መጽሐፈ ጥበብ 16
16
ስለ እስራኤል ድኅነትና ስለ ግብፃውያን ጥፋት
1ስለዚህም አምልኮታቸውን በሚመስል በሚገባ ተቀጡ፥ በብዙ ተናካሽ ትንኞችም ተሠቃዩ። 2ለሕዝብህም በጠላቶቻቸው ፊት በጎ አደረግህላቸው፥ ለፍላጎታቸውም ድርጭትን ሰጠሃቸው። ጣዕሙ ልዩ የሆነ መናንም ይበሉ ዘንድ ሰጠሃቸው። 3እነዚያ ግን መብልን በተመኙ ጊዜ በእነርሱ ስለ ተላከባቸው ፍጥረት ከፍላጎታቸው ተመለሱ፥ የዘወትሩንም ልማድ ናቁ። እነዚህ ግን ምግብን በማጣት ጥቂት ወራት ከተቸገሩ በኋላ ጣዕሙ ልዩ ለሆነ ምግብ ተዘጋጁ። 4በእነዚህ ላይ ፍርድ ያለ ርኅራኄ ይደርስ ዘንድ ግድ ነው። ክፉዎችና በኀይል የሚገዙ ናቸውና። ነገር ግን ለእነዚህ የሚገባው ጠላቶቻቸው እንዴት እንደሚሠቃዩ ያዩ ዘንድ ብቻ ነው።
5የክፉዎች አራዊት ቍጣ ቢመጣባቸው፥ በክፉዎች እባቦች መንደፍም ቢያልቁ፥ ለጥቂት ወራት ይቀጡ ዘንድ ታወኩ እንጂ ቍጣህ ለብዙ ጊዜ የጸናባቸው አይደለም፤ 6ይህም ምልክት የሕግህን ትእዛዝ ያሳስባቸው ዘንድ ለድኅነት ማስጠንቀቂያ ሆናቸው። 7ሁሉን የምታድን ሆይ፥ ከእነርሱ የተመለሰው በአንተ ዳነ እንጂ በማየት ብቻ የዳነ አይደለም። 8በዚህም ፈተንኻቸው፥ ከክፉ ሁሉ የምታድን አንተ እንደ ሆንህም ጠላቶቻችንን አሳመንኻቸው። 9የተቈናጣጭ ዝንብና የአንበጣ ንክሻ እነዚህን አጥፍትዋቸዋልና፤ ለነፍሳቸውም ድኅነትን አላገኙም፤ በእንደዚህ ያለ ምሳሌ ልትፈርድባቸው ይገባቸዋልና። 10በልጆችህ ግን መርዝ ያለው የእባቦች ጥርስ በታዘዘ ጊዜ አልጐዳቸውም፥ ቸርነትህ መጥቶ አድኖአቸዋልና። 11ሕግህን ለማሰብ ይህን ቀምሰዋልና፥ በጽኑ ዝንጋዔም እንዳይወድቁ፥ ተአምራትህንም ከማሰብ ወጥተው በሌላ ሥራና መከራ እንዳይወድቁ ፈጥነው ዳኑ።
12አቤቱ፥ ሁሉን የሚያድን ቃልህ ነው እንጂ የሚጠጡት እንጨት ፥ የሚቀቡትም መድኀኒት ያዳናቸው አይደለም። 13በሕይወትና በሞት ላይ ሥልጣን አለህና፥ ወደ ሲኦል በሮች ታወርዳለህ፥ ከሲኦልም ታወጣለህ። 14ሰው ግን በክፉ ይገድላል፥ ነፍስ ከሥጋ ከተለየ በኋላ አይመለስም፥ የተለየች ነፍስም አትመለስም። 15ከእጅህ ግን መሸሽ አይቻልም።
ማዕበል ግብፃውያንን እንደ መታ
16ዝንጉዎች እንዲክዱህ ባወቅህ ጊዜ በክንድህ ኀይል ተቀሠፉ፤ በልዩ ዝናምና በረድ፥ ያለ ምሕረትና ያለ መገታት በወረደ በሰማይ ሿሿቴ ጠፉ፥ በእሳትም አለቁ። 17ድንቅ ሥራስ ሁሉን በሚያጠፋ በውኃ ውስጥ የእሳት ኀያል መሆንና መሠልጠን ነው። ዓለም ለጻድቃን ረዳት ነውና። 18የእሳት ነበልባል በዝንጉዎች ላይ የተላኩ እንስሳትን እንዳያቃጥል ለማዳ ሆነ፥ ነገር ግን ይህን ባዩ ጊዜ በእግዚአብሔር ፍርድ እንደሚጠፉ ያውቃሉ። 19የዐመፀኛዋን ምድር ፍሬ ያጠፋ ዘንድ የእሳቱ ኀይል በውኃው መካከል የሚነድድበት ጊዜ ነበር።
ለእስራኤል መና ስለ መውረዱ
20ስለ ፍሬውም ፋንታ የመላእክትን ምግብ ለሕዝብህ መገብኻቸው፥ ያለ ድካም የተዘጋጀ፥ ጣዕሙም ከሚጣፍጠው ሁሉ የሚበልጥ፥ ጣዕምንም ሁሉ የሚያስንቅ ኅብስትን ከሰማይ ላክህላቸው። 21የሰማያዊው መልክህ አርአያ የሚሆን መና ለልጆችህ የፍቅርህን ጣዕም ገለጠ፥ ከእርሱም ለሚበላ ጣዕሙ ይዘዋወር ነበር፥ ከምግቦችም ይልቅ ያሰበውንና የወደደውን ፍላጎቱን ለመፈጸም ያገለግለው ነበር። 22በረድና ውርጭ ከእሳት ጋር ጸንተው ቆሙ፤ እሳቲቱ በበረዱ መካከል እየነደደች፥ በዝናሞችም መካከል ቦግ ቦግ እያለች፥ የጠላቶችን አዝመራ ፍሬ እንዳጠፋች ያውቁ ዘንድ አልቀለጡም። 23ጻድቃንም ዳግመኛ ይህን በተመገቡ ጊዜ የራሳቸውን ምግብ ኀይል ይረሳሉ።
24ፈጣሪ ሆይ፥ ፍጥረቱ ሁሉ ለአንተ ያገለግላልና፥ በዐመፀኞች ላይ የሚላክ ፍርድን ታመጣለህ፥ በአንተ ወደሚታመኑም ይደርስ ዘንድ ደስታን ትሰጣለህ። 25ስለዚህም ያንጊዜ ስጦታህ ነበረች፥ ወደ ሥራውም ሁሉ ትለዋወጥ ነበር፤ በለመኑትና በወደዱትም ምግብ ሁሉ ታገለግል ነበር። 26አቤቱ በአንተ ያመኑ ሰዎችን ቃልህ ይጠብቃቸዋል እንጂ፥ ሰው የሚመገበው የተለያየ የዘር ፍሬ እንዳይደለ የወደድኻቸው ልጆችህ ያውቁ ዘንድ ነው። 27እሳት የማያጠፋው መና በጥቂት የፀሐይ ሙቀት ሞቆ ቀልጧልና። 28በፀሐይ መውጫ በኩል አንተን እናመሰግን ዘንድ፥ ወዳንተም እንለምን ዘንድ ፀሐይ ወደ እኛ እንዲመጣ ይፈለጋልና ይህ ይታወቅ ዘንድ ነው። 29ለማያመሰግን አለኝታው እንደ ክረምት ውርጭ ይቀልጣልና፥ እንደማይረባ ርኩስ ውኃም ይፈስሳልና።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 16: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ