የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 25:23-44

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 25:23-44 አማ05

አቢጌልም ዳዊትን ባየችው ጊዜ በፍጥነት ከአህያዋ ወርዳ በዳዊት ጫማ አጠገብ መሬት ላይ ለጥ ብላ እጅ ነሣች፤ በጫማውም ላይ ወድቃ እንዲህ አለች፦ “ጌታዬ ሆይ! እባክህ የእኔን የአገልጋይህን ቃል አድምጠኝ! በደሉን እኔ ልሸከም፤ የናባልን ጉዳይ ከቁም ነገር አታግባው! እርሱ ልክ እንድ አስሙ አጠራር ሞኝ ነው! ጌታዬ፥ የአንተ አገልጋዮች በመጡ ጊዜ እኔ በዚያ አልነበርኩም፤ የበቀል እርምጃ በመውሰድ ጠላቶችህን እንዳትገድል የጠበቀህ ራሱ እግዚአብሔር ነው፤ እነሆ፥ እኔ አሁን በሕያው እግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ፤ ጠላቶችህና አንተን ለመጒዳት የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ናባል ቅጣታቸውን ይቀበሉ፤ ጌታዬ ሆይ! እባክህ ይህ እኔ አገልጋይህ ያመጣሁልህን ስጦታ ተቀብለህ ለአገልጋዮችህ ይሁን። ጌታዬ፥ አንተ የእግዚአብሔርን ጦርነት እየተዋጋህ ነው፤ በምትኖርበትም ዘመን ሁሉ ምንም ዐይነት ክፉ ነገር ማድረግን ስለማትፈልግ ስለ ፈጸምኩት በደል እባክህ ይቅር በለኝ፤ እግዚአብሔር አንተንና ዘሮችህን ለዘለዓለም ያነግሣል፤ ማንም ሰው በአንተ ላይ አደጋ ጥሎ ሊገድልህ ቢፈልግ አንድ ሰው ውድ የሆነ ሀብቱን እንደሚጠብቅ አምላክህ እግዚአብሔር አንተን በሰላም ይጠብቅሃል፤ ስለ ጠላቶችህም የሆነ እንደ ሆነ አንድ ሰው ድንጋዩን ከወንጭፍ እንደሚያስፈነጥር እግዚአብሔር ራሱ አሽቀንጥሮ ይጥላቸዋል። እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት፥ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ባደረገልህና በእስራኤልም ላይ በሚያነግሥህ ጊዜ፥ ምንም ዐይነት ጸጸት ወይም የኅሊና ወቀሳ አይደርስብህም። ጌታዬ ሆይ፥ ያለ ምክንያት ወይም የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ብለህ የገደልከው ሰው የለም፤ ስለዚህ ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር በሚባርክህ ጊዜ እኔንም አትርሳኝ።” ዳዊትም እንዲህ አላት፤ “ከእኔ ጋር እንድትገናኚ አንቺን ወደ እኔ የላከ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን! በዛሬው ቀን ደም ከማፍሰስና በቀልንም ከመበቀል የጠበቀኝ መልካም አስተሳሰብሽ የተባረከ ይሁን፤ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ። በአንቺ ላይ ጒዳት ከማድረስ እግዚአብሔር ጠብቆኛል፤ ፈጥነሽ ወደ እኔ ባትመጪ ኖሮ ግን፥ ከናባል ወንዶች አንድ እንኳ ሳላስተርፍ ከንጋት በፊት ሁሉንም ለመግደል በሕያው እግዚአብሔር ስም ምዬ ነበር።” ከዚያም በኋላ ዳዊት ያመጣችለትን ስጦታ ተቀብሎ “ወደ ቤትሽ በሰላም ተመልሰሽ ሂጂ፤ ልመናሽን ሰምቼአለሁ፤ የጠየቅሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” አላት። አቢጌልም እንደ ቤተ መንግሥት ግብር ታላቅ ግብዣ በማድረግ ላይ ወደነበረው ወደ ናባል ተመልሳ ሄደች፤ እርሱም ሰክሮ በደስታ ይፈነድቅ ስለ ነበር እስከ ማግስቱ ጧት ድረስ ምንም ቃል አልነገረችውም፤ በማግስቱም ስካሩ ከበረደለት በኋላ ሁሉንም ነገር አስረዳችው፤ ልቡም በድንጋጤ ስለ ተመታ እንደ ድንጋይ ሆነ። ከዐሥር ቀኖች በኋላም እግዚአብሔር ስለ ቀሠፈው ናባል ሞተ። ዳዊትም የናባልን መሞት በሰማ ጊዜ “እኔን በመስደቡ እግዚአብሔር ናባልን ስለ ተበቀለውና እኔንም ከስሕተት ስለ ጠበቀኝ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እርሱ ናባልን ስለ ክፉ ሥራው ቀጥቶታል” አለ። ከዚህም በኋላ ዳዊት ወደ አቢጌል መልእክተኛ ልኮ ሊያገባት መፈለጉን ገለጠላት። አገልጋዮቹም እርስዋ ወዳለችበት ወደ ቀርሜሎስ ሄደው “ሊያገባሽ ስለ ፈቀደ ወደ ዳዊት ልንወስድሽ መጥተናል” አሉአት። አቢጌልም ወደ መሬት ለጥ ብላ እጅ በመንሣት “እኔ ለእርሱ ገረዱ ነኝ፤ የአገልጋዮቹንም እግር ለማጠብ ዝግጁ ነኝ” አለች። ፈጥናም ተነሥታ በአህያዋ ላይ ተቀመጠች፤ በአምስት ገረዶችዋም ታጅባ ከዳዊት አገልጋዮች ጋር በመሄድ ሚስቱ ሆነች። ዳዊት ከዚህ በፊት የኢይዝራኤል ተወላጅ የሆነችውን አሒኖዓምን አግብቶ ነበር፤ አሁን ደግሞ አቢጌልን አገባ፤ ይህ በዚህ እንዳለ ሳኦል የዳዊት ሚስት የነበረችውን ልጁን ሜልኮልን የጋሊም ተወላጅ ለሆነው ለላዊሽ ልጅ ለፓልጢ ዳረለት።