የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 25

25
1ሳሙኤልም ሞተ፥ እስራኤልም ሁሉ ተሰብስበው አለቀሱለት፥ በአርማቴምም በቤቱ ቀበሩት። ዳዊትም ተነሥቶ ወደ ፋራን ምድረ በዳ ወረደ።
2በማዖንም የተቀመጠ አንድ ሰው ነበረ፥ ከብቱም በቀርሜሎስ ነበረ፥ እጅግም ታላቅ ሰው ነበረ፥ ለእርሱም ሦስት ሺህ በጎችና አንድ ሺህ ፍየሎች ነበሩት፥ በቀርሜሎስም በጎቹን ይሸልት ነበር። 3የሰውዮውም ስም ናባል፥ የሚስቱም ስም አቢግያ ነበረ፥ የሴቲቱም አእምሮ ታላቅ፥ መልክዋም የተዋበ ነበረ፥ ሰውዮው ግን ባለጌ ነበረ፥ ግብሩም ክፉ ነበረ፥ ከካሌብም ወገን ነበረ። 4ዳዊትም በምድረ በዳ ሳለ፦ ናባል በጎቹን ይሸልታል የሚል ወሬ ሰማ። 5ዳዊትም አሥር ጕልማሶች ላከ ለጕልማሶችም አለ፦ ወደ ቀርሜሎስ ወጥታችሁ ወደ ናባል ሂዱ፥ በስሜም ስለ ሰላም ጠይቁት፥ እንዲህም በሉት፦ 6በደኅንነት ኑር፥ ለአንተና ለቤትህም ለአንተም ላሉት ሁሉ ሰላም ይሁን። 7አሁንም በጎችህን እንድትሸልት ሰምቻለሁ፥ እረኞችህም ከእኛ ጋር ነበሩ፥ ከቶ አልበደልናቸውም፥ በቀርሜሎስም በተቀመጡበት ዘመን ሁሉ ከመንጋው አንዳች አልጎደለባቸውም። 8ጕልማሶችህን ጠይቃቸው፥ እነርሱም ይነግሩሃል፥ አሁንም እንግዲህ በመልካም ቀን መጥተንብሃልና ጕልማሶች በፊትህ ሞገስ ያግኙ፥ በእጅህም ከተገኘው ለባሪያዎችህና ለልጅህ ለዳዊት፥ እባክህ፥ ስጥ።
9የዳዊትም ጕልማሶች መጡ፥ ይህንም ቃል ሁሉ በዳዊት ስም ለናባል ነግረው ዝም አሉ። 10ናባልም ለዳዊት ባሪያዎች፦ ዳዊት ማን ነው? የእሴይስ ልጅ ማን ነው? እያንዳንዳቸው ከጌቶቻቸው የኮበለሉ ባሪያዎች ዛሬ ብዙዎች ናቸው። 11እንጀራዬንና የወይን ጠጄን ለሸላቾቼም ያረድሁትን ሥጋ ወስጄ ከወዴት እንደ ሆኑ ለማላውቃቸው ሰዎች እሰጣለሁን? ብሎ መለሰላቸው። 12የዳዊትም ጕልማሶች ዞረው በመጡበት መንገድ ተመለሱ፥ መጥተውም ይህን ነገር ሁሉ ለዳዊት ነገሩት። 13ዳዊትም ሰዎቹን፦ ሁላችሁ ሰይፋችሁን ታጠቁ አላቸው። ሁሉም ሰይፋቸውን ታጠቁ፥ ዳዊትም ሰይፉን ታጠቀ፥ አራት መቶ ሰዎችም ዳዊትን ተከትለው ወጡ፥ ሁለት መቶውም በዕቃው ዘንድ ተቀመጡ።
14ከብላቴኖቹ አንዱ ለናባል ሚስት ለአቢግያ እንዲህ ብሎ ነገራት፦ እነሆ፥ ዳዊት በምድረ በዳ ሳለ ጌታችንን ሊባርኩ መልእክተኞች ላከ፥ እርሱ ግን ሰደባቸው። 15እነዚህ ሰዎች ግን በእኛ ዘንድ እጅግ መልካም ነበሩ፥ አልበደሉንምም፥ ከእነርሱም በሄድንበት ዘመን ሁሉ በምድረ በዳ ሳለን አንዳች አልጠፋብንም፥ 16ከእነርሱ ጋር ሆነን መንጋውን በጠበቅንበት ዘመን ሁሉ ሌሊትና ቀን አጥር ሆነውን ነበር። 17ስለዚህም በጌታችንና በቤቱ ሁሉ ላይ ክፉ ነገር እንዲመጣ ተቆርጦአልና፥ እርሱ ምናምንቴ ሰው ስለ ሆነ ማንም ሊናገረው አይችልምና የምታደርጊውን ተመልከቺና እወቂ።
18አቢግያም ፈጥና ሁለት መቶ እንጀራ፥ ሁለት አቁማዳ የወይን ጠጅ፥ አምስትም የተዘጋጁ በጎች፥ አምስትም መስፈሪያ ጥብስ እሸት፥ አንድ መቶ ዘለላ ዘቢብ፥ ሁለት መቶም የበለስ ጥፍጥፍ ወሰደች፥ በአህዮችም ላይ አስጫነች። 19ለብላቴኖችዋም፦ አስቀድማችሁ በፊቴ ሂዱ፥ እነሆም፥ እከተላችኋለሁ አለች። ይህንም ለባልዋ ለናባል አልነገረችውም። 20እርስዋም በአህያዋ ላይ ተቀምጣ በተራራው ላይ በተሰወረ ስፍራ በወረደች ጊዜ፥ እነሆ፥ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እርስዋ ወረዱ፥ እርስዋም ተገናኘቻቸው። 21ዳዊትም፦ ለዚህ ሰው ከሆነው ሁሉ አንድ ነገር እንዳይጠፋበት በእውነት ከብቱን ሁሉ በምድረ በዳ በከንቱ ጠበቅሁ፥ እርሱም ስለ በጎነቴ ክፋት መለሰልኝ። 22ለእርሱም ከሆነው ሁሉ እስከ ነገ ጥዋት ድረስ አንድ ወንድ ስንኳ ብተው እግዚአብሔር በዳዊት ላይ እንዲህ ያድርግ እንዲህም ይጨምር ብሎ ነበር።
23አቢግያም ዳዊትን ባየች ጊዜ ከአህያዋ ላይ ፈጥና ወረደች፥ በዳዊትም ፊት በግምባርዋ ወደቀች፥ በምድርም ላይ እጅ ነሣች። 24በእግሩም ላይ ወደቀች፥ እንዲህም አለች፦ ጌታዬ ሆይ፥ ይህ ኃጢአት በእኔ ላይ ይሁን፥ እኔ ባሪያህ በጆሮህ ልናገር፥ የባሪያህንም ቃል አድምጥ። 25በዚህ ምናምንቴ ሰው በናባል ላይ ጌታዬ ልቡን እንዳይጣል እለምናለሁ፥ እንደ ስሙ እንዲሁ እርሱ ነው፥ ስሙ ናባል ነው፥ ስንፍናም አድሮበታል፥ እኔ ባሪያህ ግን ከአንተ የተላኩትን የጌታዬን ጕልማሶች አላየሁም። 26አሁንም፥ ጌታዬ ሆይ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! ወደ ደም እንዳትገባ፥ እጅህም ራስህን እንዳታድን የከለከለህ እግዚአብሔር ነው፥ አሁንም ጠላቶችህና በጌታዬ ላይ ክፉ የሚሹ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ። 27አሁንም ባሪያህ ወደ ጌታዬ ያመጣችው ይህ መተያያ ጌታዬን ለሚከተሉ ጕልማሶች ይሰጥ። 28የእግዚአብሔርን ጦርነት ስለምትዋጋ እግዚአብሔር በእውነት ለጌታዬ የታመነ ቤት ይሠራልና የእኔን የባሪያህን ኃጢአት፥ እባክህ፥ ይቅር በል፥ በዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህም። 29ያሳድድህ ዘንድ ነፍስህንም ይሻ ዘንድ ሰው ቢነሣ፥ የጌታዬ ነፍስ በሕያዋን ወገን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የታሰረች ትሆናለች፥ የጠላቶችህንም ነፋስ ከወንጭፍ እንደሚጣል እንዲሁ ይጥላታል። 30እግዚአብሔርም ለጌታዬ የተናገረውን ቸርነት ሁሉ ባደረገልህ ጊዜ፥ በእስራኤልም ላይ አለቃ አድርጎ ባስነሣህ ጊዜ፥ 31አንተ በከንቱ ደም እንዳላፈሰስህ፥ በገዛ እጅህም እንዳልተሳካልህ ይህ ዕንቅፋትና የሕሊና ጸጸት በጌታዬ አይሆንልህም፥ እግዚአብሔርም ለጌታዬ በጎ ባደረገልህ ጊዜ፥ ባሪያህን አስብ።
32ዳዊትም አቢግያን አላት፦ ዛሬ እኔን ለመገናኘት አንቺን የሰደደ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። 33ወደ ደም እንዳልሄድ፥ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን፥ አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ። 34ነገር ግን ክፉ እንዳላደርግብሽ የከለከለኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔን ለመገናኘት ፈጥነሽ ባልመጣሽ ኖሮ፥ እስኪነጋ ድረስ ለናባል አንድ ወንድ ስንኳ ባልቀረውም ነበር። 35ዳዊትም ያመጣችውን ከእጅዋ ተቀብሎ፦ በደኅና ወደ ቤትሽ ሂጂ፥ እነሆ፥ ቃልሽን ሰማሁ፥ ፊትሽንም አከበርሁ አላት።
36አቢግያም ወደ ናባል መጣች፥ እነሆም፥ በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ግብዣ ያደርግ ነበር፥ ናባልም እጅግ ሰክሮ ነበርና ልቡ ደስ ብሎት ነበር፥ ስለዚህም እስኪነጋ ድረስ ታናሽ ነገር ወይም ታላቅ ነገር አልነገረችውም ነበር። 37በነጋውም የጠጁ ስካር ከናባል ባለፈ ጊዜ ሚስቱ ይህን ነገር ነገረችው፥ ልቡም በውስጡ ሞተ፥ 38እንደ ድንጋይም ሆነ፥ ከአሥር ቀንም በኋላ እግዚአብሔር ናባልን ቀሠፈው፥ እርሱም ሞተ።
39ዳዊትም ናባል እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ፦ ከናባል እጅ የስድቤን ፍርድ የፈረደልኝ፥ ባሪያውንም ከክፋት የጠበቀ እግዚአብሔር ይመስገን፥ እግዚአብሔርም የናባልን ክፋት በራሱ ላይ መለሰ አለ። ዳዊትም ልኮ ያገባት ዘንድ አቢግያን ተነጋገራት። 40የዳዊትም ባሪያዎች ወደ ቀርሜሎስ ወደ አቢግያ በመጡ ጊዜ፦ ዳዊት ያገባሽ ዘንድ ወደ አንቺ ልኮናል ብለው ነገሩአት። 41ተነሥታም በግምባርዋ ወድቃ እጅ ነሣችና፦ እነሆ፥ እኔ ገረድህ የጌታዬን ሎሌዎች እግር አጥብ ዘንድ አገልጋይ ነኝ አለች። 42አቢግያም ፈጥና ተነሣች፥ በአህያም ላይ ተቀመጠች፥ አምስቱም ገረዶችዋ ተከተሉአት፥ የዳዊትንም መልእክተኞች ተከትላ ሄደች፥ ሚስትም ሆነችው።
43-44ዳዊትም ደግሞ ኢይዝራኤላዊቱን አኪናሆምን ወሰደ፥ ሁለቱም ሚስቶች ሆኑለት። ሳኦል ግን የዳዊትን ሚስት ልጁን ሜልኮልን አገሩ ጋሊም ለነበረው ለሌሳ ልጅ ለፈልጢ ሰጥቶ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ