የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 20

20
1ዳዊትም ከአርማቴም አገር ከነዋትዘራማ ሸሸ፥ ወደ ዮናታንም መጥቶ፦ ምን አደረግሁ? እኔንስ ለመግደል የሚፈልግ በአባትህ ፊት ጠማምነቴና ኃጢአቴ ምንድር ነው? ብሎ ተናገረው። 2ዮናታንም፦ ይህንስ ያርቀው፥ አትሞትም፥ እነሆ፥ አባቴ አስቀድሞ ለእኔ ሳይገልጥ ትልቅም ትንሽም ነገር ቢሆን አያደርግም፥ አባቴስ ይህን ነገር ለምን ይሰውረኛል? እንዲህ አይደለም አለው። 3ዳዊትም፦ እኔ በፊትህ ሞገስ እንዳገኘሁ አባትህ በእውነት ያውቃል፥ እርሱም፦ ዮናታን እንዳይከፋው አይወቅ ይላል፥ ነገር ግን ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! በእኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ያህል ቀርቶአል ብሎ ማለ። 4ዮናታንም ዳዊትን፦ ነፍስህ የወደደችውን ሁሉ አደርግልሃለሁ አለው። 5ዳዊትም ዮናታንን አለው፦ እነሆ፥ ነገ መባቻ ነው፥ በንጉሥም አጠገብ ለምሳ አልቀመጥም፥ እስከ ሦስተኛው ቀን ማታ ድረስ በውጭ በሜዳ እንድሸሸግ አሰናብተኝ። 6አባትህም ቢፈልገኝ፦ ለዘመዶቹ ሁሉ በዚያ በቤተልሔም የዓመት መሥዋዕት አላቸውና ዳዊት ወደ ከተማው ፈጥኖ ይሄድ ዘንድ አጽንቶ ለምኖኛል በለው። 7እርሱም፦ መልካም ነው ቢል ለእኔ ለባሪያህ ደኅንነት ይሆናል፥ ቢቆጣ ግን ክፋት ከእርሱ ዘንድ በእኔ ላይ እንደ ተቆረጠች እወቅ። 8እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ከባሪያህ ጋር አድርገሃልና ለባሪያህ ቸርነት አድርግ፥ በደል ግን ቢገኝብኝ አንተ ግደለኝ፥ ለምን ወደ አባትህ ታደርሰኛለህ? 9ዮናታንም፦ ይህ ከአንተ ይራቅ፥ ከአባቴ ዘንድ ክፋት በላይህ እንደ ተቆረጠች ያወቅሁ እንደ ሆነ አልነግርህምን? አለው። 10ዳዊትም ዮናታንን፦ አባትህ ስለ እኔ ክፉ ነገር የነገረህ እንደ ሆን ማን ይነግረኛል? አለው። 11ዮናታንም ዳዊትን፦ ና ወደ ሜዳ እንውጣ አለው። ሁለቱም ወደ ሜዳ ወጡ።
12ዮናታንም ዳዊትን አለው፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁን፥ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በዚህ ጊዜ አባቴን መርምሬ፥ እነሆ፥ በዳዊት ላይ መልካም ቢያስብ ልኬ እገልጥልሃለሁ፥ 13አባቴም በአንተ ላይ ክፋት ማድረግ ቢወድድ እኔም ባላስታውቅህ በደህና ትሄድ ዘንድ ባላሰናብትህ፥ እግዚአብሔር በዮናታን ይህን ያድርግ ይህንም ይጨምር፥ እግዚአብሔርም ከአባቴ ጋር እንደ ነበረ ከአንተ ጋር ይሁን። 14እኔም እንዳልሞት በሕይወቴ ዘመን የእግዚአብሔርን ቸርነት አድርግልኝ፥ 15ደግሞም እግዚአብሔር የዳዊትን ጠላቶች ሁሉ እያንዳንዱ ከምድር ባጠፋቸው ጊዜ ለዘላለም ቸርነትህን ከቤቴ አታርቀው። 16ዮናታንም፦ እግዚአብሔር ከዳዊት ጠላቶች እጅ ይፈልገው ብሎ ከዳዊት ቤት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። 17ዮናታንም ዳዊትን እንደ ነፍሱ ይወድድ ነበርና እንደ ገና ማለለት።
18ዮናታንም አለው፦ ነገ መባቻ ነው፥ መቀመጫህም ባዶ ሆኖ ይገኛልና ትታሰባለህ። 19ሦስት ቀንም ያህል ቆይ፥ ከዚህም በኋላ ፈጥነህ ውረድ፥ ነገሩም በተደረገበት ቀን ወደ ተሸሸግህበት ስፍራ ሂድ፥ በኤዜል ድንጋይም አጠገብ ቆይ። 20እኔም በዓላማ ላይ እወረውራለሁ ብዬ ሦስት ፍላጻዎችን ወደ አጠገቡ እወረውራለሁ። 21እነሆም፦ ሂድ ፍላጻዎችን ፈልግ ብዬ ብላቴናውን እልከዋለሁ፥ ብላቴናውንም፦ እነሆ፥ ፍላጻው ከአንተ ወደዚህ ነው፥ ይዘኸው ወደ እኔ ና ያልሁት እንደ ሆነ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! ለአንተ ደኅንነት ነውና ምንም የለብህም። 22ብላቴናውን ግን፦ እነሆ፥ ፍላጻው ከአንተ ወዲያ ነው ያልሁት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔር አሰናብቶሃልና መንገድህን ሂድ። 23አንተና እኔም ስለ ተነጋገርነው፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለዘላለም በመካከላችን ምስክር ነው።
24ዳዊትም በሜዳው ተሸሸገ፥ መባቻም በሆነ ጊዜ ንጉሡ ግብር ለመብላት ተቀመጠ። 25ንጉሡም እንደ ቀድሞው በግንቡ አጠገብ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፥ ዮናታንም ቆሞ ነበር፥ አበኔርም በሳኦል አጠገብ ተቀመጠ፥ የዳዊትም ስፍራ ባዶውን ነበረ። 26ሳኦልም፦ አንድ ነገር ሆኖአል፥ ንጹሕም አይደለም፥ በእውነት ንጹሕ አይደለም ብሎ አስቦአልና በዚያን ቀን ምንም አልተናገረም። 27ከመባቻም በኋላ በማግሥቱ በሁለተኛው ቀን የዳዊት ስፍራ ባዶውን ነበረ፥ ሳኦልም ልጁን ዮናታንን፦ የእሴይ ልጅ ትናንትና ወይም ዛሬ ግብር ሊበላ ያልመጣ ስለ ምን ነው? አለው። 28ዮናታንም ለሳኦል፦ ዳዊት ወደ ቤተ ልሔም ይሄድ ዘንድ አጽንቶ ለመነኝ፥ 29እርሱም፦ ዘመዶቼ በከተማ ውስጥ መሥዋዕት አላቸውና፥ ወንድሜም ጠርቶኛልና እባክህ፥ አሰናብተኝ፥ አሁንም በዓይኖችህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ልሂድና ወንድሞቼን ልይ አለ፥ ስለዚህ ወደ ንጉሥ ሰደቃ አልመጣም ብሎ መለሰለት።
30የሳኦል ቁጣ በዮናታን ላይ ነደደና፦ አንተ የጠማማ ሴት ልጅ፥ የእሴይን ልጅ ለአንተ ማፈርያ ለእናትህም ኅፍረተ ሥጋ ማፈርያ እንደ መረጥህ እኔ አላውቅምን? 31የእሴይም ልጅ በምድር ላይ በሕይወት በሚኖርበት ዘመን ሁሉ አንተና መንግሥትህ አትጸኑም፥ አሁንም የሞት ልጅ ነውና ልከህ አስመጣልኝ አለው። 32ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል፦ ስለ ምን ይሞታል? ያደረገውስ ምንድር ነው? ብሎ መለሰለት። 33ሳኦልም ሊወጋው ጦሩን ወረወረበት፥ ዮናታንም አባቱ ዳዊትን ፈጽሞ ሊገድለው እንደ ፈቀደ አወቀ። 34አባቱ ዳዊትን ስላሳፈረው ዮናታን ስለ ዳዊት አዝኖአልና እጅግ ተቆጥቶ ከሰደቃው ተነሣ፥ በመባቻውም በሁለተኛ ቀን ግብር አልበላም።
35እንዲህም ሆነ፥ በነጋው ዮናታን ከዳዊት ጋር ወደ ተቃጠረበት ቦታ ወደ ሜዳ ወጣ፥ ከእርሱም ጋር ታናሽ ብላቴና ነበረ። 36ብላቴናውንም፦ ሮጠህ የምወረውራቸውን ፍላጻዎች ፈልግልኝ አለው። ብላቴናውም በሮጠ ጊዜ ፍላጻውን ወደ ማዶ ወረወረው። 37ብላቴናውም ዮናታን ፍላጻውን ወደ ወረወረበት ስፍራ በመጣ ጊዜ ዮናታን፦ ፍላጻው ከአንተ ወዲያ ነው ብሎ ወደ ብላቴናው ጮኸ። 38ዮናታንም ደግሞ፦ ቶሎ ፍጠን፥ አትቆይ ብሎ ወደ ብላቴናው ጮኸ፥ የዮናታንም ብላቴና ፍላጻዎቹን ሰብስቦ ወደ ጌታው መጣ። 39ዮናታንና ዳዊት ብቻ ነገሩን ያውቁ ነበር እንጂ ብላቴናው ምንም አያውቅም ነበር። 40ዮናታንም መሣርያውን ለብላቴናው ሰጥቶ፦ ወደ ከተማ ውሰድ አለው። 41ብላቴናውም በሄደ ጊዜ ዳዊት ከስፍራው በደቡብ አጠገብ ተነሣ፥ በምድርም ላይ በግምባሩ ተደፋ፥ ሦስት ጊዜም ለሰላምታ ሰገደ፥ እየተላቀሱም እርስ በእርሳቸው ተሳሳሙ፥ ይልቁንም ዳዊት እጅግ አለቀስ። 42ዮናታንም ዳዊትን፦ በደኅና ሂድ፥ እነሆ፥ እኛ ሁለታችን በእኔና በአንተ፥ በዘሬና በዘርህ መካከል ለዘላለም እግዚአብሔር ይሁን ብለን በእግዚአብሔር ስም ተማምለናል አለው። ዳዊትም ተነሥቶ ሄደ፥ ዮናታንም ወደ ከተማ ገባ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ