አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 3
3
ንጉሥ ሰሎሞን ጥበብን ይሰጠው ዘንድ እግዚአብሔርን መለመኑ
(2ዜ.መ. 1፥3-12)
1ሰሎሞንም ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን አማች ሆነ፤ የፈርዖንን ልጅ አገባ፤ ቤቱንና የእግዚአብሔርንም ቤት በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ያለውን ቅጥር ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ ወደ ዳዊት ከተማ አመጣት። 2እስከዚያም ቀን ድረስ ለእግዚአብሔር ስም መቅደስ አልተሠራም ነበርና ሕዝቡ በኮረብታ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋ ነበር። 3ሰሎሞንም እግዚአብሔርን ይወድድ ነበር፤ በአባቱም በዳዊት ሥርዐት ይሄድ ነበር፤ ብቻ በኮረብታ መስገጃ ይሠዋና ያጥን ነበር።
4ገባዖን ዋና የኮረብታ መስገጃ ነበረችና ንጉሡ ይሠዋ ዘንድ ወደዚያ ሄደ፤ ሰሎሞንም በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። 5እግዚአብሔርም በገባዖን ለሰሎሞን በሌሊት በሕልም ተገለጠለት፤ እግዚአብሔርም “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ለምን፤” አለ። 6ሰሎሞንም አለ “እርሱ በፊትህ በእውነትና በጽድቅ በልብም ቅንነት ከአንተ ጋር እንደ ሄደ፥ ከባሪያህ ከአባቴ ከዳዊት ጋር ታላቅ ቸርነት አድርገሃል፤ ዛሬ እንደ ሆነም በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ሰጥተህ ታላቁን ቸርነትህን አቆይተህለታል። 7አሁንም፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ! እኔን ባሪያህን በአባቴ በዳዊት ፋንታ አንግሠኸኛል፤ እኔም መውጫውንና መግቢያን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝ። 8ባሪያህም ያለው አንተ በመረጥኸው ሕዝብህ ስለ ብዛቱም ይቈጠርና ይመጠን ዘንድ በማይቻል በታላቅ ሕዝብ መካከል ነው። 9ስለዚህም በሕዝብህ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ፥ መልካሙንና ክፉውንም ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡና ስጠው፤ አለዚያማ በዚህ በታላቅ ሕዝብህ ላይ ይፈርድ ዘንድ ማን ይችላል?”
10ሰሎሞንም ይህን ነገር ስለ ለመነ፤ ነገሩ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው። 11እግዚአብሔርም አለው “ፍርድን ትለይ ዘንድ ለራስህ ማስተዋልን ለመንህ እንጂ ለራስህ ብዙ ዘመናትን ባለጠግነትንም የጠላቶችህንም ነፍስ ሳትለምን ይህን ነገር ለምነሃልና እነሆ፥ 12እኔ እንደ ቃል አድርጌልሃለሁ፤ እነሆ፥ ማንም የሚመስልህ ከአንተ በፊት እንደሌለ ከአንተም በኋላ እንዳይነሣ አድርጌ ጥበበኛና አስተዋይ ልቡና ሰጥቼሃለሁ። 13ደግሞም ከነገሥታት የሚመስልህ ማንም እንዳይኖር ያልለመንኸውን ባለጠግነትና ክብር ሰጥቼሃለሁ። 14አባትህም ዳዊት እንደ ሄደ፥ ሥርዐቴንና ትእዛዜን ትጠብቅ ዘንድ በመንገዴ የሄድህ እንደ ሆነ፥ ዕድሜህን አረዝመዋለሁ።” 15ሰሎሞንም ነቃ፤ እነሆም፥ ሕልም ነበረ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጥቶ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቆመ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አሳረገ፤ የደኅንነትንም መሥዋዕት አቀረበ፤ ለባሪያዎቹም ሁሉ ግብዣ አደረገ።
ጥበብ የሞላበት የሰሎሞን ፍርድ
16በዚያን ጊዜም ሁለት ጋለሞቶች ሴቶች ወደ ንጉሡ መጥተው በፊቱ ቆሙ። 17አንደኛይቱም ሴት አለች “ጌታዬ ሆይ! እኔና ይህች ሴት በአንድ ቤት እንኖራለን፤ እኔም ከእርስዋ ጋር በቤት ሳለሁ ወለድሁ። 18እኔ ከወለድሁ ከሦስት ቀን በኋላ ይህች ሴት ደግሞ ወለደች፤ እኛ በቤት ውስጥ አብረን ነበርን፤ ከሁለታችንም በቀር ማንም በቤት ውስጥ አልነበረም። 19እርስዋም በላዩ ስለ ተኛችበት የዚህች ሴት ልጅ በሌሊት ሞተ። 20እርስዋም በእኩለ ሌሊት ተነሥታ፥ እኔ ባሪያህ ተኝቼ ሳለሁ፥ ልጄን ከአጠገቤ ወሰደች፤ በብብትዋም አደረገችው፤ የሞተውንም ልጅዋን በእኔ ብብት አደረገች። 21ልጄንም አጠባ ዘንድ በማለዳ ብነሣ፥ እነሆ፥ ሞቶ ነበር፤ ነገር ግን ብርሃን በሆነ ጊዜ ተመለከትሁት፤ እነሆም፥ የወለድሁት ልጄ አልነበረም።” 22ሁለተኛይቱም ሴት “ደኅነኛው የኔ ልጅ ነው፤ የሞተውም የአንቺ ልጅ ነው እንጂ አንቺ እንደምትዪው አይደለም፤” አለች። ይህችም “የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፤ ደኅነኛውም የእኔ ልጅ ነው፤” አለች፤ እንዲሁም በንጉሡ ፊት ይነጋገሩ ነበር።
23በዚያን ጊዜም ንጉሡ “ይህች ‘ደኅነኛው የእኔ ልጅ ነው፤ የሞተውም የአንቺ ልጅ ነው፤’ ትላለች፤ ያችኛይቱም ‘አይደለም፤ የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፤ ደኅነኛውም የእኔ ልጅ ነው፤’ ትላለች፤” አለ። 24ንጉሡም “ሰይፍ አምጡልኝ፤” አለ፤ ሰይፍም ይዘው ወደ ንጉሡ ፊት መጡ። 25ንጉሡም “ደኅነኛውን ሕፃን ለሁለት ከፍላችሁ ለአንዲቱ አንዱን ክፍል፥ ለሁለተኛይቱም ሁለተኛውን ክፍል ስጡ፤” አለ። 26ደኅነኛውም የነበራት ሴት አንጀትዋ ስለ ልጅዋ ናፍቆአልና “ጌታዬ ሆይ! ደኀነኛውን ለእርስዋ ስጣት እንጂ አትግደል፤” ብላ ለንጉሡ ተናገረች። ያችኛይቱ ግን “ይከፈል እንጂ ለእኔም ለአንቺም አይሁን፤” አለች። 27ንጉሡም መልሶ “ይህችኛይቱ እናቱ ናትና ደኅነኛውን ሕፃን ለእርስዋ ስጡአት እንጂ አትግደሉት፤” አለ። 28ንጉሡም የፈረደውን ፍርድ እስራኤል ሁሉ ሰሙ፤ ፍርድን ለማድረግ የእግዚአብሔር ጥበብ እንደ ነበረበት አይተዋልና ንጉሡን ፈሩ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 3: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ