይ ተረጨ፤ ኢዩም በሬሳዋ ላይ ፈረሶቹንና ሠረገላውን ነዳበት፤ 34ወደ ቤተ መንግሥቱም ገብቶ ተመገበ፤ ከዚህም በኋላ “ምንም ቢሆን የንጉሥ ልጅ ነችና፥ ያችን የተረገመች ሴት ወስዳችሁ ቅበሩ” አለ። 35ሊቀብሩአት የሄዱ ሰዎች ግን ከራስ ቅልዋ፥ ከእግሮችዋና ከእጆችዋ አጥንት በቀር ምንም አላገኙም፤ 36ይህንንም ሁሉ ለኢዩ በነገሩት ጊዜ ኢዩ እንዲህ አለ፤ “ይህ ሁሉ የተፈጸመው እግዚአብሔር በአገልጋዩ ቴስቢያዊው በኤልያስ አማካይነት አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ነው፤ ይኸውም ‘የኤልዛቤልም ሬሳ በኢይዝራኤል ግዛት ውሾች ይበሉታል፤ #1ነገ. 21፥23። 37ከሬሳውም የሚተርፈው እንደ ፍግ በዚያ ይበተናል፤ ስለዚህም ማንም እርስዋነትዋን ለይቶ በማወቅ፦ ይህች ኤልዛቤል ናት፥ ሊል አይችልም’ ያለው ነው።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ