አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 21
21
ዳዊት የሕዝብ ቈጠራ እንዳደረገ
(2ሳሙ. 24፥1-25)
1ሰይጣንም በእስራኤል ላይ ተነሣ፤ እስራኤልንም ይቈጥር ዘንድ ዳዊትን አነሣሣው። 2ዳዊትም ኢዮአብንና የሕዝቡን አለቆች “ሂዱ፤ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ እስራኤልን ቍጠሩ፤ ድምራቸውንም አውቅ ዘንድ አስታውቁኝ፤” አላቸው። 3ኢዮአብም “እግዚአብሔር ሕዝቡን በአሁኑ ላይ መቶ እጥፍ ይጨምር፤ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! ሁሉ የጌታዬ ባሪያዎች አይደሉምን? ይህን ነገር ጌታዬ ለምን ይሻል? በእስራኤል ላይ በደል ስለ ምን ያመጣል?” አለ። 4ነገር ግን የንጉሡ ቃል በኢዮአብ ላይ አሸነፈ፤ ኢዮአብም ወጥቶ በእስራኤል ሁሉ ላይ ተዘዋወረ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣ። 5ኢዮአብም የቈጠራቸውን የሕዝቡን ድምር ለዳዊት ሰጠ፤ ከእስራኤልም ሁሉ አንድ ሚሊዮን ከመቶ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎችን አገኘ፤ ከይሁዳም አራት መቶ ሰባ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎችን አገኘ። 6የንጉሡ ትእዛዝ ግን በኢዮአብ ዘንድ የተጠላ ነበረና ሌዊና ብንያም ከእነርሱ ጋር አልተቈጠሩም።
7ከዚህም ነገር የተነሣ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ እስራኤልንም ቀሠፈ። 8ዳዊትም እግዚአብሔርን “ይህን በማድረግ እጅግ በድያለሁ፤ አሁን ግን ታላቅ ስንፍና አድርጌአለሁና የባሪያህን ኀጢአት ታስወግድ ዘንድ እለምንሃለሁ፤” አለው። 9እግዚአብሔርንም ለዳዊት ባለ ራዕይ ለጋድ 10“ሂድ፤ ለዳዊት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ሦስቱን ነገሮች በፊትህ አኖራለሁ፤ አደርግብህ ዘንድ ከእነርሱ አንዱን ምረጥ፤’ ብለህ ንገረው፤” ብሎ ተናገረው። 11ጋድም ወደ ዳዊት መጥቶ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘የምትወድደውን ምረጥ፤ 12የሦስት ዓመት ራብ፥ ወይም ሦስት ወር የጠላቶችህ ሰይፍ እንዲያገኝህ ከጠላቶችህ መሰደድን፥ ወይም ሦስት ቀን የእግዚአብሔር ሰይፍ ቸነፈርም በምድር ላይ መሆንን፥ የእግዚአብሔርም መልአክ በእስራኤል ምድር ሁሉ ማጥፋትን ምረጥ፤ አሁንም ለላከኝ ምን እንድመልስ ተመልከት፤’” አለው። 13ዳዊትም ጋድን “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ብዙ ነውና በእግዚአብሔር እጅ ልውደቅ፤ በሰው እጅ ግን አልውደቅ፤” አለው።
14እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ቸነፈርን ሰደደ፤ ከእስራኤልም ሰባ ሺህ ሰዎች ወደቁ። 15እግዚአብሔርም ያጠፋት ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም መልአክን ሰደደ፤ ሊያጠፋትም በቀረበ ጊዜ እግዚአብሔር አይቶ ስለ ክፉው ነገር ተፀፀተ፤ የሚያጠፋውንም መልአክ “በቃህ፤ አሁን እጅህን መልስ፤” አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር። 16ዳዊትም ዐይኖቹን አነሣ፤ የእግዚአብሔር መልአክ በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ፥ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ተዘርግቶ አየ። ዳዊትም ሽማግሌዎችም ማቅ ለብሰው በግምባራቸው ተደፉ። 17ዳዊትም እግዚአብሔርን “ሕዝቡ ይቈጠር ዘንድ ያዘዝሁ እኔ አይደለሁምን? የበደልሁና ክፉ የሠራሁ እኔ ነኝ፤ እነዚህ በጎች ግን ምን አድርገዋል? አቤቱ አምላኬ ሆይ! እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን፤ ነገር ግን ይቀሰፍ ዘንድ በሕዝብህ ላይ አትሁን፤” አለው።
18የእግዚአብሔርም መልአክ ዳዊት ወጥቶ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ ላይ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራ ዘንድ ለዳዊት እንዲነግረው ጋድን አዘዘው። 19ዳዊትም በእግዚአብሔር ስም እንደ ተናገረው እንደ ጋድ ነገር ወጣ። 20ኦርናም ዘወር ብሎ መልአኩን አየ፤ እርሱም ጋር የነበሩ አራቱ ልጆች ተሸሸጉ፤ ኦርናም ስንዴ ያበራይ ነበር። 21ዳዊትም ወደ ኦርና በመጣ ጊዜ ኦርና ተመልክቶ ዳዊትን አየ፤ ከአውድማውም ወጥቶ ዳዊትን እጅ ሊነሣ በምድር ላይ ተደፋ። 22ዳዊትም ኦርናን “በላዩ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እሠራ ዘንድ ይህን የአውድማ ስፍራ ስጠኝ፤ በሙሉ ዋጋ ስጠኝ፤ መቅሰፍቱም ከሕዝቡ ይከለከላል” አለው። 23ኦርናም ዳዊትን “ለአንተ ውሰደው፤ ጌታዬ ንጉሡም ደስ የሚያሰኘውን ያድርግ፤ እነሆ፥ ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሬዎቹን፥ ለእንጨትም የአውድማውን ዕቃ፥ ለእህልም ቍርባን ስንዴውን እሰጥሃለሁ፤ ሁሉን እሰጣለሁ፤” አለው። 24ንጉሡም ዳዊት ኦርናን “አይደለም፤ ነገር ግን ለአንተ ያለውን ለእግዚአብሔር አምጥቼ የሚቃጠል መሥዋዕት በከንቱ አላቀርብምና በሙሉ ዋጋ እገዛዋለሁ፤” አለው። 25ዳዊትም ስለ ስፍራው ስድስት መቶ ሰቅል ወርቅ በሚዛን ለኦርና ሰጠው። 26ዳዊትም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት አቀረበ፤ እግዚአብሔርንም ጠራ፤ ከሰማይም ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ በእሳት መለሰለት። 27እግዚአብሔርም መልአኩን አዘዘው፤ ሰይፉንም በአፎቱ ከተተው።
28በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ እንደ መለሰለት ዳዊት ባየ ጊዜ፥ በዚያ መሥዋዕት ሠዋ። 29ሙሴም በምድረ በዳ የሠራት የእግዚአብሔር ማደሪያና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያ በዚያን ጊዜ በገባዖን ባለው በኮረብታው መስገጃ ነበሩ። 30ዳዊት ግን የእግዚአብሔርን መልአክ ሰይፍ ስለ ፈራ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደዚያ ይሄድ ዘንድ አልቻለም።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 21: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ