የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 24

24
ኢዮአስ ቤተ መቅደሱን እንዳደሠ
(2ነገ. 12፥1-16)
1ኢዮአስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሰባት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አርባ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች። 2በካህኑም በዮዳሄ ዘመን ሁሉ ኢዮአስ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። 3ዮዳሄም ሁለት ሚስቶች አጋባው፤ ወንዶችና ሴቶችም ልጆችንም ወለደ።
4ከዚህም በኋላ ኢዮአስ የእግዚአብሔርን ቤት ይጠግን ዘንድ አሰበ። 5ካህናትንና ሌዋውያንን ሰብስቦ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ውጡ፤ የአምላካችሁንም ቤት በየዓመቱ ለማደስ ከእስራኤል ሁሉ ገንዘብን ሰብስቡ፤ ነገሩንም ፈጥናችሁ አድርጉ” አላቸው። ሌዋውያን ግን ቸል አሉ። 6ንጉሡም አለቃውን ዮዳሄን ጠርቶ “የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ስለ ምስክሩ ድንኳን የእስራኤል ጉባኤ እንዲያወጣ ያዘዘውን ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ያመጡ ዘንድ ስለ ምን ሌዋውያንን አላተጋሃቸውም?” አለ። 7ጎቶሊያ ከሐዲት ነበረችና ልጆችዋም የእግዚአብሔርን ቤት አፍርሰዋልና፤ በእግዚአብሔርም ቤት ተቀድሶ የነበረውን ሁሉ ለበኣሊም ሰጥተዋልና።
8ንጉሡም አዘዘ፤ ሣጥንም ሠርተው በእግዚአብሔር ቤት በር አጠገብ በስተ ውጭ አኖሩት። 9የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ በእስራኤል ላይ ያዘዘውን ግብር ለእግዚአብሔር ያመጡ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም አዋጅ ነገሩ። 10አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ደስ ብሎአቸው አቀረቡት፤ እስኪሞላም ድረስ በሣጥኑ ውስጥ ጣሉት። 11ሣጥኑም በሌዋውያን እጅ ወደ ንጉሡ ሹማምት በደረሰ ጊዜ፥ ብዙ ገንዘብም እንዳለበት ባየ ጊዜ፥ የንጉሡ ጸሐፊና የዋነኛው ካህን ሹም እየመጡ ብሩን ከሣጥን ያወጡ ነበር፤ ሣጥኑንም ደግሞ ወደ ስፍራው ይመልሱት ነበር። እንዲሁም በየቀኑ ያደርጉ ነበር፤ ብዙም ገንዘብ አከማቹ። 12ንጉሡና ዮዳሄም በእግዚአብሔር ቤት ሥራ ላይ ለተሾሙት ሰጡአቸው፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤት የሚጠግኑትን ጠራቢዎችንና አናጢዎችን፥ የእግዚአብሔርንም ቤት የሚያድሱትን የብረትና የናስ ሠራተኞችን ይገዙበት ነበር። 13ሠራተኞችም ሠሩ፤ የፈረሰውም በእጃቸው ተጠገነ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት እንደ ቀድሞው ሥራ መለሱ፤ አጽንተውም አቆሙት። 14በጨረሱም ጊዜ የተረፈውን ገንዘብ በንጉሡና በዮዳሄ ፊት አመጡ፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር ቤት ዕቃ፥ ለአገልግሎትና ለቍርባን ዕቃ፥ ለጭልፋዎችም፥ ለወርቅና ለብርም ዕቃ አደረጉት። በዮዳሄም ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔር ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት ሁልጊዜ ያቀርቡ ነበር።
15ዮዳሄም ሸመገለ፤ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ፤ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሠላሣ ዓመት ነበረ። 16ከእስራኤልም ጋር፥ ከእግዚአብሔርና ከቤቱም ጋር ቸርነትን ሠርቶአልና በዳዊት ከተማ ከነገሥታቱ ጋር ቀበሩት።
ንጉሥ ኢዮአስ ከእግዚአብሔር እንደራቀ
17ዮዳሄም ከሞተ በኋላ የይሁዳ አለቆች ገብተው ለንጉሡ እጅ ነሡ፤ ንጉሡም እሺ አላቸው። 18የአባቶቻቸውንም አምላክ እግዚአብሔርን ትተው የማምለኪያ ዐጸዶችንና ጣዖታትን አመለኩ፤ በዚህ በደላቸውም ምክንያት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ቍጣ ወረደ። 19ወደ እግዚአብሔርም ይመልሱአቸው ዘንድ ነቢያትን ይሰድድላቸው ነበር፤ መሰከሩባቸውም፤ እነርሱ ግን አላደመጡም።
20የእግዚአብሔርም መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆመና “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? መልካምም አይሆንላችሁም፤ እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁ እርሱ ትቶአችኋል’” አላቸው። 21ተማማሉበትም በንጉሡም ትእዛዝ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ወገሩት። 22እንዲሁም ንጉሡ ኢዮአስ ዮዳሄ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፤ ልጁንም ዘካርያስን አስገደለው፤ እርሱም ሲሞት “እግዚአብሔር ይየው፤ ይፈልገውም” አለ።
23ዓመቱም ካለፈ በኋላ የሶርያውያን ሠራዊት መጡበት፤ ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌምም መጥተው ከሕዝቡ መካከል የሕዝቡን አለቆች ሁሉ አጠፉ፤ ምርኮአቸውንም ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ደማስቆ ላኩ። 24የሶርያውያንም ሠራዊት ቍጥር ጥቂት ሆኖ ሳለ እግዚአብሔር ታላቅን ሠራዊት አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው፤ ይህም የሆነው የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ትተው ስለ ነበረ ነው። እነርሱም በኢዮአስ ላይ ፍርድ ፈረዱበት።
25ከእርሱም ዘንድ አልፈው ከሄዱ በኋላ እጅግ ታምሞ ነበር፤ የገዛ ባሪያዎቹም ስለ ካህኑ ስለ ዮዳሄ ልጅ ተበቅለው ተማማሉበት፤ በአልጋውም ላይ ገደሉት፤ ሞተም፤ በዳዊት ከተማ እንጂ በነገሥታት መቃብር አልቀበሩትም። 26የተማማሉበትም የአሞናዊቱ የሰምዓት ልጅ ዛባድ፥ የሞዓባዊቱም የሰማሪት ልጅ ዮዛባት ነበሩ። 27የልጆቹና በእርሱ ላይ የተደረገው ነገር የእግዚአብሔርንም ቤት ማደሱ፥ እነሆ፥ በነገሥታቱ መጽሐፍ ተጽፎአል። ልጁም አሜስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ