የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 18

18
1ዳዊትም ለሳኦል መናገሩን በፈጸመ ጊዜ የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሰረች፥ ዮናታንም እንደ ነፍሱ ወደደው። 2በዚያም ቀን ሳኦል ወሰደው፥ ወደ አባቱም ቤት ይመልሰው ዘንድ አልተወውም። 3ዮናታንም እንደ ነፍሱ ስለ ወደደው ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። 4ዮናታንም የለበሰውን ካባ አውልቆ እርሱንና ልብሱን ሰይፉንም ቀስቱንም መታጠቂያውንም ለዳዊት ሸለመው። 5ዳዊትም ሳኦል ወደ ሰደደው ሁሉ ይሄድ ነበር፥ አስተውሎም ያደርግ ነበር፥ ሳኦልም በጦረኞች ላይ ሾመው፥ ይህም በሕዝብ ሁሉ ዓይንና በሳኦል ባሪያዎች ዓይን መልካም ነበረ።
6እንዲህም ሆነ፥ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ፥ እየዘመሩና እየዘፈኑ እልልም እያሉ ከበሮና አታሞ ይዘው ንጉሡን ሳኦልን ሊቀበሉ ሴቶች ከእስራኤል ከተሞች ሁሉ ወጡ። 7ሴቶችም፦ ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም እልፍ ገደለ እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር። 8ሳኦልም እጅግ ተቆጣ፥ ይህም ነገር አስከፋው፥ እርሱም፦ ለዳዊት እልፍ ሰጡት፥ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ ሰጡኝ፥ ከመንግሥት በቀር ምን ቀረበት? አለ። 9ከዚያም ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ተመቅኝቶ ተመለከተው።
10በነጋውም ሳኦልን ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው፥ በቤቱም ውስጥ ትንቢት ተናገረ። ዳዊትም በየቀኑ ያደርግ እንደ ነበረ በእጁ በገና ይመታ ነበር። ሳኦልም ጦሩን በእጁ ይዞ ነበር። 11ሳኦልም፦ ዳዊትን ከግንቡ ጋር አጣብቄ እመታዋለሁ ብሎ ጦሩን ወረወረ። ዳዊትም ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ። 12እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ ከሳኦልም ስለ ተለየ ሳኦል ዳዊትን ፈራው። 13ስለዚህም ሳኦል ከእርሱ አራቀው፥ የሺህ አለቃም አደረገው፥ በሕዝቡም ፊት ይወጣና ይገባ ነበር። 14ዳዊትም በአካሄዱ ሁሉ አስተውሎ ያደርግ ነበር፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ። 15ሳኦልም እጅግ ብልህ እንደ ሆነ አይቶ እጅግ ፈራው። 16ነገር ግን በፊታቸው ይወጣና ይገባ ስለ ነበረ እስራኤልና ይሁዳ ሁሉ ዳዊትን ወደዱ።
17ሳኦልም ዳዊትን፦ ታላቂቱ ልጄ ሜሮብ እነኋት፥ እርስዋን እድርልሃለሁ፥ ብቻ ቀልጣፋ ልጅ ሁንልኝ፥ ስለ እግዚአብሔርም ጦርነት ተጋደል አለው። ሳኦልም፦ የፍልስጥኤማውያን እጅ በእርሱ ላይ ትሁን እንጂ የእኔ እጅ በእርሱ ላይ አትሁን ይል ነበር። 18ዳዊትም ሳኦልን፦ ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ሰውነቴስ ምንድር ናት? የአባቴስ ወገን በእስራኤል ዘንድ ምንድር ነው? አለው። 19ነገር ግን የሳኦል ልጅ ሜሮብ ዳዊትን የምታገባበት ጊዜ ሲደርስ ለመሓላታዊው ለኤስድሪኤል ተዳረች። 20የሳኦልም ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደች፥ ይህም ወሬ ለሳኦል ደረሰለት፥ ነገሩም ደስ አሰኘው። 21ሳኦልም፦ ወጥመድ ትሆነው ዘንድ፥ የፍልስጥኤማውያንም እጅ በእርሱ ላይ ትሆን ዘንድ እርስዋን እድርለታለሁ አለ፥ ሳኦልም ዳዊትን፦ ዛሬ ሁለተኛ አማች ትሆነኛለህ አለው።
22ሳኦልም ባሪያዎቹን፦ እነሆ ንጉሥ እጅግ ወድዶሃል፥ ባሪያዎቹም ሁሉ ወድደውሃል፥ አሁንም ለንጉሥ አማች ሁን ብላችሁ በስውር ለዳዊት ንገሩት ብሎ አዘዛቸው። 23የሳኦልም ባሪያዎች ይህን ቃል በዳዊት ጆሮ ተናገሩ፥ ዳዊትም፦ እኔ ድሀ የተጠቃሁም ሰው ስሆን ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ ለእናንተ ትንሽ ነገር ይመስላችኋልን? አለ። 24የሳኦልም ባሪያዎች፦ ዳዊት እንዲህ ብሎ ተናገረ ብለው ነገሩት። 25ሳኦልም ዳዊትን በፍልስጥኤማውያን እጅ ይጥለው ዘንድ አስቦ፦ የንጉሥን ጠላቶች ይበቀል ዘንድ ከመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት በቀር ንጉሥ ማጫ አይሻም ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት አላቸው። 26የሳኦልም ባሪያዎች ይህን ቃል ለዳዊት ነገሩት፥ ለንጉሥም አማች ይሆን ዘንድ ዳዊትን ደስ አሰኘው። 27ዳዊትና ሰዎቹም ተነሥተው ሄዱ፥ ከፍልስጥኤማውያንም መቶ ሰዎች ገደሉ፥ ዳዊትም ለንጉሥ አማች ይሆን ዘንድ ሰለባቸውን አምጥቶ በቁጥራቸው ልክ ለንጉሡ ሰጠ። ሳኦልም ልጁን ሜልኮልን ዳረለት። 28ሳኦልም እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንደ ሆነ አየ፥ እስራኤልም ሁሉ ወደዱት። 29ሳኦልም ዳዊትን አጥብቆ ፈራው፥ ሳኦልም ዕድሜውን ሁሉ ለዳዊት ጠላት ሆነ።
30የፍልስጥኤማውያንም አለቆች ይወጡ ነበር፥ በወጡም ጊዜ ሁሉ ከሳኦል ባሪያዎች ሁሉ ይልቅ ዳዊት አስተውሎ ያደርግ ነበርና ስሙ እጅግ ተጠርቶ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ