አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 2

2
ዳዊት ለሰሎሞን የሰጠው የመጨረሻ ምክር
1ዳዊትም የሚሞትበት ቀን ቀረበ፤ ልጁንም ሰሎሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ 2“እኔ የምድሩን ሁሉ መንገድ እሄዳለሁ፤ 3በርታ፤ ሰውም ሁን፤ የምታደርገውንና የምትሄድበትን ሁሉ ታከናውን ዘንድ፥ በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ ሥርዐቱንና ትእዛዛቱን ፍርዱንና ምስክሩንም ትጠብቅ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ፥ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ። 4ይኸውም ደግሞ እግዚአብሔር ስለ እኔ ‘ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በፊቴም በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው በእውነት ቢሄዱ ከእስራኤል ዙፋን ሰው አይቆረጥብህም፤’ ብሎ የተናገረውን ቃል ያጸና ዘንድ ነው። 5አንተም ደግሞ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ! ሁለቱን የእስራኤልን ጭፍራ አለቆች የኔር ልጅ አበኔርን የዬቴሩንም ልጅ አሜሳይን ገድሎ፥ በእኔ ላይ ያደረገውን ታውቃለህ፤ የሰልፉንም ደም በሰላም አፈሰሰ፤ በወገቡም ባለው ድግና በእግሩ ባለው ጫማ ንጹሕ ደም አኖረ። 6አንተም እንደ ጥበብህ አድርግ፤ ሽበቱንም በሰላም ወደ መቃብር አታውርደው። 7ከወንድምህ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸሁ ጊዜ ቀርበውኛልና ለገለዓዳዊው ለቤርዜሊ ልጆች መልካም ቸርነት አድርግላቸው፤ በማዕድህም ከሚበሉት መካከል ይሁኑ። 8እኔም ወደ መሃናይም በሄድሁ ጊዜ ብርቱ እርግማን የረገመኝ የብራቂም አገር ሰው የብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ፥ እነሆ፥ በአንተ ዘንድ ነው፤ እርሱ ግን ዮርዳኖስን በተሻገርሁ ጊዜ ሊቀበለኝ ወረደ፤ እኔም ‘በሰይፍ አልገድልህም፤’ ብዬ በእግዚአብሔር ምዬለታለሁ። 9አንተ ግን ጥበበኛ ሰው ነህና ያለ ቅጣት አትተወው፤ የምታደርግበትንም አንተ ታውቃለህ፤ ሽበቱንም ከደም ጋር ወደ መቃብር አውርድ።”
የዳዊት መሞት
10ዳዊትም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ። 11ዳዊትም በእስራኤል ላይ የነገሠው ዘመን አርባ ዓመት ነበረ። በኬብሮን ሰባት ዓመት ነገሠ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላላ ሦስት ዓመት ነገሠ። 12ሰሎሞንም በአባቱ በዳዊት ዙፋን ተቀመጠ፤ መንግሥቱም እጅግ ጸና።
የአዶንያስ መሞት
13የአጊት ልጅ አዶንያስም ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ መጣ፤ እርስዋም “ወደ እኔ መምጣትህ በሰላም ነውን?” አለች፤ 14እርሱም “በሰላም ነው፤” አለ። ደግሞም “ከአንቺ ጋር ጉዳይ አለኝ፤” አለ፤ እርስዋም “ተናገር፤” አለች። 15እርሱም “መንግሥቱ ለእኔ እንደ ነበረ፥ እስራኤልም ሁሉ ንጉሥ እሆን ዘንድ ፊታቸውን ወደ እኔ አድርገው እንደ ነበረ አንቺ ታውቂያለሽ፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆኖለታልና መንግሥቱ ከእኔ አልፎ ለወንድሜ ሆኖአል። 16አሁንም አንዲት ልመና እለምንሻለሁ፤ አታሳፍሪኝ፤” አለ። እርስዋም “ተናገር፤” አለችው። 17እርሱም “አያሳፍርሽምና ሱነማይቱን አቢሳን ይድርልኝ ዘንድ ለንጉሡ ለሰሎሞን እንድትነግሪው እለምንሻለሁ፤” አለ። 18ቤርሳቤህም “መልካም ነው፤ ስለ አንተ ለንጉሡ እነግረዋለሁ፤” አለች።
19ቤርሳቤህም የአዶንያስን ነገር ትነግረው ዘንድ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ገባች፤ ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ፤ ሳማትም፤ በዙፋኑም ተቀመጠ፤ ለንጉሡም እናት ወንበር አስመጣላት፤ በቀኙም ተቀመጠች። 20እርስዋም “አንዲት ታናሽ ልመና እለምንሃለሁ፤ አታሳፍረኝ፤” አለች። ንጉሡም “እናቴ ሆይ! አላሳፍርሽምና ለምኝ፤” አላት። 21እርስዋም “ሱነማይቱ አቢሳ ለወንድምህ ለአዶንያስ ትዳርለት፤” አለች። 22ንጉሡም ሰሎሞን ለእናቱ መልሶ “ሱነማይቱን አቢሳን ለአዶንያስ ለምን ትለምኝለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ ነውና መንግሥትን ደግሞ ለምኚለት፤ ካህኑም አብያታርና የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ ደግሞ ከእርሱ ጋር ናቸው፤” አላት። 23ንጉሡም ሰሎሞን “አዶንያስ ይህን ቃል በሕይወቱ ላይ አለመናገሩ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ ይህንም ይጨምርብኝ። 24አሁንም ያጸናኝ፥ በአባቴም በዳዊት ዙፋን ላይ ያስቀመጠኝ፥ እንደ ተናገረውም ቤትን የሠራልኝ ሕያው እግዚአብሔርን! ዛሬ አዶንያስ ፈጽሞ ይገደላል፤” ብሎ በእግዚአብሔር ማለ። 25ንጉሡም ሰሎሞን የዮዳሄን ልጅ በናያስን ላከ፤ እርሱም ወደቀበት፤ ሞተም።
የአብያታር መሳደድና የኢዮአብ በሞት መቀጣት
26ንጉሡም ካህኑን አብያታርን “አንተ ዛሬ የሞት ሰው ነበርህ፤ ነገር ግን የአምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ስለ ተሸከምህ፥ አባቴም የተቀበለውን መከራ ሁሉ አንተ ስለ ተቀበልህ አልገድልህምና በዓናቶት ወዳለው ወደ እርሻህ ሂድ፤” አለው። 27በሴሎም በዔሊ ቤት ላይ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ ሰሎሞን አብያታርን ከእግዚአብሔር ክህነት አወጣው።
28ለኢዮአብም ወሬ ደረሰለት፤ ኢዮአብም አቤሴሎምን አልተከተለም ነበር ነገር ግን አዶንያስን ተከትሎ ነበር። ኢዮአብም ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ የመሠዊያውን ቀንድ ያዘ። 29ንጉሡም ሰሎሞን ኢዮአብ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ መሠዊያውን እንደ ያዘ ሰማ፤ ሰሎሞንም የዮዳሄን ልጅ በናያስን “ሂድ፤ ውደቅበት፤” ብሎ አዘዘው። 30በናያስም ወደ እግዚአብሔር ድንኳን መጥቶ “ንጉሡ ‘ውጣ’ ይልሃል፤” አለው፤ እርሱም “በዚህ እሞታለሁ እንጂ አልወጣም፤” አለ። በናያስም “ኢዮአብ የተናገረው ቃል የመለሰልኝም እንዲህ ነው፤” ብሎ ወደ ንጉሡ ወሬ አመጣ። 31ንጉሡም አለው “እንደ ነገረህ አድርግ፤ ኢዮአብም በከንቱ ያፈሰሰውን ደም ከእኔና ከአባቴ ቤት ታርቅ ዘንድ ገድለህ ቅበረው። 32አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ከእርሱ የሚሻሉትን ሁለቱን ጻድቃን ሰዎች፥ የእስራኤልን ሠራዊት አለቃ የኔርን ልጅ አበኔርን፥ የይሁዳንም ሠራዊት አለቃ የዬቴርን ልጅ አሜሳይን፥ በሰይፍ ገድሎአልና እግዚአብሔር ደሙን በራሱ ላይ ይመልሰው። 33ደማቸውም በኢዮአብ ራስና በዘሩ ራስ ላይ ለዘላለም ይመለስ፤ ለዳዊት ግን ለዘሩና ለቤቱ ለዙፋኑም የእግዚአብሔር ሰላም ለዘላለም ይሁን።” 34የዮዳሄም ልጅ በናያስ ወጥቶ ወደቀበት፤ ገደለውም፤ በምድረ በዳም ባለው በቤቱ ተቀበረ። 35ንጉሡም በእርሱ ፋንታ የዮዳሄን ልጅ በናያስን የሠራዊቱ አለቃ አደረገ፤ በአብያታርም ፋንታ ካህኑን ሳዶቅን አደረገ።
የሳሚ መሞት
36ንጉሡም ልኮ ሳሚን አስጠራውና “በኢየሩሳሌም ቤት ሠርተህ ተቀመጥ፤ ወዲህና ወዲያም አትውጣ። 37በወጣህበትም ቀን፥ የቄድሮንንም ፈፋ በተሻገርህበት ቀን ፈጽመህ እንድትሞት እወቅ፤ ደምህ በራስህ ላይ ይሆናል፤” አለው። 38ሳሚም ንጉሡን “ነገሩ መልካም ነው፤ ጌታዬ ንጉሥ እንደ ተናገረ ባሪያህ እንዲሁ ያደርጋል፤” አለው፤ ሳሚም በኢየሩሳሌም ብዙ ቀን ተቀመጠ።
39ከሦስት ዓመትም በኋላ ከሳሚ ባሪያዎች ሁለቱ ወደ ጌት ንጉሥ ወደ መዓካ ልጅ ወደ አንኩስ ኮበለሉ፤ ሳሚንም “እነሆ፥ ባሪያዎችህ በጌት ናቸው፤” ብለው ነገሩት። 40ሳሚም ተነሣ፤ አህያውንም ጭኖ ባሪያዎቹን ይሻ ዘንድ ወደ ጌት ወደ አንኩስ ዘንድ ሄደ፤ ሳሚም ሄዶ ባሪያዎቹን ከጌት አመጣ። 41ሰሎሞንም ሳሚ ከኢየሩሳሌም ወደ ጌት ሄዶ እንደ ተመለሰ ሰማ። 42ንጉሡም ልኮ ሳሚን አስጠራና “ወዲህና ወዲያ ለመሄድ በወጣህ ቀን ፈጽመህ እንድትሞት እወቅ ብዬ በእግዚአብሔር አላስማልሁህምን? ወይስ አላስመሰከርሁብህምን? አንተም ‘ቃሉ መልካም ነው፤ ሰምቻለሁ፤’ አልኸኝ። 43የእግዚአብሔርን መሐላ እኔስ ያዘዝሁህን ትእዛዝ ስለ ምን አልጠበቅህም?” አለው። 44ንጉሡም ደግሞ ሳሚን “አንተ በአባቴ በዳዊት ላይ የሠራኸውን ልብህም ያሰበውን ክፋት ሁሉ ታውቃለህ፤ እግዚአብሔርም ክፋትህን በራስህ ላይ ይመልሳል። 45ንጉሡ ሰሎሞን ግን የተባረከ ይሆናል፤ የዳዊትም ዙፋን በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ይጸናል፤” አለው። 46ንጉሡም የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፤ ወጥቶም ወደቀበት፤ ሞተም። መንግሥትም በሰሎሞን እጅ ጸና።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ