መጽሐፈ ጥበብ 17
17
በግብፃውያን ላይ ፍርሀት በሌሊት እንደ ወደቀችባቸው
1ፍርድህ ታላቅ ነው፥ ለመናገርም ድንቅ ነው። ስለዚህም የፈጣሪ ትምህርት የሌላቸው ሰውነቶች ሳቱ። 2ኃጥኣን ቅዱስ ሕዝብን በያዙ ጊዜ፥ በተበረታቱባቸውም ጊዜ፥ ኀያላንም በረዥም የሌሊት ጨለማ በታሰሩ ጊዜ ያንጊዜ በቤታቸው ጣራ ስር ተጋዙ። ከዘለዓለማዊው አገልግሎት ሥርዐትም ሸሸተው ተገኙ። 3የበደሉትንም ዐስበው በውስጡ ብርሃን በሌለበት ቤት ውስጥ ከዝንጋዔ መጋረጃ በታች ተሰወሩ፥ እጅግም እየተደነቁ በድንጋጤ ቀለጡ፥ በምትሀትም ታወኩ። 4የያዛቸው አመንዝራ#ግሪኩ “ያሉበት አዳራሽ” ይላል። ከድንጋጤ ይጠብቃቸው ዘንድ አልቻለም፥ ነገሩ ስቅጥጥ የሚያደርግ የታላቅ ቃል ድምፅም ያውካቸው ጀመር። የክፉ ምትሀት መልክም ፊቱ ያዘነውን ሁሉ አጠፋ። 5የእሳቱም ብርሃን አንዲት ሰዓት እንኳ ያበራ ዘንድ አልቻለም፥ የብሩሃን ከዋክብት ብርሃንም ለዚያች ለምታስፈራዋ ሌሊት ጨለማ ያበራ ዘንድ አልቻለም። 6ነገር ግን ከዚህ ከሚታየው መልክ ይልቅ ግርማው ፍጹም የሆነ፥ ከማይታዩትም መልኮች ይልቅ የከፋ ብቸኛ እሳት ድንገት ታያቸው። 7በሚሳደቡት ላይ የትዕቢት ዘለፋ ሊሆንባቸው የስንፍና ድካም የሆነ የሟርት ሥራን ከወርቅና ከብር አደረጉ። 8ከታመመች ሰውነት ሁከትንና ድንጋጤን ያስወግዱ ዘንድ ተስፋ የሰጡ እነዚህን ፍርሀት አሳመማቸው፥ ለሣቅም የተገቡ ሆኑ።
9የሚያውከው ነገር ምንም ባያስፈራቸው የሚበርር ተሓዋሲ እንቅስቃሴና የእባቦች ጩኸት አባረራቸው። አስደንግጦም አሸሻቸው። ከሁሉ አቅጣጫ የሚሸሽ ነፋስንም ማየት አልተቻላቸውም። 10የክፉ ሰው ሥራው የሚያስመሰክርበትና የሚያስፈርድበት ዐመፅ ነው፥ ሁልጊዜም እየታወቀውና ዕውቀት ባለው ሕሊና እየተመለከተ ክፉና ጠማማ ሥራን ይቀበላል፥ ይሠራልም። 11ፍርሀት ምንም አይደለም፥ ነገር ግን የፍርድ ጥርጥርን በሕሊና ያሳድራል። 12ጥቂት ወይም ጐደሎ የልቡና ጥርጥር ብትኖርም ባለማወቅ ነው፥ በስንፍናም ነው፥ ለፍርድም መንገድ የምትሰጥ ናት ተብላ ትታሰባለች። 13በእውነት ሊታገሡአት ከማይቻል ከሲኦል ጕድጓድ የወጣች ያች ሊታገሡአት የማይቻል ሌሊት እነርሱን በሸፈነቻቸው ጊዜ ያችን ቀን ተኝተው ነበር። 14የሚያስደነግጡ አጋንንት አስደንግጠዋቸዋልና፥ ምትሀትን በማሳየት የሚያሳድዱአቸው አሉ፥ የሰውነትንም ተስፋ የሚያደክም አለ፥ ያልጠበቁትና ያልተጠራጠሩት ፍርሀትና ድንጋጤም ድንገት ደረሰባቸው። 15በዚያም ያለው ማንኛውም ሁሉ እንዲህ ነው፥ የወደቀም ቢሆን፥ በእግር ብረት ወይም ያለ እግር ብረት ታስሮ በእስር ቤት የሚጠበቅም ቢሆን፥ 16አራሽም ቢሆን፥ እረኛም ቢሆን፥ በምድረ በዳ ተቀምጦ ምድርን በማረስ የሚደክም ምንደኛም ቢሆን፦ ያገኘችውን ያችን አስጨናቂ መከራ ታግሦአልና።
17ማኅበራቸው በአንዲት የጨለማ እግር ብረት ታስሯልና ያገኛቸው ምትሀት እንዲህ ነው፥ የሚያፏጭ ምትሀት፥ ወይም ጭፍቅ ካሉና ከሚያስጠልሉ ከዛፎች የተነሣ ድምፁ ያማረ የቅርንጫፎች ቃል ወይም ዜማቸው ያማረ የወፎች ድምፅ፥ 18ወይም በኀይል የሚሄድ የውኃ ሿሿቴ ድምፅ፥ ወይም በማስፈራራት የሚገለባበጡ የዋሻዎች ድምፅ፥ ወይም የሚሮጡና ሩጫቸው የማይታይ የእንስሳት ሩጫ፥ ወይም በሚያስፈራ ቃል የሚጮኹ የአውሬዎች ጩኸት፥ ወይም ከአዕዋፍና ከአራዊት ድምፅ የተነሣ እርስ በርሳቸው ድምፅን ለዋውጠው የሚመልሱ የሚያስፈሩ የተራራዎች ድምፅ ነው። አስደንግጦም ያጠፋቸው መከራ እንዲህ ነው። 19ዓለሙ ሁሉ በሚያበራ ብርሃን ይበራ ነበርና፥ ያለማቋረጥና ያለመከልከልም ሥራውን ይፈጽም ነበርና። 20እነዚህን ግን ብቻቸውን ይወስዳቸው ዘንድ ያለው የጨለማ ምሳሌ የሆነው የሌሊት ክብደት ሰወራቸው፥ እነርሱ ራሳቸውም ለራሳቸው ከጨለማ የጸኑ ናቸው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 17: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ