የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 20:1-17

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 20:1-17 አማ54

ዳዊትም ከአርማቴም አገር ከነዋትዘራማ ሸሸ፥ ወደ ዮናታንም መጥቶ፦ ምን አደረግሁ? እኔንስ ለመግደል የሚፈልግ በአባትህ ፊት ጠማምነቴና ኃጢአቴ ምንድር ነው? ብሎ ተናገረው። ዮናታንም፦ ይህንስ ያርቀው፥ አትሞትም፥ እነሆ፥ አባቴ አስቀድሞ ለእኔ ሳይገልጥ ትልቅም ትንሽም ነገር ቢሆን አያደርግም፥ አባቴስ ይህን ነገር ለምን ይሰውረኛል? እንዲህ አይደለም አለው። ዳዊትም፦ እኔ በፊትህ ሞገስ እንዳገኘሁ አባትህ በእውነት ያውቃል፥ እርሱም፦ ዮናታን እንዳይከፋው አይወቅ ይላል፥ ነገር ግን ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! በእኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ያህል ቀርቶአል ብሎ ማለ። ዮናታንም ዳዊትን፦ ነፍስህ የወደደችውን ሁሉ አደርግልሃለሁ አለው። ዳዊትም ዮናታንን አለው፦ እነሆ፥ ነገ መባቻ ነው፥ በንጉሥም አጠገብ ለምሳ አልቀመጥም፥ እስከ ሦስተኛው ቀን ማታ ድረስ በውጭ በሜዳ እንድሸሸግ አሰናብተኝ። አባትህም ቢፈልገኝ፦ ለዘመዶቹ ሁሉ በዚያ በቤተልሔም የዓመት መሥዋዕት አላቸውና ዳዊት ወደ ከተማው ፈጥኖ ይሄድ ዘንድ አጽንቶ ለምኖኛል በለው። እርሱም፦ መልካም ነው ቢል ለእኔ ለባሪያህ ደኅንነት ይሆናል፥ ቢቆጣ ግን ክፋት ከእርሱ ዘንድ በእኔ ላይ እንደ ተቆረጠች እወቅ። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ከባሪያህ ጋር አድርገሃልና ለባሪያህ ቸርነት አድርግ፥ በደል ግን ቢገኝብኝ አንተ ግደለኝ፥ ለምን ወደ አባትህ ታደርሰኛለህ? ዮናታንም፦ ይህ ከአንተ ይራቅ፥ ከአባቴ ዘንድ ክፋት በላይህ እንደ ተቆረጠች ያወቅሁ እንደ ሆነ አልነግርህምን? አለው። ዳዊትም ዮናታንን፦ አባትህ ስለ እኔ ክፉ ነገር የነገረህ እንደ ሆን ማን ይነግረኛል? አለው። ዮናታንም ዳዊትን፦ ና ወደ ሜዳ እንውጣ አለው። ሁለቱም ወደ ሜዳ ወጡ። ዮናታንም ዳዊትን አለው፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁን፥ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በዚህ ጊዜ አባቴን መርምሬ፥ እነሆ፥ በዳዊት ላይ መልካም ቢያስብ ልኬ እገልጥልሃለሁ፥ አባቴም በአንተ ላይ ክፋት ማድረግ ቢወድድ እኔም ባላስታውቅህ በደህና ትሄድ ዘንድ ባላሰናብትህ፥ እግዚአብሔር በዮናታን ይህን ያድርግ ይህንም ይጨምር፥ እግዚአብሔርም ከአባቴ ጋር እንደ ነበረ ከአንተ ጋር ይሁን። እኔም እንዳልሞት በሕይወቴ ዘመን የእግዚአብሔርን ቸርነት አድርግልኝ፥ ደግሞም እግዚአብሔር የዳዊትን ጠላቶች ሁሉ እያንዳንዱ ከምድር ባጠፋቸው ጊዜ ለዘላለም ቸርነትህን ከቤቴ አታርቀው። ዮናታንም፦ እግዚአብሔር ከዳዊት ጠላቶች እጅ ይፈልገው ብሎ ከዳዊት ቤት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ዮናታንም ዳዊትን እንደ ነፍሱ ይወድድ ነበርና እንደ ገና ማለለት።