አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 19
19
ዳዊት አሞናውያንንና ሶርያውያንን ድል እንዳደረገ
(2ሳሙ. 10፥1-19)
1ከዚህም በኋላ የአሞን ልጆች ንጉሥ ናዖስ ሞተ፤ ልጁም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 2ዳዊትም “አባቱ ስላደረገልኝ ወረታ እኔ ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ቸርነት አደርጋለሁ፤” አለ። ዳዊትም አባቱ ስለ ሞተ ሊያጽናናው መልእክተኞችን ላከ፤ የዳዊትም ባሪያዎች ሊያጽናኑት ወደ ሐኖን ወደ አሞን ልጆች ምድር መጡ። 3የአሞን ልጆች አለቆች ግን ሐኖንን “ዳዊት አባትህን አክብሮ የሚያጽናኑህን ወደ አንተ የላከ ይመስልሃልን? ባሪያዎቹስ አገሪቱን ለመመርመር፥ ለማጥፋት፥ ለመሰለልም ወደ አንተ የመጡ አይደሉምን?” አሉት። 4ሐኖንም የዳዊትን ባሪያዎች ወስዶ አስላጫቸው፤ ልብሳቸውንም እስከ ወገባቸው ድረስ ከሁለት ቀድዶ ሰደዳቸው። 5ወሬኞችም ሄደው በሰዎቹ ላይ የተደረገውን ለዳዊት አስታወቁት። ሰዎቹም በብዙ አፍረዋልና ተቀባዮች ላከ፤ ንጉሡም “ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ተቀመጡ፤ ከዚያም በኋላ ተመለሱ፤” አለ።
6የአሞንም ልጆች በዳዊት ዘንድ እንደ ተጠሉ ባዩ ጊዜ ሐኖንና የአሞን ልጆች ከመስጴጦምያ፥ ከአራምመዓካ፥ ከሱባ ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን ይቀጥሩ ዘንድ አንድ ሺህ መክሊት ብር ላኩ። 7ሠላሳ ሁለትም ሺህ ሠረገሎች የመዓካንም ንጉሥ ሕዝቡንም ቀጠሩ፤ መጥተውም በሜድባ ፊት ለፊት ሰፈሩ። የአሞንም ልጆች ከየከተሞቻቸው ተሰብስበው ወደ ሰልፍ መጡ። 8ዳዊትም ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮአብንና የኀያላኑን ሠራዊት ሁሉ ላከ። 9የአሞንም ልጆች ወጥተው በከተማይቱ በር አጠገብ ተሰለፉ፤ የመጡትም ነገሥታት ለብቻቸው በሜዳው ላይ ነበሩ።
10ኢዮአብም በፊትና በኋላ ሰልፍ እንደ ከበበው ባየ ጊዜ ከእስራኤል ምርጥ ምርጦችን ሁሉ ለይቶ በሶርያውያን ላይ አሰለፋቸው። 11የቀረውንም ሕዝብ ለወንድሙ ለአቢሳ ሰጠው፤ በአሞንም ልጆች ላይ ተሰለፉ። 12እርሱም “ሶርያውያን ቢበረቱብኝ እርዳኝ፤ የአሞንም ልጆች ቢበረቱብህ እረዳሃለሁ። 13አይዞህ! ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችንም ከተሞች እንበርታ፤ እግዚአብሔርም ደስ ያሰኘውን ያድርግ፤” አለ። 14ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ለሰልፍ ወደ ሶርያውያን ፊት ቀረቡ፤ እነርሱም ከፊቱ ሸሹ። 15የአሞንም ልጆች ሶርያውያን እንደ ሸሹ ባዩ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ከወንድሙ ከአቢሳ ፊት ሸሹ፤ ወደ ከተማይቱም ገቡ። ኢዮአብም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።
16ሶርያውያንም በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ መልእክተኞች ልከው በወንዝ ማዶ የነበሩትን ሶርያውያን አስመጡ፤ የአድርአዛርም ሠራዊት አለቃ ሾፋክ በፊታቸው ነበረ። 17ዳዊትም በሰማ ጊዜ እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፤ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ መጣባቸው፤ ከእነርሱም ጋር ተዋጋ፤ ዳዊትም በሶርያውያን ላይ በተሰለፈ ጊዜ እነርሱ ከእርሱ ጋር ተዋጉ። 18ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት ሺህ ሠረገለኞች፥ አርባ ሺህም እግረኞች ገደለ፤ የሠራዊቱንም አለቃ ሾፋክን ገደለ። 19የአድርአዛርም ባሪያዎች በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ታረቁ፤ ገበሩለትም፤ ሶርያውያንም ከዚያ ወዲያ የአሞንን ልጆች ይረዱ ዘንድ “እንቢ” አሉ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 19: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ