አቢግያም ዳዊትን ባየች ጊዜ ከአህያዋ ላይ ፈጥና ወረደች፥ በዳዊትም ፊት በግምባርዋ ወደቀች፥ በምድርም ላይ እጅ ነሣች። በእግሩም ላይ ወደቀች፥ እንዲህም አለች፦ ጌታዬ ሆይ፥ ይህ ኃጢአት በእኔ ላይ ይሁን፥ እኔ ባሪያህ በጆሮህ ልናገር፥ የባሪያህንም ቃል አድምጥ። በዚህ ምናምንቴ ሰው በናባል ላይ ጌታዬ ልቡን እንዳይጣል እለምናለሁ፥ እንደ ስሙ እንዲሁ እርሱ ነው፥ ስሙ ናባል ነው፥ ስንፍናም አድሮበታል፥ እኔ ባሪያህ ግን ከአንተ የተላኩትን የጌታዬን ጕልማሶች አላየሁም። አሁንም፥ ጌታዬ ሆይ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! ወደ ደም እንዳትገባ፥ እጅህም ራስህን እንዳታድን የከለከለህ እግዚአብሔር ነው፥ አሁንም ጠላቶችህና በጌታዬ ላይ ክፉ የሚሹ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ። አሁንም ባሪያህ ወደ ጌታዬ ያመጣችው ይህ መተያያ ጌታዬን ለሚከተሉ ጕልማሶች ይሰጥ። የእግዚአብሔርን ጦርነት ስለምትዋጋ እግዚአብሔር በእውነት ለጌታዬ የታመነ ቤት ይሠራልና የእኔን የባሪያህን ኃጢአት፥ እባክህ፥ ይቅር በል፥ በዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህም። ያሳድድህ ዘንድ ነፍስህንም ይሻ ዘንድ ሰው ቢነሣ፥ የጌታዬ ነፍስ በሕያዋን ወገን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የታሰረች ትሆናለች፥ የጠላቶችህንም ነፋስ ከወንጭፍ እንደሚጣል እንዲሁ ይጥላታል። እግዚአብሔርም ለጌታዬ የተናገረውን ቸርነት ሁሉ ባደረገልህ ጊዜ፥ በእስራኤልም ላይ አለቃ አድርጎ ባስነሣህ ጊዜ፥ አንተ በከንቱ ደም እንዳላፈሰስህ፥ በገዛ እጅህም እንዳልተሳካልህ ይህ ዕንቅፋትና የሕሊና ጸጸት በጌታዬ አይሆንልህም፥ እግዚአብሔርም ለጌታዬ በጎ ባደረገልህ ጊዜ፥ ባሪያህን አስብ። ዳዊትም አቢግያን አላት፦ ዛሬ እኔን ለመገናኘት አንቺን የሰደደ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። ወደ ደም እንዳልሄድ፥ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን፥ አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ። ነገር ግን ክፉ እንዳላደርግብሽ የከለከለኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔን ለመገናኘት ፈጥነሽ ባልመጣሽ ኖሮ፥ እስኪነጋ ድረስ ለናባል አንድ ወንድ ስንኳ ባልቀረውም ነበር። ዳዊትም ያመጣችውን ከእጅዋ ተቀብሎ፦ በደኅና ወደ ቤትሽ ሂጂ፥ እነሆ፥ ቃልሽን ሰማሁ፥ ፊትሽንም አከበርሁ አላት። አቢግያም ወደ ናባል መጣች፥ እነሆም፥ በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ግብዣ ያደርግ ነበር፥ ናባልም እጅግ ሰክሮ ነበርና ልቡ ደስ ብሎት ነበር፥ ስለዚህም እስኪነጋ ድረስ ታናሽ ነገር ወይም ታላቅ ነገር አልነገረችውም ነበር። በነጋውም የጠጁ ስካር ከናባል ባለፈ ጊዜ ሚስቱ ይህን ነገር ነገረችው፥ ልቡም በውስጡ ሞተ፥ እንደ ድንጋይም ሆነ፥ ከአሥር ቀንም በኋላ እግዚአብሔር ናባልን ቀሠፈው፥ እርሱም ሞተ። ዳዊትም ናባል እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ፦ ከናባል እጅ የስድቤን ፍርድ የፈረደልኝ፥ ባሪያውንም ከክፋት የጠበቀ እግዚአብሔር ይመስገን፥ እግዚአብሔርም የናባልን ክፋት በራሱ ላይ መለሰ አለ። ዳዊትም ልኮ ያገባት ዘንድ አቢግያን ተነጋገራት። የዳዊትም ባሪያዎች ወደ ቀርሜሎስ ወደ አቢግያ በመጡ ጊዜ፦ ዳዊት ያገባሽ ዘንድ ወደ አንቺ ልኮናል ብለው ነገሩአት። ተነሥታም በግምባርዋ ወድቃ እጅ ነሣችና፦ እነሆ፥ እኔ ገረድህ የጌታዬን ሎሌዎች እግር አጥብ ዘንድ አገልጋይ ነኝ አለች። አቢግያም ፈጥና ተነሣች፥ በአህያም ላይ ተቀመጠች፥ አምስቱም ገረዶችዋ ተከተሉአት፥ የዳዊትንም መልእክተኞች ተከትላ ሄደች፥ ሚስትም ሆነችው። ዳዊትም ደግሞ ኢይዝራኤላዊቱን አኪናሆምን ወሰደ፥ ሁለቱም ሚስቶች ሆኑለት። ሳኦል ግን የዳዊትን ሚስት ልጁን ሜልኮልን አገሩ ጋሊም ለነበረው ለሌሳ ልጅ ለፈልጢ ሰጥቶ ነበር።
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 25 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 25:23-44
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos