መጽሐፈ ጥበብ 14
14
የጣዖት ከንቱነት
1ዳግመኛም ሰው በክፉ የባሕር ማዕበል መካከል ይሄድ ዘንድ ወድዶ በመርከብ ላይ በወጣ ጊዜ ከምትሸከመው ከመርከቢቱ፥ ከሚዋረደውና ከሚደክመው እንጨት ይለምናል። 2ያን ጣዖት ትርፍ በመውደድ ሠርቶታልና፥ ብልህም በብልሀቱ ሠርቶታልና። 3አብ ሆይ፥ ያንተ አመራር ግን ሁሉን ትሠራራለች፤ በባሕር ውስጥ መንገድን፥ በሞገድም መካከል ጽኑ መተላለፊያን ሰጥተሃልና። 4ወደ መርከብ በማውጣት፥ ዳግመኛም ያለ ጥበብ ሰውን በባሕር ላይ በማሳለፍ በእውነት ሁሉን ማዳን እንደሚቻልህ ታሳይ ዘንድ፥ 5የጥበብህ ሥራው ስንፍና እንዳይሆን ትወዳለህ፥ ስለዚህ ሰዎች ሰውነታቸውን በተናቀና በተዋረደ እንጨት ተማምነው በታላቅና በታናሽ መርከብ በሞገዱ መካከል ተሻግረው ይድናሉ።
6ቀድሞም ትዕቢተኞች ረዓይት#“ረዓይት” ግዙፋን ወፍራሞች ረዥሞች ማለት ነው። በጠፉ ጊዜ የዓለም ተስፋ በመርከብ ተጭኖና ተጠግቶ ዳነ፥ በእጅህም ተመርቶ የሰውን ዘርዕ ለዓለም አተረፈ። 7ይህ መርከብ ጽድቅ ይሠራበት ዘንድ ተባርኳልና። 8በእጅ የተሠራው ግን የሚጠፋ ሲሆን አምላክ ስለ ተባለ የተረገመ ነው፤ የሠራውም ይህን በመሥራቱ ርጉም ነው። 9በእግዚአብሔር ዘንድ ክፉና ክፋቱ በትክክል ተጠልተዋልና፥ 10የተሠራው ሥራ ከሠሪው ጋር ይፈረድበታልና። 11ስለዚህም በአሕዛብ ጣዖታት ምርመራ ይደረጋል። ፍጥረትን ለማጥፋት ለሰዎችም ነፍሳት መሰናክል፥ ለአላዋቂዎች ሰዎች እግሮችም ወጥመድ ሆኖ ተሠርትዋልና፥
ጣዖትን ማምለክ የዝሙት መጀመሪያ ስለ መሆኑ
12የዝሙት መጀመሪያዋ ጣዖትን የመሥራት ዐሳብ ነውና፥ እርሱንም ማግኘት የሕይወት ጥፋት ነው። 13ከጥንት ጀምሮ አልነበረምና ለዘለዓለሙም አይኖርምና። 14ተነጥቀው የመሄዳቸውን ፍጻሜ የሚያፋጥን ስለሆነ በከንቱ ሰው ምክንያት ጣዖት ወደዚህ ዓለም ገባ። ከዚህም በኋላ ጣዖት መሥራትን ዐሰቡ። 15ልጁ ሕፃን ሳለ ፈጥኖ በሞት ስለ ተነጠቀ አባቱ ላንድ ልጁ ይጨነቅና ያለቅስ ነበርና፥ ቀድሞ ለሞተው ልጁ ምስል ሠራለት፥ ዛሬ ግን እንደ አምላክ አድርገው አከበሩት። ለኀጢአት የተገዙ ሰዎችም በስውር በዓል አደረጉለት፥ የምሥጢር መሥዋዕትንም ሠዉለት። 16ከዚህ በኋላ በዘመን መራቅ የበደልና የዝንጋዔ ልማድ ሥርዐት ሆኖ ተያዘ፥ እንደ ሕግም አድርገው ጠበቁት፥ በክፉዎች መኳንንት ትእዛዝም ጣዖታትን አመለኳቸው። 17በሩቅ ስለሚኖሩ ፊት ለፊት ሊያከብሯቸው የማይቻላቸውን ሰዎች ቅርፁ በሩቅ ያለ መልካቸውን ቀረፁ፥ በእነርሱ ዘንድ ክቡር ለሚሆን ለንጉሡም ግልጥ የሆነ ምስል ሠሩለት። የሌለውንም እንዳለ አድርገው በትጋት ይለምናሉ። 18ስሕተታቸውንም ያላወቁ ሰዎች በአምልኮታቸው ጸኑ። የጥበበኛውንም ክብር ወደ ጣዖት አምልኮ መለሱ። 19ዳግመኛ ገዥውን ንጉሥ አድልቶ ደስ ያሰኘው ዘንድ የሚወድ አለ። ባማረና በተሻለ ሁኔታ ምስሉን ለመሥራት ተራቅቆአልና። 20በሥራውም መልክ ማማር ደስ ስላላቸው ብዙ ሰዎች በዚህ ተሳቡ፥ ከጥቂት ቀን አስቀድሞ በትንሽ ክብር የነበረ ሰውንም ዛሬ እንደ አምላክ አደረጉት። 21በችግር ወይም በግድ ሰው ሁሉ ተገዝትዋልና ይህ ለሰው መሰናክልን ሆነ፤ ከእነርሱ ጋር አንድነት የሌለውን የፈጣሪን ስም ለሚጠቀሙባቸው ለድንጋይና እንጨት አድርገውታልና።
የአምልኮ ጣዖት ውጤት
22ዳግመኛም እግዚአብሔርን ካለማወቃቸው የተነሣ ስሕተታቸው አልበቃቸውም፥ ነገር ግን በታላቅ ሰልፍ ሳሉ በስንፍናቸው ይኖራሉ። ይህን ያህል ክፉ የሆነውንም ታላቅ አደረጉ፥ ሰላም ብለውም ጠሩት። 23ልጆቻቸውን የሚሠዉ አሉና፤ የተሰወረ ምሥጢርንም ያደርጋሉ፥ በልዩ ሥርዐትም እየተቅበዘበዙ ያስባሉ። 24ሕጋቸውንና ጋብቻቸውን አልጠበቁም፤ ነገር ግን ባልንጀራ ባልንጀራውን ይገድለዋል፤ ያም ባይሆን ያባብለዋል፥ በሽተኛም ያደርገው ዘንድ ተስፋ ይሰጠዋል። 25ሥራዎቻቸው ሁሉ ደም ከማፍሰስና ነፍስ ከመግደል ጋር፥ ከመስረቅም ጋር፥ ከሐሰትና ከጥፋት፥ ምስጋናንም ከማጕደል ጋር፥ ካለማመንም ጋር፥ ከመሐላና በጎውን ሰው ከማወክ ጋር፥ 26ዋጋን ካለማሰብ ጋር፥ ሰውነትን ከማስተዳደፍ ጋር፥ ፍጥረትንም ከመለወጥ ጋር፥ የጋብቻን ሥርዐት ከማፍረስ ጋር፥ ከምንዝርና ከርኵሰት ጋር፥ የተቀላቀለ ነው። 27ስም የሌላቸው ጣዖቶችን ማምለክ የክፋት ሁሉ መጀመሪያ ነውና፥ የፍጻሜውም ምክንያት ነውና። 28የሚያመልኳቸው ሰዎች እንደ እነዚህ ደስ ቢላቸው አእምሮአቸውን ያጣሉና። ያም ባይሆን በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፥ ያም ባይሆን ይሙት በቃውን ያድናሉ፥ ያም ባይሆን ፈጥነው ይምላሉ። 29ቃልና ዕውቀት ያላቸው እነዚህ ሁሉን እንደሚያውቅ እንደ ፈጣሪ አድርገው ነፍስ የሌለው ሐሰተኛና ድዳ ጣዖትን ይታመናሉ፥ ቢምሉም እንደሚፈረድባቸው አያስቡም። 30እውነተኛ ፍርድ በአንድነት ያገኛቸዋል፥ ጣዖቱን በተመለከቱ ጊዜ በእግዚአብሔር ክፉ ነገርን ዐስበዋልና፥ የፈጣሪን እውነት አቃልለው በግፍና በሐሰት ምለውበታልና። 31በኀጢአታቸው የተፈረደባቸውን ፍርድ ለማስተላለፍ ነው እንጂ ኀይሉን ይገልጥብናል ሲሉ የማሉ አይደለምና፤ እንግዲህ ሁልጊዜ ሰውን በሚበድሉ ሰዎች ወንጀል ላይ ፍርድ ትምጣባቸው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 14: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ