መጽሐፈ ጥበብ 19
19
ግብፃውያን በኤርትራ ባሕር እንደ ሰጠሙ
1በዝንጉዎች ላይ ግን ያለ ርኅራኄ ፈጽማ እስክትጨርሳቸው ድረስ መዓትህ ጸናች። የሚደረግ ሥራቸውን አስቀድመው ዐውቀዋልና። 2እነዚያ ከመሄድ መልሰዋቸዋልና፥ ዳግመኛም በብዙ ችኮላ ሰድደዋቸዋልና፥ በተጸጸቱም ጊዜ በሩጫ ገሠገሡ፥ በፊታቸውም ማዕበል አለ ብለው ተከተሏቸው። 3ገና በልቅሶ ሳሉ፥ በመቃብሮቻቸውም ላይ ሲጮኹ ልዩ የስንፍና ዐሳብ ስቧቸዋልና፥ ከእነርሱ ይሄዱ ዘንድ ማልደው ያስወጧቸውን እንደ ኰበለሉ ሰዎች ይከተሏቸው ዘንድ በሩጫ ገሠገሡ። 4የተገቧት የመከራ መጨረሻ ወደዚህ ሥራ ሳበቻቸው፤ ዝንጋዔም አሳታቸው፥ የጐደለውንም ፍርድ በፍርዶች ቍጥር ይፈጽሙና ይሞሉ ዘንድ ያገኛቸውን መከራ አላሰቡም። 5ወገኖችህ ግን ድንቅ መንገድን ሄዱ፥ እነዚያም ክፉ ሞትን አገኙ።
እግዚአብሔር እስራኤልን እንደ ጠበቃቸውና እንደ አዳናቸው
6ፍጥረት ሁላ ከወገኖችዋ ጋር በእነርሱ ላይ ተለወጠች፤ ዳግመኛ ልጆችህ ያለ ክፋት በደኅና ይጠበቁባት ዘንድ የታዘዘችበትን ትእዛዝ እያገለገለች ተለወጠች። 7ደመና ሰፈሩን ጋረደች፥ ውኃዋም ከቀድሞዋ ይልቅ የረጋች ሆና ታየች፥ የደረቀችውም ምድር የለመለመች መስክ ሆና ታየች፥ በኤርትራ ባሕር መካከልም መሰናክል የሌለው መንገድ ታየ። 8በከበረች እጅህና ከፍ ባለች ክንድህ ተጋርደው፥ ወገኖችህ ሁሉ ባለፉበት ኀይለኛ ማዕበል መካከልም የለመለመ መስክ ታየ፤ ድንቅ ሥራህንም ባዩ ጊዜ ይህችን እጅህን አመሰገኑ። 9አቤቱ፥ ያዳንሃቸው እነርሱ አንተን እያመሰገኑ እንደ ፈረሶች ተሰማሩ፥ እንደ ወይፈኖችም ዘለሉ። 10በባዕድ ሀገር በእንግድነት በነበሩ ጊዜ ያደረጉትን ሁሉ ዐስበዋልና፤ ምድራቸው እንስሳትን በማስገኘት ፋንታ ተቈናጣጭ ዝንብን እንዴት አወጣች? ባሕርስ በብዙው ውኃ ውስጥ በነበረው ዓሣ ፋንታ ጓጕንቸርን እንዴት አስገኘች?
11ከዚህም በኋላ መናውን በመገብሃቸው ጊዜ፥ አዲስ የአዕዋፍ ፍጥረትን አዩ፥ የተድላና የደስታ ምግብን በተመኙና በለመኑ ጊዜም፥ ብዙ ፍላጎታቸውን ለማርካት ከባሕር ውስጥ ብዙ ድርጭት ወጣላቸው። 12ከመብረቆች ያልራቀች ቀድሞ በተአምር በተደረገው የመቅሠፍት ኀይል የምትመሰል መቅሠፍት በኃጥኣን ላይ መጣች፥ እነርሱ እንደ ክፋታቸው ሚዛን በእውነት ተፈርዶባቸዋልና።
13እንግዶችን ስለ መቀበል እጅግ የተጠላ ጠባይን ወድደዋልና፥ እነዚህ የማያውቋቸው በደረሱ ጊዜ አልተቀበሉአቸውም፤ እነዚያ ግን መልካም እያደረጉ ሲጠቅሙአቸው በእነርሱ ዘንድ በእንግድነት የኖሩትን አስጨንቀው ገዙአቸው። 14በዚህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለሥራቸው መጐብኛና መመርመሪያ ይሆን ዘንድ ነው፥ በእነርሱ ዘንድ እንግዳ የሆኑትን በጭንቅ ይቀበሏቸው ነበርና። 15እነዚህ ግን በዓል በማድረግ የተቀበሏቸውንና ከእነርሱ የአንድ ሕግ ተካፋዮች ያደረጓቸውን ጻድቃን በጭንቅ መከራ አጸኑባቸው። 16ስለዚህ በጻድቃን ደጃፍ እንደ ተሰበሰቡ እንደ እነዚያ ሰዎች ብርሃንን በማጣት ተቀጡ፥ ድንገት በጥልቅ ጨለማ ተግዘዋልና፥ ከእነርሱም እያንዳንዱ የቤቱን የደጃፉን መግቢያ መንገድ ይፈልግ ነበር። 17ብርሃናት ከባሕርያቸው ተለውጠውባቸው ነበርና፤ የዜማውን ነገር በማወቅ የበገናው ስም እንደሚለወጥ፥ የቀናም ሆኖ በዜማው ጸንቶ እንደሚኖር በየወገናቸው የተፈጠሩትን በማየት ፈጽሞ የሚሰፈር ሥራም፥ እንዲሁ ነው።
የእግዚአብሔር ተአምራዊ ኀይል
18በደረቅ ያሉ ፍጥረቶች ወደ ውኃ ተመልሰዋልና፥ በውኃ የሚንቀሳቀሱና የሚዋኙ ፍጥረታትም ኑሮአቸው ወደ የብስተመልሷልና። 19እሳቱም በውኃው ውስጥ ፈጽሞ በረታ፥ ውኃውም የባሕርዩን ተፈጥሮ ሰወረ። 20ፈጥኖ የሚጠፋ የእሳቱም ነበልባል ሥራው ባይደለ በመካከላቸው ወዲያና ወዲህ እያለና እየተመላለሰ የከብቶችን ሥጋ አላቃጠለም። የማይጠፋ የፍጥረታት ወገን እሳትም ፈጥኖ የሚቀልጥ ውርጭን አላቀለጠውም። አቤቱ፥ በሥራው ሁሉ የወገኖችህን ክብር ፈጽመህ አብዝተሃልና። በሁሉም አክብረሃቸዋልና ወደ እኛም በመጣው ነገር ሁሉ ቸርነትህን አላራቅህብንም፥ እኛንም በየጊዜው ቸል አላልኸንም፥ በየቦታውም ሁሉ በዚያ አንተ ትኖራለህ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 19: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ