አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 4
4
የሰሎሞን ሹማምንት
1ንጉሡም ሰሎሞን በእስራኤል ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር። 2የነበሩትም አለቆች እነዚህ ናቸው፤ የሳዶቅ ልጅ ካህኑ ዓዛርያስ፥ 3ጸሐፊዎቹም የሴባ ልጆች ኤልያፍና አኪያ፥ ታሪክ ጸሐፊም የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ፥ 4የዮዳሄም ልጅ በናያስ የሠራዊት አለቃ ነበረ፤ ሳዶቅና አብያታርም ካህናት ነበሩ፤ 5የናታንም ልጅ ዓዛርያስ የሹሞች አለቃ ነበረ፤ የናታንም ልጅ ዛቡድ የንጉሡ አማካሪና ወዳጅ ነበረ፤ 6አሒሳርም የቤት አዛዥ፥ የዓብዳም ልጅ አዶኒራም አስገባሪ ነበረ።
7ለንጉሡና ለቤተ ሰቡም ቀለብ የሚሰጡ በእስራኤል ሁሉ ላይ ዐሥራ ሁለት ሹሞች ለሰሎሞን ነበሩት። ከዓመቱ ውስጥ አንዱን ወር እያንዳንዳቸው ይቀልቡ ነበር። 8ስማቸውም ይህ ነበረ፤ በተራራማው አገር በኤፍሬም የሑር ልጅ፤ 9በማቃጽና በሸዓልቢም በቤትሳሚስና በኤሎንቤትሐና የዴቀር ልጅ፤ 10በአሩቦት የሔሴድ ልጅ፥ ለእርሱም ሰኰትና የኦፌር አገር ሁሉ ነበረ፤ 11በዶር አገር ዳርቻ ሁሉ የአሚናዳብ ልጅ፥ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ጣፈትን አግብቶ ነበር፤ 12ከቤትሳን ጀምሮ እስከ አቤልምሖላና እስከ ዮቅምዓም ማዶ ድረስ በታዕናክና በመጊዶ በጸርታንም አጠገብ በኢይዝራኤል በታች ባለው በቤትሳን ሁሉ የአሒሉድ ልጅ በዓና ነበረ፤ 13በሬማት ዘገለዓድ የጌበር ልጅ ነበረ፤ ለእርሱም በገለዓድ ያሉት የምናሴ ልጅ የኢያዕር መንደሮች ነበሩ፤ ለእርሱም ደግሞ በባሳን በአርጎብ ዳርቻ ያሉት ቅጥርና የናስ መወርወሪያዎች የነበረባቸው ስድሳ ታላላቅ ከተሞች ነበሩበት፤ 14በመሃናይም የዒዶ ልጅ አሒናዳብ፤ 15በንፍታሌም አኪማአስ ነበረ፤ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ባስማትን አግብቶ ነበር፤ 16በአሴርና በበዓሎት የኩሲ ልጅ በዓና፤ 17በይሳኮር የፋሩዋ ልጅ ኢዮሣፍጥ፤ 18በብንያም የኤላ ልጅ ሳሚ፤ 19በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎንና በባሳን ንጉሥ በዐግ አገር፥ በገለዓድ አገር፥ የኡሪ ልጅ ጌበር ነበረ፤ በዚያችም ምድር ላይ እርሱ ብቻውን ሹም ነበረ።
ብልጽግና የሞላበት የሰሎሞን መንግሥት
20ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር። 21ሰሎሞንም ከወንዙ ጀምሮ እስከ ግብጽ ዳርቻ እስከ ፍልስጥኤም ድረስ በመንግሥታት ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር፤ ግብርም ያመጡለት ነበር፤ በዕድሜውም ሙሉ ለሰሎሞን ይገዙ ነበር። 22ለሰሎሞንም ለቀን ለቀኑ ቀለብ የሚሆን ሠላሳ ኮር መልካም ዱቄትና ስድሳ ኮር መናኛ ድቄት፥ 23ከዋላና ከሚዳቋ ከበረሃ ፍየልና ከሰቡ ወፎች በቀር ዐሥር ፍሪዳዎች ሃያም የተሰማሩ በሬዎች አንድ መቶም በጎች ነበረ። 24ከወንዙ ወዲህ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ከወንዙም ወዲህ ባለው አገር ሁሉ ላይ ከቲፍሳ ጀምሮ እስከ ጋዛ ድረስ ነግሦ ነበር፤ በዙሪያውም ባለ በሁሉ ወገን ሰላም ሆኖለት ነበር። 25በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እስራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር። 26ለሰሎሞንም በአርባ ሺህ ጋጥ የሚገቡ የሠረገላ ፈረሶች ዐሥራ ሁለትም ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት። 27እነዚያም ሹሞች እያንዳንዱ በየወሩ ንጉሡን ሰሎሞንንና ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ማዕድ የሚቀርቡትን ሁሉ ይቀልቡ ነበር፤ ምንም አያጎድሉም ነበር። 28እያንዳንዱም እንደ ደንቡ ለፈረሶቹና ለሰጋር በቅሎች ገብስና ጭድ ወደ ስፍራቸው ያመጡ ነበር።
ለሰሎሞን የተሰጠ ጥበብ
29እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው። 30የሰሎሞንም ጥበብ በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብጽ ጥበብ ሁሉ በለጠ። 31ከሰውም ሁሉ ይልቅ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታንና ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ከደራልም ይልቅ ጥበበኛ ነበረ። በዙሪያውም ባሉ አሕዛብ ሁሉ ዝናው ወጣ። 32እርሱም ሦስት ሺህ ምሳሌዎች ተናገረ፤ መኃልዩም ሺህ አምስት ነበረ። 33ስለ ዛፍም ከሊባኖስ ዝግባ ጀምሮ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው እስከ ሂሶጵ ድረስ ይናገር ነበር፤ ደግሞም ስለ አውሬዎችና ስለ ወፎች ሰለተንቀሳቃሾችና ስለ ዓሣዎች ይናገር ነበር። 34ከአሕዛብም ሁሉ፥ ጥበቡንም ሰምተው ከነበሩ ከምድር ነገሥታ ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ሰዎች ይመጡ ነበር።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 4: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ