የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 20

20
ዳዊት ረባት ተብላ የምትጠራውን ከተማ ድል እንዳደረገ
(2ሳሙ. 12፥26-31)
1እንዲህም ሆነ፤ በዓመት መለወጫ ነገሥታት ወደ ሰልፍ በሚወጡበት ጊዜ ኢዮአብ ሠራዊቱን አወጣ፤ የአሞንንም ልጆች አገር አጠፋ፤ መጥቶም ረባትን ከበበ። ዳዊትም በኢየሩሳሌም ቈይቶ ነበር። ኢዮአብም ረባትን መትቶ አፈረሳት። 2ዳዊትም የንጉሣቸውን ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፤ ክብደቱም አንድ መክሊት ወርቅ ያህል ነበረ፥ ክቡርም ዕንቍ ነበረበት፤ በዳዊትም ራስ ላይ አስቀመጡት፤ ከከተማይቱም እጅግ ብዙ ምርኮ አወጣ። 3በውስጥዋም የነበረውን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝና በብረት መቈፈሪያ በመጥረቢያም እንዲሠሩ አደረጋቸው። እንዲሁም ዳዊት በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ አደረገ። ዳዊትም ሕዝቡም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
ከፍልስጥኤማውያን ኀያላን ጋር የተደረገ ጦርነት
(2ሳሙ. 21፥15-22)
4ከዚህም በኋላ በጌዝር ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ሆነ፤ ኩሳታዊውም ሴቦካይ ከራፋይም ወገን የነበረውን ሲፋይን ገደለ። 5ደግሞም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ነበረ፤ የያዒርም ልጅ ኤልያናን የጦሩ የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የነበረውን የጌት ሰው የጎልያድን ወንድም ለሕሚን ገደለ። 6ደግሞ በጌት ላይ ሰልፍ ነበረ፤ ከዚያም በእጁና በእግሩ ስድስት ስድስት ባጠቃላይ ሃያ አራት ጣቶች ያሉት አንድ ረጅም ሰው ነበረ፤ እርሱም ደግሞ ከራፋይም የተወለደ ነበረ። 7እስራኤልንም በተገዳደረ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ዮናታን ገደለው። 8እነዚያም በጌት ውስጥ ከራፋይም የተወለዱ ነበሩ፤ በዳዊትና በባሪያዎቹ እጅ ወደቁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ