መጽሐፈ ጥበብ 15
15
እውነተኛውን አምላክ የማምለክ ጥቅም
1አንተ ፈጣሪያችን ግን ቸር፥ እውነተኛ፥ ታጋሽም ነህ፥ በምሕረትህም ሁሉን ትሠራለህ። 2ኀይልህን እያወቅን ብንበድል፥ ያንተ መሆናችንን እያወቅንም ባንበድል ያንተ ነን። 3አንተን ማወቅ ፍጽምት ጽድቅ ናትና፥ ኀይልህንም ማወቅ የሕይወት ሥር ናትና። 4ክፉ ዐሳብ፥ የሰው ጥበብ፥ ፍሬ የሌለው የማስጌጥ ድካም፥ ወይም ቀለም በመቀባት መልካቸው የሚለወጥ ሥራዎች አያስቱንምና። 5የእነዚህም መልካቸው እነርሱን ወደ መመኘት ይመጣ ዘንድ አላዋቂን ሰው ይስበዋል፤ ነፍስና መንቀሳቀስ የሌለው ምውት ጣዖትንም ያስወድደዋል። 6የሚሠሯቸው የሚወዷቸውና የሚያመልኳቸውም ክፋትን የሚወድዱ ናቸው። እንደዚህም የሚያደርጉ በእነርሱ ላይ ተስፋ ያደርጋሉ።
የሸክላ ጣዖትን የማምለክ ሞኝነት
7ሸክላ ሠሪ ለስላሳ አፈርን በለወሰ ጊዜ ከእኛ ለእያንዳንዱ ሁሉ ሊያገለግል የሚገባውን የተለያየ ሥራን ይሠራል፥ ነገር ግን ከዚያው ጭቃ ለንጹሕ ሥራ አገልግሎት ዕቃዎችን ይሠራል፥ እንደዚሁም ለሌሎች ሥራዎች በእነዚህ አምሳል ይሠራል፤ የእነዚህም ሁሉ ተግባር ለተለያየ መፍቅድ ነው፥ ነገር ግን ይህ ወይም ያ ለምን ጥቅም እንደሚውል ፈራጁ ዳኛ ሸክላ ሠሪው ነው። 8ለክፋት የሚደክም ሰው ግን ከዚያ ጭቃ ከንቱ ጣዖትን ይሠራል፥ ይህም ከጥቂት ቀን አስቀድሞ ከምድር ተሠራ፤ ከጥቂት ቀንም በኋላ ከእርሷ ወደ ወጣባት ምድር ይመለስ ዘንድ አለው፥ ስለ ነፍሱ ፍርድም ይመረመራል።
9በእርሱም ዘንድ ያለው ትጋት ይሠራና ይደክም ዘንድ ስላለውና ሕይወቱም ጥቂት ስለሆነ አይደለም። ወርቅና ብርን የሚሠሩ ሰዎችን ይፎካከራቸው ዘንድ ነው እንጂ፤ ናስ ሠሪዎችንም ይመስላቸው ዘንድ ነው እንጂ፥ የተዋረደውንም ሠርቶ ክብር ይሰጠዋል። 10ልቡናው አመድ ነው፥ ተስፋውም ከአፈር ይጐሰቍላል፥ ሕይወቱም ከጭቃ እጅግ የተናቀ ነው። 11የፈጠረውንና ነባቢት ነፍስን ያሳደረበትን፥ የሕይወት መንፈስንም እፍ ያለበትን አላወቀውምና። 12ነገር ግን እነዚህ ሕይወታችንን ጨዋታና መዘባበቻ አድርገው ዐሰቡ፥ ኑሯችንንም የትርፍ ምልክት አደረጉት፤ ስላጣሁ ይጨንቀኛል ብሏልና፥ ከዚህም በኋላ ያተርፋል፥ ክፋትንም ገንዘብ ያደርጋል። 13ይህም ከሁሉ ፈጽሞ እንደሚበድል ታወቀ፥ በምድር ከሚታየውና ፈጥኖ ከሚጠፋው ከእንጨት የተቀረፀ ጣዖትን ሠርትዋልና።
14ሁሉም አላዋቂዎችና ጐስቋሎች ናቸው፥ ሁሉም ከተማረኩ ወገኖች ተለይተው ሙታን ናቸው፥ በእርሱ የታሰሩም ሰዎች ከሕፃናት ሰውነት ይልቅ ስንፍናን ያበዛሉ። 15መሥራት የማይቻላቸው፥ በዐይናቸው ማየት፥ ባፍንጫቸው ነፋስን ማሽተት፥ በጆሮአቸውም መስማት፥ በእጆቻቸው ጣቶች መዳሰስ የማይቻላቸው፥ እግሮቻቸውም ከመሄድ የቦዘኑ የአሕዛብን ጣዖቶች አማልክት አድርገው ዐስበዋልና። 16ሰው ሠርትዋቸዋልና፥ መንፈስ የተከፈለውም ሰው ቀርፆአቸዋልና፥ ራሱን አስመስሎ አምላክን ይሠራ ዘንድ ለሰው አይቻለውምና። 17እርሱ መዋቲ ሲሆን በኀጢአት እጅ መዋቲን ይሠራል፥ እርሱ ሕያው ስለሆነ እነዚህ ግን ከቶ ሕያዋን ስላይደሉ ከጣዖቶቹ ይሻላልና። 18እንስሳዎችንም አማልክት ያደረጓቸው እነዚህ በስንፍና ያመልኳቸዋል፥ እነዚህን ግን በሕሊና ቢመዝኗቸው ከሌሎች አማልክት ይከፋሉ። 19ምኞትን የወደደም እንስሳትን በማየት ከእነርሱ በአንዱ ምኞቱን ፈጸመ፥ በአንዱም በደለ፥ የእግዚአብሔር ምስጋናና ክብር በዚህ ርቋልና።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 15: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ