የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 23

23
ካህኑ ዮዳሄ ኢዮአስን እንዳነገሠ (2ነገ. 11፥ 4-21)
1በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ በረታ፤ የመቶ አለቆቹንም፥ የይሮሐምን ልጅ ዓዛርያስን፥ የይሆሐናንንም ልጅ ይስማኤልን፥ የዖቤድንም ልጅ ዓዛሪያስን፥ የዓዳያንም ልጅ መዕሤያን፥ የዝክሪንም ልጅ ኤሊሳፋጥን ወስዶ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። 2ይሁዳንም ዞሩ፤ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ሌዋውያንንና የእስራኤልን አባቶች ቤቶች አለቆች ሰብስበው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 3ጉባኤውም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ከንጉሥ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ዮዳሄም አላቸው “እነሆ፥ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ልጆች እንደተናገረ የንጉሡ ልጅ ይነግሣል። 4የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሰንበት ቀን ከምትገቡት ከእናንተ ከካህናትና ከሌዋዊውያን ከሦስት አንድ እጅ በመግቢያ በሮች በረኞች ሁኑ፤ 5ከሦስት አንድ እጅም በንጉሥ ቤት ሁኑ፤ አንድ እጅም በመካከለኛው በር ሁኑ፤ ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ይሁኑ። 6ወደ እግዚአብሔር ቤት ግን ከካህናትና ከአገልጋዮቹ ሌዋውያን በቀር ማንም አይግባ፤ እነርሱ ቅዱሳን ናቸውና ይግቡ፤ ሕዝቡም ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ይጠብቅ። 7ሌዋውያንም የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው ንጉሡን በዙሪያው ይክበቡት፤ ወደ ቤቱም የሚገባ ይገደል ንጉሡም ሲገባና ሲወጣ ከእርሱ ጋር ሁኑ።” 8ሌዋውያንና ይሁዳም ሁሉ ካህኑ ዮዳሄ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ ካህኑም ዮዳሄ ሰሞነኞቹን አላሰናበተም ነበርና እያንዳንዱ በሰንበት ቀን ይገቡ የነበሩትን በሰንበትም ቀን ይወጡ የነበሩትን ሰዎች ወሰደ። 9ካህኑም ዮዳሄ በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን የንጉሡን የዳዊትን ጋሻና ጦር አላባሽ አግሬውንም ጋሻ ለመቶ አለቆች ሰጣቸው። 10ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ የጦር መሣሪያውን በእጁ እየያዘ በንጉሡ ዙሪያ ከቤቱ ቀኝ እስከ ቤቱ ግራ ድረስ በመሠዊያውና በቤቱ አጠገብ እንዲቆም አደረገ። 11የንጉሡንም ልጅ አውጥተው ዘውዱን ጫኑበት፤ ምስክሩንም ሰጡት፤ አነገሡትም፤ ዮዳሄና ልጆቹም “ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ!” እያሉ ቀቡት።
12ጎቶሊያም የሚሮጡትንና ንጉሡን የሚያመሰግኑትን የሕዝቡን ድምጽ በሰማች ጊዜ ወደ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ቤት መጣች። 13እነሆም፥ ንጉሡ በመግቢያው በዓምዱ አጠገብ ሆኖ፥ ከንጉሡም ጋር አለቆችና መለከተኞች ቆመው አየች። የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ ብሎአቸው መለከቱን ይነፉ ነበር፤ መዘምራንም በዜማ ዕቃ እያዜሙ የምስጋና መዝሙር ይዘምሩ ነበር። ጎቶሊያም ልብስዋን ቀድዳ “ዓመፅ ነው! ዓመፅ ነው!” ብላ ጮኸች። 14ካህኑም ዮዳሄ በጭፍራው ላይ የተሾሙትን የመቶ አለቆች “ወደ ሰልፉ መካከል አውጡአት የሚከተላትም በሰይፍ ይገደል” ብሎ አዘዛቸው። ካህኑም “በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ አትግደሉአት” አለ። 15ገለልም ብለው አሳለፉአት፤ እርስዋም ወደ ፈረሱ በር መግቢያ ወደ ንጉሡ ቤት ሄደች፤ በዚያም ገደሉአት።
16ዮዳሄም በእርሱና በሕዝቡ ሁሉ በንጉሡም መካከል የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረገ። 17ሕዝቡም ሁሉ ወደ ባኣል ቤት ሄደው አፈረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹንም አደቀቁ፤ የባኣልንም ካህን ማታንን በመሠዊያው ፊት ገደሉት። 18ዮዳሄም በሙሴ ሕግ እንደተጻፈው፥ እንደ ዳዊትም ትእዛዝ፥ በደስታና በመዝሙር ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ ዳዊት በእግዚአብሔር ቤት የከፈላቸውን ካህናትና ሌዋውያን በእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ላይ ሾመ። 19በማናቸውም ነገር ሁሉ ርኩስ የሆነ ሰው እንዳይገባ በእግዚአብሔር ቤት በር በረኞችን አኖረ። 20የመቶ አለቆችንም፥ ከበርቴዎቹንም፥ የሕዝቡንም አለቆች፥ የአገሩንም ሕዝብ ሁሉ ወሰደ፤ ንጉሡንም ከእግዚአብሔር ቤት አወረደ፤ በላይኛውም በር በኩል ወደ ንጉሡ ቤት መጡ፤ ንጉሡንም በመንግሥቱ ዙፋን ላይ አኖሩት። 21የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አላቸው፤ ከተማይቱም ጸጥ አለች፤ ጎቶሊያንም በሰይፍ ገደሉአት።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ