ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 25
25
አሜስያስ በይሁዳ እንደነገሠ (2ነገ. 14፥1-6)
1አሜስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 2በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ነገር ግን በፍጹም ልብ አይደለም። 3መንግሥትም በጸናለት ጊዜ አባቱን የገደሉትን ባሪያዎች ገደለ። 4በሙሴም ሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔርም “ሰው ሁሉ በገዛ ኃጢአቱ ይሙት እንጂ አባቶች በልጆች ፋንታ አይሙቱ፤ ልጆችም በአባቶች ፋንታ አይሙቱ” ብሎ እንዳዘዘ የነፍሰ ገዳዮችን ልጆች አልገደለም።
ኤዶማዊያን ድል እንደተሆኑ (2ነገ. 14፥ 7)
5አሜስያስም ይሁዳን ሰበሰበ፤ በእየአባቶቻቸውም ቤቶች ከሺህ አለቆችና ከመቶ አለቆች እጅ በታች አቆማቸው፤ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን የይሁዳንና ብንያምን ሁሉ ቋጠረ፤ ለሰልፍም የሚወጡ፥ ጋሻና ጦርም የሚይዙ ሦስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች አገኘ። 6ደግሞም ከእስራኤል ዘንድ መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን በመቶ መክሊት ብር ቀጠረ። 7አንድ የእግዚአብሔር ሰው ግን ወደ እርሱ መጥቶ “ንጉሥ ሆይ! እግዚአብሔር ከእስራኤልና ከኤፍሬም ልጆች ጋር አይደለምና የእስራኤል ጭፍራ ከአንተ ጋር አይውጣ። 8ብትሄድ ግን፥ በእነርሱም ማሸነፍን ብታስብ፥ የመርዳትና የመጣል ኃይል ከእግዚአብሔር ዘንድ ነውና እግዚአብሔር በጠላቶችህ ፊት ይጥልሃል” አለው። 9አሜስያስም የእግዚአብሔርን ሰው “ለእስራኤል ጭፍራ የሰጠሁት መቶ መክሊት ምን ይሁን?” አለው። የእግዚአብሔርም ሰው “ከዚህ አብልጦ ይሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ይችላል” ብሎ መለሰለት። 10አሜስያስም ከኤፍሬም የመጡት ጭፍሮች ወደ ስፍራቸው ይመለሱ ዘንድ ለይቶ አሰናበታቸው፤ ስለዚህም ቍጣቸው በይሁዳ ላይ ጸና፤ ወደ አገራቸውም በጽኑ ቍጣ ተመለሱ። 11አሜስያስም በረታ፤ ሕዝቡንም አውጥቶ ወደ ጨው ሸለቆ ሄደ፤ ከሴይርም ልጆች አሥር ሺህ ገደለ። 12የይሁዳም ልጆች ደግሞ አሥር ሺህ ሰዎችን በሕይወታቸው ማረኩ፤ ወደ ዓለቱም ራስ ላይ አመጡአቸው፤ ከዓለቱም ራስ ላይ ጣሉአቸው፤ ሁሉም ተፈጠፈጡ። 13አሜስያስ ግን ከእርሱ ጋር ወደ ሰልፍ እንዳይሄዱ ያሰናበታቸው ጭፍሮች ከሰማርያ ጀምረው እስከ ቤትሖሮን ድረስ በይሁዳ ከተሞች ላይ አደጋ ጣሉ፤ ከእነርሱም ሦስት ሺህ ገደሉ፤ ብዙ ምርኮም ማረኩ።
14አሜስያስም የኤዶማያስን ሰዎች ከገደለ በኋላ የሴይርን ልጆች አማልክት አመጣ፤ የእርሱም አማልክት ይሆኑ ዘንድ አቆማቸው፤ ይሰግድላቸው፥ ያጥንላቸውም ነበር። 15ስለዚህም የእግዚአብሔር ቍጣ በአሜስያስ ላይ ነደደና “ሕዝባቸውን ከአንተ እጅ ያላዳኑትን የአሕዛብን አማልክት ስለ ምን ፈለግሃቸው?” የሚል ነቢይ ሰደደበት። 16እርሱም ሲናገር ንጉሡ “በውኑ አንተ የንጉሡ አማካሪ ልትሆን ሾመነሃልን? ተው፤ ቅጣትን ስለ ምን ትሻለህ?” አለው። ነቢዩም “ይህን አድርገሃልና፥ ምክሬንም አልሰማህምና እግዚአብሔር ሊያጠፋህ እንዳሰበ አወቅሁ” ብሎ ተወ።
እስራኤል ይሁዳን ድል እንዳደረገ (2ነገ14፥ 8-14)
17የይሁዳም ንጉሥ አሜስያስ ምክር አደረገና “ና፥ እርስ በርሳችን ፊት ለፊት እንተያይ” ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደኢዩ ልጅ ወደ ኢዮአካዝ ልጅ ወደ ኢዮአስ ላከ። 18የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአያስ “የሊባኖስ ኵርንችት ‘ልጅህን ለልጄ ሚስት አድርገህ ስጠው’ ብሎ ወድ ሊባኖስ ዝግባ ላከ፤ የሊባኖስም አውሬ አልፎ ኵርንችቱን ረገጠ። 19አንተም ‘እነሆ፥ ኤዶምያስን መትቻለሁ’ ብለህ ኵርተሃል፤ በቤትህ ተቀመጥ፤ አንተ ከይሁዳ ጋር ትወድቅ ዘንድ ስለ ምን መከራ ትሻላህ?” ብሎ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ ላከ።
20የኤዶምያስንም አማልክት ስለ ፈለጉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበረና አሜስያስ አልሰማም። 21የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ ወጣ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ባለች በቤትሳሚስ ላይ እርስ በርሳቸው ተያዩ። 22ይሁዳም በእስራኤል ፊት ተመታ፤ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ። 23የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን በቤትሳሚስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር ከኤፍሬም በር ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ አራት መቶ ክንድ አፈረሰ። 24ወርቁንና ብሩን ሁሉ፥ በእግዚአብሔርም ቤት ከዖቤድኤዶም ጋር የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ፥ የንጉሡም ቤት መዛግብት፥ በመያዣ የተያዙትንም ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
25የይሁዳም ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ከእስራኤል ንጉሥ ከኢዮአካዝ ልጅ ከኢዮአስ ሞት በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ። 26የቀረውም የፊተኛውና የኋላኛው የአሜስያስ ነገር፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 27አሜስያስም እግዚአብሔርን ከመከተል ከራቀ በኋላ በኢየሩሳሌም የዓመፅ መሐላ አደረጉበት፤ ወደ ለኪሶም ኵበለለ፤ በስተ ኋላውም ወደ ለኪሶ ላኩ፤ በዚያም ገደሉት። 28በፈረስም ጭነው አመጡት፤ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 25: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ