መጽሐፈ ጥበብ 18
18
ለእስራኤል ብርሃን እንደ ወጣላቸው
1በጻድቃንህ ዘንድ ግን ታላቅ ብርሃን ነበር፥ እነዚያ ቃላቸውን ይሰሙ ነበርና፥ መልካቸውን ግን አያዩም ነበርና።#ግሪኩ “ነገር ግን እነርሱ የተሠቃዩትን ያህል ስላልተሠቃዩ ደስ እንደ ተሰኙ ይቈጥሩአቸው ነበር” የሚል ይጨምራል። 2እነዚያ የሚወዷቸውን ይደበድቧቸው ነበርና፤ የተበደሉትንም መከራ ስለ አጸኑባቸው እርስ በርሳቸው ይመሰጋገኑ ነበር።#ግሪኩ “ጠላቶቻቸው የበደሉአቸውን ሰዎች አመሰገኑአቸው፥ ምክንያቱም ስለ ፈጸሙባቸው በደል አልተበቀሉአቸውምና፥ ሀገራቸውንም ለቅቀው እንዲሄዱ ለመኑአቸው” ይላል። 3እነዚህ ግን በተላከላቸው የማዳን ስጦታ ደስ አላቸው፥ የማይታወቅ ጎዳናንም ይመራቸው ዘንድ የእሳት ዐምድን ሰጣቸው፥ በሚወደደውም መንገድ የማያቃጥል ፀሐይን ሰጣቸው። 4ብርሃንን ያጡ ዘንድ፥ በጨለማም ይታሰሩ ዘንድ ለእነዚያ ይገባቸዋል፤ ለዓለም ይሰጥ ዘንድ ያለው፥ የማያልፍ የሕግህ ብርሃን ያላቸው ልጆችህን አስረው አግዘዋቸዋልና።
የግብፃውያን የበኵር ልጆች ሞት
5የጻድቃን ልጆችን ይገድሉ ዘንድ ባሰቡና በመከሩ ጊዜ፥ ለዘለፋ ሊሆንባቸው አንዱ ሕፃን ተጥሎ ዳነ። በእርሱም ብዙዎች ልጆቻቸውንና ማኅበራቸውን ሁሉ ያለ ርኅራኄ በብዙ ውኃ አጠፋህ። 6የተማማሉባትን መሐላ ባወቁ ጊዜ፥ በፍቅር ያስቧት ዘንድ አባቶቻችን ያቺን ሌሊት ዐወቋት። 7ለጻድቃን ሕዝብህ ደኅንነትን፥ ለተቃዋሚዎች ጠላቶችም ጥፋትን ሰጠህ። 8የሚቃረኑትን እንዳጠፋሃቸው፥ እንዲሁ የጠራኸንን እኛን አክብረኸናልና። 9አገልጋዮችህ ጻድቃን ያማረ መሥዋዕትን ይሠዉ ነበረና፥ በመስማማትም የጌትነትህን ሕግ በልቡናቸው አሳድረዋልና በዚህ አምሳል ቅዱሳን መልካሙን ነገር ተቀበሉ፥ መከራውም ለሚገባቸው ነው። አባቶቻችን ግን የምስጋናውን መዝሙር በደስታ ይዘምሩ ነበር።
10ነገራቸው ሳይተባበር ከጠላቶች ልቅሶ ጩኸት ጋር ቃላቸው ይገናኝ ነበር። እናቶችም ስለ ልጆቻቸው የልቅሶውን ድምፅ ያደምጡ ነበር። 11የባሪያውም ቅጣት ከጌታው ጋር በመቅሠፍት ተካከለ። ጭፍራውንና ንጉሡንም ይህች መከራ እኩል አገኘቻቸው። 12ሁሉም በአንድነት በአንድ አምሳል ሞቱ፤ ቍጥር የሌላቸው የሞቱ ሰዎች በድኖችም ነበሩ። በአንዲት ሰዓት የከበረች ፍጥረታቸው ፈጽማ ስለ ጠፋች ሕያዋን የሞቱትን ሰዎች ይቀብሯቸው ዘንድ አልቻሉምና። 13ስለ ሟርታቸውም የመጣባቸውን መቅሠፍት ሁሉ አላወቁምና በበኸር ልጃቸው መጥፋት ሕዝቡ የእግዚአብሔር ልጆች እንደ ሆኑ ዐወቁ። 14ፍጹም ጸጥታ ፍጥረትን ሁሉ በሸፈነ ጊዜ፥ ሌሊቷም በፍጥነቷ መካከል ሳለች፥ 15ሁሉን የሚችል ቃልህ እንደ ድል አድራጊና ጦረኛ ሆኖ፥ ከሰማያት ከዙፋንህ ውስጥ ወደ ጥፋት ምድር መካከል ወረደ። 16አድልዎ የሌለባት ትእዛዝህንም እንደ ተሳለ ሰይፍ ታጥቆ፥ በመካከላቸውም ቆሞ አውራጃዎቻቸውን ሁሉ በሞት ሞላ፥ ሰማይንም ነካ፤ በምድርም ቁሞ ነበር። 17ያንጊዜም በአስፈሪዎች ሕልሞች ምትሀት አወካቸው፥ ያላሳቧት ድንጋጤም በላያቸው ሠለጠነችባቸው። 18ከእነርሱም እኩሌታው የሞተ ሆኖ በሌላ ቦታ የሚወድቅ ነበረ፥ የሚሞቱባትንም ምክንያት ገለጠላቸው። 19ክፉ ነገር ስለምን እንደሚያገኛቸውና እንደሚያጠፋቸውም ባለማወቅ እንዳይሆኑ ያወኳቸው ሕልሞች አስቀድመው ይህን ነግረዋቸዋልና።
በእስራኤል ላይ ስለ ታዘዘው መቅሠፍት አሮን እንደ ጸለየ
20ከጻድቃንም አስቀድሞ ለሞት የሚያበቃ መከራ ያገኛቸው አሉ። በምድረ በዳም መቅሠፍት ሆነ፥ ከእነርሱም ብዙዎችን አጠፋ። ነገር ግን መቅሠፍቱ ብዙ ዘመን አልዘገየም። 21ነውር የሌለበት ሰው ጸሎት የሚጸልይበትን፥ ዕጣንም የሚያጥንበትን የአገልግሎት መሣሪያ፥ ልብሰ መትከፉን ይዞ ፈጥኖ ተዋግቶአልና ኀጢአታቸውን ለማቃለል ባለሟልነትን አገኘ፤ መዓቱን ተቃወመ፥ መቅሠፍቱንም ጸጥ አደረገ። በዚህም ያንተ መልእክተኛ እንደ ሆነ ራሱን አስታወቀ። 22አጥፊዎችንም አሸነፈ፤ በሥጋዊ ኀይል ወይም በጦር መሣሪያ አይደለም፤ ነገር ግን የአባቶችን መሐላና ቃል ኪዳናቸውን በማሰብ ቀሣፊውን በቃልህ አስወገደ። 23ብዛታቸው የማይቈጠር የሞቱ ሰዎች እርስ በርሳቸው በወደቁ ጊዜ በበሽተኞቹና በሕያዋኖቹ መካከል ቁሞ መቅሠፍቱን ጸጥ አደረገ። ለሕያዋንም መንገድን ለየ። 24የዓለሙ ክህነት ሁሉ በልብሱ ጫፍ ላይ ነበርና፥ ባሕርይ በሚባሉ ዕንቍዎች አራት ዙሪያዎች የተቀረጸው የአበውም ክብር በጫንቃው ላይ ነበርና፥ የአንተም ልዕልና በራሱ አክሊል ላይ ነበርና። 25በዚህም የሚያጠፉ ቸነፈሮች ራቁ፥ እነዚህ ሥራዎችም አስፈሯቸው፥ ነገር ግን መቅሠፍቱ ብቻ በበቃ ነበር።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 18: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ