ዳዊት ከሳኦል ጋራ የሚያደርገውን ንግግር እንዳበቃ፤ የዮናታን ነፍስ ከዳዊት ነፍስ ጋራ ተቈራኘች፤ እንደ ራሱም አድርጎ ወደደው። ከዚያች ዕለት አንሥቶ ሳኦል ዳዊትን ዐብሮት እንዲኖር አደረገ፤ ወደ አባቱም ቤት እንዲመለስ አላሰናበተውም። ዮናታን እንደ ራሱ አድርጎ ስለ ወደደው፣ ከዳዊት ጋራ ኪዳን አደረገ፤ ዮናታን የለበሰውን ካባ አውልቆ ከነጦር ልብሱ፣ በተጨማሪም ሰይፉን፣ ቀስቱንና መታጠቂያውን ሰጠው። ሳኦል በሚልከው በማናቸውም ስፍራ፣ ዳዊት ተልእኮውን በሚገባ ይፈጽም ስለ ነበር፣ በሰራዊቱ ላይ ሾመው፤ ይህም ሕዝቡን በሙሉ፣ የሳኦልንም የጦር ሹማምት ደስ አሠኘ። ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ከገደለ በኋላ፣ ሰዎቹ ወደ የቤታቸው በሚመለሱበት ጊዜ፣ ሴቶች ከበሮና መሰንቆ ይዘው እየዘፈኑ፣ እየጨፈሩና እልል እያሉ ንጉሥ ሳኦልን ለመቀበል ከእስራኤል ከተሞች ሁሉ ወጡ። ሴቶቹም እንዲህ ሲሉ በመቀባበል ዘፈኑ፤ “ሳኦል ሺሕ ገደለ፤ ዳዊት ግን ዐሥር ሺሕ ገደለ።” ሳኦል እጅግ ተቈጣ፤ ይህም ነገር አላስደሰተውም። እርሱም፣ “ለዳዊት ዐሥር ሺሕ አሉለት፤ ለእኔ ግን ሺሕ ብቻ! እንግዲህ መንግሥት እንጂ ሌላ ምን ቀረው” አለ። ከዚያች ዕለት አንሥቶ ሳኦል ዳዊትን በቅናት ዐይን ይመለከተው ጀመር። በማግስቱም ከእግዚአብሔር የታዘዘ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በኀይል መጣበት፣ በዚህ ጊዜ ዳዊት ወትሮ እንደሚያደርገው ሁሉ በገና ሲደረድር፣ ሳኦል በቤቱ ሆኖ ትንቢት ይናገር ነበር። ሳኦል በእጁ ጦር ይዞ ነበር፤ እርሱም፣ “ዳዊትን ከግድግዳው ጋራ አጣብቀዋለሁ” ብሎ በማሰብ ጦሩን ወረወረበት፤ ዳዊት ግን ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ። እግዚአብሔር ከርሱ ተለይቶ ከዳዊት ጋራ ስለ ሆነ፣ ሳኦል ዳዊትን ፈራው። ስለዚህ ዳዊትን ከአጠገቡ በማራቅ የሺሕ አለቃ አደረገው። ዳዊትም ሰራዊቱን እየመራ በፊታቸው ይወጣና ይገባ ነበር። እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ ስለ ነበር የሚያደርገው ነገር ሁሉ ይሳካለት ነበር። ሳኦልም፣ ዳዊት እንደ ተሳካለት ባየ ጊዜ ፈራው፤ መላው እስራኤልና ይሁዳ ግን ዳዊትን ወደዱት፤ በፊታቸው እየወጣና እየገባ የሚመራቸው እርሱ ነበርና።
1 ሳሙኤል 18 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ሳሙኤል 18
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ሳሙኤል 18:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos