የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 20:1-17

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 20:1-17 አማ05

ከዚህ በኋላ ዳዊት በራማ ከምትገኘው ከናዮት በመሸሽ ወደ ዮናታን ሄዶ “ከቶ ምን አደረግሁ? ምንስ ወንጀል ፈጸምኩ? አባትህ ለመግደል የሚፈልገኝስ ምን በድየው ነው?” ሲል ጠየቀው። ዮናታንም “ይህንንስ ከአንተ ያርቀው! አትሞትም፤ ትልቅም ሆነ ትንሽ አባቴ ከእኔ የሚሰውረው ነገር የለም፤ ይህንንም ነገር ቢሆን አባቴ ከእኔ አይሰውርም በፍጹም አይደረግም!” አለው። ዳዊት ግን “አባትህ አንተ እኔን ምን ያኽል እንደምትወደኝ በደንብ ያውቃል፤ ስለዚህም ዕቅዱን አንተ እንድታውቅበት ላለማድረግ ወስኖአል፤ ይህንንም የሚያደርገው አንተ ይህን ብታውቅ በብርቱ እንደምታዝን ስለሚያውቅ ነው፤ በሕያው እግዚአብሔር ስምና በነፍስህ እምላለሁ፤ ከአሁን ወዲያ ወደ ሞት ለመድረስ የቀረችን አንዲት ዕርምጃ ብቻ ናት!” አለው። ዮናታንም “አንተ የምትፈልገውን ሁሉ አደርግልሃለሁ” አለው። ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ነገ አዲስ ጨረቃ የምትታይበት በዓል ነው፤ እኔም ከንጉሡ ጋር መብላት ይኖርብኛል፤ እስከ ነገ ወዲያ ምሽት ድረስ እንድደበቅ ፍቀድልኝ” አለው። “ምናልባት አባትህ ቢፈልገኝ በቤተሰቡ ዓመታዊ በዓል የሚከበር ስለ ሆነ ወደ ቤተልሔም እንዲሄድ እፈቅድለት ዘንድ ዳዊት እኔን አጥብቆ ለምኖኛል ብለህ ንገረው። ንጉሡም ‘እሺ’ ቢል፥ እኔ አገልጋይህ በሰላም እንደምኖር ዐውቃለሁ፤ ንጉሡ ከተቈጣ ግን ጒዳት ሊያደርስብኝ የወሰነ መሆኑን ታውቃለህ፤ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስለ ተማመንን የሰጠኸኝን የተቀደሰ ተስፋ በመጠበቅ እባክህ ለእኔ ለአገልጋይህ መልካም ነገር አድርግልኝ፤ ወንጀለኛ ሆኜ ከተገኘሁ ግን አንተው ራስህ ግደለኝ እንጂ እንዲገድለኝ ወደ አባትህ ለምን ትወስደኛለህ?” ዮናታን ግን “እንዲህ ያለውን ነገር ፈጽሞ አታስብ! በአንተ ክፉ ነገር አስቦ ቢሆን ኖሮ፥ እነግርህ አልነበረም?” አለው። ዳዊትም “ታዲያ አባትህ ስለ እኔ ክፉ ቃል ቢናገር ማን ያስረዳኛል?” ሲል ጠየቀ። ዮናታንም “ና! ወደ ሜዳ እንሂድ!” ሲል መለሰለት፤ ሁለቱም ወደ ሜዳ ወጡ። ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ነገ በዚህ ሰዓት ወይም በሦስተኛው ቀን ስለ አንተ መልካም አስተሳሰብ ያለው መሆኑን አባቴን ጠይቄ ከተረዳሁ በኋላ ስለዚሁ ጉዳይ የሚገልጥልህ መልእክተኛ እልክብሃለሁ፤ ለዚህም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁን! አንተን ለመጒዳት የሚፈልግ ከሆነ ግን፥ ስለ እርሱ ባልገልጥልህና አንተም በሰላም እንድታመልጥ ባላደርግ አባቴ በአንተ ላይ ሊያደርግ ያሰበውን ክፉ ነገር እግዚአብሔር በእኔ ላይ ያድርሰው። እግዚአብሔር ከአባቴ ጋር እንደ ነበር ከአንተም ጋር ይሁን፤ በሕይወት ብኖር እግዚአብሔር የሚወድደውን ታማኝ ፍቅር አሳየኝ፤ ብሞት ግን እግዚአብሔር የአንተን የዳዊትን ጠላቶች ሁሉ ከገጸ ምድር በሚያጠፋበት ጊዜ ታማኝ የሆነውን ፍቅርህን ከቤተሰቤም አታቋርጥ፥ ይህ የገባነው ቃል ኪዳን ለዘለቄታው እንደ ተጠበቀ ይኑር፤ ይህን ቃል ኪዳን ብታፈርስ ግን እግዚአብሔር ይፈርድብሃል።” ዮናታን ዳዊትን እንደ ራሱ አድርጎ ይወደው ስለ ነበር “በእርግጥ እንደምትወደኝ ለመግለጥ እንደገና ማልልኝ” አለው።