ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 35:1-15

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 35:1-15 አማ54

ኢዮስያስም ለእግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ፋሲካ አደረገ፤ በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አረዱ። ካህናቱንም በየሥርዓታቸው አቆመ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ያገለግሉ ዘንድ አጸናቸው። እስራኤልንም ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩት፥ ለእግዚአብሔርም ለተቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አለ “ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ አኑሩት፤ ከዚህም በኋላ በትከሻችሁ ላይ ሸክም አይሆንባችሁም፤ አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዳዊትና ልጁም ሰሎሞን እንደ ጻፉት በየሰሞናችሁና በየአባቶቻችሁ ቤቶች ተዘጋጁ፤ እንደ ሕዝቡም ልጆች እንደ ወንድሞቻችሁ በየአባቶቻችሁ ቤቶች ሆናችሁ በመቅደሱ ቁሙ፤ የሌዋውያንም ነገድ በየወገናቸው እንደ ተከፈሉ እናንተም ተከፈሉ፤ ፋሲካውንም እረዱ፤ እናንተም ተቀደሱ፤ እግዚአብሔርም በሙሴ እጅ የተናገረውን ቃል ያደርጉ ዘንድ ለወንድሞቻችሁ አዘጋጁ።” ኢዮስያስም ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን በዚያ ለነበሩት ለሕዝቡ ልጆች ከመንጋው ሠላሳ ሺህ የበግና የፍየል ጠቦቶች፥ ሦስት ሺህም ወይፈኖች ሰጣቸው፤ እነዚህም ከንጉሡ ሀብት ነበሩ። መሳፍንቱም ለሕዝቡና ለካህናቱ ለሌዋውያኑም በፈቃዳቸው ሰጡ፤ የእግዚአብሔርም ቤት አለቆች፥ ኬልቂያስ፥ ዘካርያስ፥ ይሒኤል፥ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን ሁለት ሺህ ስድስት መቶ በጎችና ፍየሎች፥ ሦስት መቶም በሬዎች ለካህናቱ ሰጡ። የሌዋውያኑም አለቆች ኮናንያ፥ ወንድሞቹም ሸማያና ናትናኤል፥ ሐሸቢያ፥ ይዒኤል፥ ዮዛባት ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን አምስት ሺህ በጎችና ፍየሎች፥ አምስት መቶም በሬዎች ለሌዋውያን ሰጡ። አገልግሎቱም ተዘጋጀ፤ ካህናቱም በስፍራቸው፥ ሌዋውያኑም በየክፍላቸው እንደ ንጉሡ ትእዛዝ ቆሙ። ፋሲካውንም አረዱ፤ ሌዋውያኑም ቁርበቱን ገፈፉ፤ ካህናቱም ከእጃቸው የተቀበሉትን ደም ረጩ። በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ በየአባቶቻቸው ቤቶች ለሕዝቡ ልጆች እንዲሰጡ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለዩ። እንዲሁም በበሬዎቹ አደረጉ። ፋሲካውንም እንደ ሥርዓቱ በእሳት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቍርባን በምንቸትና በሰታቴ፥ በድስትም ቀቀሉ፤ ለሕዝቡም ልጆች ሁሉ በፍጥነት አደረሱ። ከዚያም በኋላ ለራሳቸውና ለካህናቱ አዘጋጁ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን ለማቅረብ እስከ ሌሊት ድረስ ይሠሩ ነበርና ስለዚህ ሌዋውያን ለራሳቸውና ለአሮን ልጆች ለካህናቱ አዘጋጁ። የአሳፍም ልጆች መዘምራን እንደ ዳዊት፥ እንደ አሣፍ፥ እንደ ኤማን፥ የንጉሡም ባለ ራእይ እንደ ነበረው እንደ ኤዶታም ትእዛዝ በየስፍራቸው ነበሩ፤ በረኞቹም በሮቹን ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤ ወንድሞቻቸውም ሌዋውያን ያዘጋጁላቸው ነበርና ከአገልግሎታቸው ይርቁ ዘንድ አያስፈልጋቸውም ነበር።