የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 18

18
ዳዊት በጦርነት የተቀዳጃቸው ድሎች
(2ሳሙ. 8፥1-14)
1ከዚህም በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን መታ፤ አዋረዳቸውም፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ጌትንና መንደሮችዋን ወሰደ። 2ሞዓብን መታ፤ ሞዓባውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት።
3ዳዊትም በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የነበረውን ግዛት ለመያዝ በሄደ ጊዜ የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን እስከ ሐማት ድረስ መታ። 4ዳዊትም ከእርሱ አንድ ሺህ ሠረገሎች፥ ሰባት ሺህም ፈረሰኞች፥ ሃያ ሺህም እግረኞች ወሰደ፤ ዳዊትም ለመቶ ሠረገሎች የሚሆኑትን ብቻ አስቀርቶ የሠረገሎቹን ፈረሶች ቋንጃ ቈረጠ።
5ከደማስቆም ሶርያውያን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ሊረዱ በመጡ ጊዜ ዳዊት ከሶርያውያን ሃያ ሁለት ሺህ ሰዎችን ገደለ። 6ዳዊትም በደማስቆ ሶርያ ጭፍሮች አኖረ፤ ሶርያውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት። እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድል ይሰጠው ነበር። 7ዳዊትም ለአድርአዛር ባሪያዎች የነበሩትን የወርቅ ጋሻዎች ወሰደ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ይዞአቸው መጣ። 8ከአድርአዛርም ከተሞች ከጢብሐትና ከኩን ዳዊት እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ፤ ከዚህም ሰሎሞን የናሱን ኵሬና ዐምዶች የናሱንም ዕቃ ሠራ።
9የሐማትም ንጉሥ ቶዑ ዳዊት የሱባን ንጉሥ የአድርአዛርን ጭፍራ ሁሉ እንደ መታ ሰማ። 10ቶዑም ከአድርአዛር ጋር ሁል ጊዜ ይዋጋ ነበርና ዳዊት አድርአዛርን ወግቶ ስለ መታው ደኅንነቱን ይጠይቅ ዘንድ ይመርቀው ዘንድ ልጁን አዶራምን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም የወርቅና የብር የናስም ዕቃ ይዞ መጣ። 11ንጉሡም ዳዊት ከአሕዛብ ሁሉ ከኤዶምና ከሞዓብ ከአሞንም ልጆች ከፍልስጥኤማውያንም ከአማሌቅም ከማረከው ብርና ወርቅ ጋር እነዚህን ደግሞ ለእግዚአብሔር ቀደሰ።
12ደግሞ የጽሩያ ልጅ አቢሳ ከኤዶማውያን በጨው ሸለቆ ውስጥ ዐሥራ ስምንት ሽህ ሰዎች ገደለ። 13በኤዶምያስም ጭፍሮች አኖረ፤ ኤዶማውያንም ሁሉ ለዳዊት ገባሮች ሆኑ። እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድል ይሰጠው ነበር።
የንጉሥ ዳዊት ሹማምንት
(2ሳሙ. 8፥15-18)
14ዳዊትም በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ፍርድንና ጽድቅን አደረገላቸው። 15የጽሩያ ልጅ ኢዮአብም የሠራዊት አለቃ ነበረ፤ የአሒሉድም ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበረ። 16የአኪጦብም ልጅ ሳዶቅ፥ የአቤሜሊክም ልጅ አብያታር ካህናት ነበሩ፤ ሱሳ ጸሐፊ ነበረ። 17የዮዳሄ ልጅ በናያስ በከሊታውያንና በፈሊታውያን ላይ ነበረ፤ የዳዊትም ልጆች በንጉሡ አጠገብ አለቆች ነበሩ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ