የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 18:1-16

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 18:1-16 አማ54

ዳዊትም ለሳኦል መናገሩን በፈጸመ ጊዜ የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሰረች፥ ዮናታንም እንደ ነፍሱ ወደደው። በዚያም ቀን ሳኦል ወሰደው፥ ወደ አባቱም ቤት ይመልሰው ዘንድ አልተወውም። ዮናታንም እንደ ነፍሱ ስለ ወደደው ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ዮናታንም የለበሰውን ካባ አውልቆ እርሱንና ልብሱን ሰይፉንም ቀስቱንም መታጠቂያውንም ለዳዊት ሸለመው። ዳዊትም ሳኦል ወደ ሰደደው ሁሉ ይሄድ ነበር፥ አስተውሎም ያደርግ ነበር፥ ሳኦልም በጦረኞች ላይ ሾመው፥ ይህም በሕዝብ ሁሉ ዓይንና በሳኦል ባሪያዎች ዓይን መልካም ነበረ። እንዲህም ሆነ፥ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ፥ እየዘመሩና እየዘፈኑ እልልም እያሉ ከበሮና አታሞ ይዘው ንጉሡን ሳኦልን ሊቀበሉ ሴቶች ከእስራኤል ከተሞች ሁሉ ወጡ። ሴቶችም፦ ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም እልፍ ገደለ እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር። ሳኦልም እጅግ ተቆጣ፥ ይህም ነገር አስከፋው፥ እርሱም፦ ለዳዊት እልፍ ሰጡት፥ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ ሰጡኝ፥ ከመንግሥት በቀር ምን ቀረበት? አለ። ከዚያም ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ተመቅኝቶ ተመለከተው። በነጋውም ሳኦልን ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው፥ በቤቱም ውስጥ ትንቢት ተናገረ። ዳዊትም በየቀኑ ያደርግ እንደ ነበረ በእጁ በገና ይመታ ነበር። ሳኦልም ጦሩን በእጁ ይዞ ነበር። ሳኦልም፦ ዳዊትን ከግንቡ ጋር አጣብቄ እመታዋለሁ ብሎ ጦሩን ወረወረ። ዳዊትም ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ። እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ ከሳኦልም ስለ ተለየ ሳኦል ዳዊትን ፈራው። ስለዚህም ሳኦል ከእርሱ አራቀው፥ የሺህ አለቃም አደረገው፥ በሕዝቡም ፊት ይወጣና ይገባ ነበር። ዳዊትም በአካሄዱ ሁሉ አስተውሎ ያደርግ ነበር፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ። ሳኦልም እጅግ ብልህ እንደ ሆነ አይቶ እጅግ ፈራው። ነገር ግን በፊታቸው ይወጣና ይገባ ስለ ነበረ እስራኤልና ይሁዳ ሁሉ ዳዊትን ወደዱ።