ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 35:1-15

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 35:1-15 አማ05

ንጉሥ ኢዮስያስ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ክብር የፋሲካን በዓል አከበረ፤ የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን ሕዝቡ የፋሲካን በግ ዐረደ፤ ካህናት የሚያከናውኑትን ተግባር መድቦ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚሰጡት አገልግሎት ላይ አበረታታቸው፤ እንዲሁም ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለለዩ፥ የመላው እስራኤል መምህራን ለሆኑ ሌዋውያን እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጠ፦ “የተቀደሰውን የቃል ኪዳን ታቦት የዳዊት ልጅ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ባሠራው ቤተ መቅደስ ውስጥ አኑሩት፤ ከእንግዲህ ወዲህ እናንተ አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን ማገልገል እንጂ፥ የቃል ኪዳኑን ታቦት በትከሻችሁ ተሸክማችሁ ከስፍራ ወደ ስፍራ መውሰድ የለባችሁም። ንጉሥ ዳዊትና ልጁም ንጉሥ ሰሎሞን በሰጡአችሁ መመሪያ መሠረት በየጐሣችሁ በመመደብ በቤተ መቅደስ አገልግሎት ቦታ ቦታችሁን ያዙ፤ እናንተ ሌዋውያን፥ እያንዳንዱን የእስራኤል ሕዝብ ቤተሰብ ለመርዳት እንድትችሉ እየተከፋፈላችሁ በተቀደሰው ስፍራ በቦታ በቦታቸው ራሳችሁን አደራጁ። ወገኖቻችሁ የሆኑ እስራኤላውያን እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት የሰጠውን መመሪያ በጥንቃቄ ይከተሉ ዘንድ ራሳችሁን አንጽታችሁ የፋሲካን በግ ዕረዱ።” ንጉሥ ኢዮስያስ በዚያው በፋሲካ በዓል የተገኙ ሰዎች መሥዋዕት አድርገው የሚያቀርቡአቸውን የራሱ ሀብት ከሆኑ የቀንድ ከብቶች፥ እንዲሁም የበግና የፍየል መንጋ፥ ሠላሳ ሺህ የበግና የፍየል ጠቦቶችንና ሦስት ሺህ ወይፈኖችን ሰጠ፤ የንጉሡ ባለሟሎች የሆኑ ባለሥልጣኖችም መሥዋዕት ሆነው የሚቀርቡ እንስሶችን በገዛ ፈቃዳቸው ለምእመናን፥ ለካህናትና ለሌዋውያን ሰጡ፤ የቤተ መቅደሱ አለቆች የሆኑት ሊቃነ ካህናቱ ሒልቂያ፥ ዘካርያስና ይሒኤልም የፋሲካ መሥዋዕት ሆነው የሚቀርቡ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ የበግና የፍየል ጠቦቶችንና ሦስት መቶ በሬዎችን ለካህናት ሰጡ፤ የሌዋውያን አለቆች ኮናንያና ወንድሞቹ የሆኑ ሸማዕያና ነታንኤል እንዲሁም ሐሻብያ፥ ይዒኤልና ዮዛባድ ሌዋውያኑ ለፋሲካ በዓል መሥዋዕት አድርገው የሚያቀርቡአቸውን አምስት ሺህ የበግና የፍየል ጠቦቶችን እንዲሁም አምስት መቶ በሬዎችን ሰጡ። ለፋሲካው በዓል የሚሆነው ዝግጅት ከተጠናቀቀ በኋላ፥ ካህናቱ በስፍራቸውና ሌዋውያኑም በየክፍላቸው በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት ቦታ ቦታቸውን ያዙ፤ ለፋሲካውም በዓል የታረዱትን የበግና የፍየል ጠቦቶች ሌዋውያኑ ቆዳቸውን ገፈፉአቸው፤ ካህናቱም ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት የቀረቡትን እንስሶች በየቤተሰቡ ለተመደበው ሕዝብ አከፋፈሉ፤ ይህንንም ያደረጉበት ምክንያት በኦሪት ሕግ በተሰጠው መመሪያ መሠረት መሥዋዕት አድርገው እንዲያቀርቡ ነው፤ እንዲሁም በበሬዎቹ አደረጉ፤ ሌዋውያኑም በሕጉ መሠረት የፋሲካውን መሥዋዕት በእሳት ጠበሱት፤ የተቀደሰውንም ቊርባን በምንቸት፥ በሰታቴና በድስት ቀቅለው ሥጋውን በፍጥነት ለሕዝቡ አከፋፈሉ፤ ከዚህም በኋላ ሌዋውያኑ ለራሳቸውና የአሮን ዘሮች ለሆኑት ካህናት የፋሲካን መሥዋዕት አዘጋጁ፤ ይህንንም ያደረጉት ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን በሙሉ ለማቃጠል እስከ ሌሊት ድረስ ይሠሩ ስለ ነበር ነው፤ ከዚህ በታች ስማቸው የተመለከተው የሌዋዊው የአሳፍ ጐሣ የሆኑ መዘምራንም ንጉሥ ዳዊት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት፥ በተመደበላቸው ስፍራ ነበሩ፤ እነርሱም አሳፍ፥ ሄማንና የንጉሡ ነቢይ ይዱታን ናቸው፤ ሌሎች ሌዋውያን የፋሲካውን መሥዋዕት ያዘጋጁላቸው ስለ ነበር፥ የቤተ መቅደሱ ዘብ ጠባቂዎች ስፍራቸውን አይተዉም ነበር፤