መጽሐፈ ጥበብ 13
13
የጣዖት አምልኮ ከንቱነት
1እግዚአብሔርን የማወቅ ጕድለት በልቡናቸው ያለባቸው ሰዎች ሁሉ በእውነት ከንቱ ናቸውና፥ በሚታዩ መልካም ነገሮች ያለውን ያውቁ ዘንድ ተሳናቸው፥ ሥራውንም እያዩ ሠሪውን አላወቁትም። 2ነገር ግን እሳትንና ፈጥኖ የሚነፍሰውን ነፋስ፥ ወይም የከዋክብትን ዙረት፥ ወይም የውኃውን ሞገድ፥ ወይም የሰማይ ብርሃናትን ዓለሙን የሚያስተዳድሩ አማልክት አስመሰሏቸው። 3በመልካቸው ውበት ደስ ባላቸው ጊዜ እነዚህን ፍጥረታት አማልክት ካደረጓቸው፥ ውበትን የፈጠረ እርሱ ይህን ፍጥረት ፈጥሯልና የእነዚህ ጌታ ፈጽሞ እንደሚበልጥ ይወቁ። 4ከኀይላቸውና ከሥራቸው የተነሣ ከተደነቁስ የፈጠራቸው እርሱ ፈጽሞ ኀያል እንደ ሆነ ያስተውሉ። 5ፍጡራን የፍጥረታትን ውበት ታላቅነት አይተው የፍጥረታትን ፈጣሪ በእርሱ መስለውታል። 6ነገር ግን ከዚህ ጋራ ዳግመኛ አምላክን እየፈለጉት፥ ያገኙትም ዘንድ እየወደዱ ቢሳሳቱ፥ በእነርሱ ላይ የሚኖረው ነቀፋ ጥቂት አይደለም። 7ወደ ሥራው ተመልሰው በፈለጉት ነበርና፥ እነርሱ ግን በማየት አበቁ፥ የሚታዩት መልካሞች ናቸውና። 8ዳግመኛም ምክንያታቸው ብዙ ነው። 9ዓለምን መረዳት እስኪገባቸው ድረስ ይመለከቱ ዘንድ ይህን ያህል ከተቻላቸው የእነዚህን ጌታ ፈጥነው ያገኙት ዘንድ እንዴት አልቻሉም? 10ከወርቅና ከብር በጥበብ የተሠሩ የሰው እጅ ሥራዎችን፥ የእንስሳ ምሳሌን፥ ወይም የማይጠቅም የጥንት የእጅ ሥራ ድንጋይን አማልክት ብለው የሚጠሩ እነዚህ ጐስቋሎች ናቸው፥ ተስፋቸውም በሞቱ ነገሮች ላይ ነው። 11የሚታየውንና የሚወዛወዘውን እንጨት የሚጠርብ ጠራቢ ቢኖር መልካም ሆኖ የበቀለውን እንጨት ይቈርጣል፥ ቅርፊቱን ሁሉ በጥበብ ይጠርባል፤ መልካም አድርጎም ይሠራዋል፥ ለኑሮ አገልግሎትም የሚጠቅም ዕቃ አድርጎ ይሠራዋል። 12ምግቡንም ለማዘጋጀት የሥራውን ጠረባ ከፈጸመ በኋላ ይጠግባል። 13ዳግመኛም ለምንም ከማይጠቅም እንጨት የተረፈ ጕማጁን፥ ጕጣሙንና ጫፉ ሁሉ የጠመመውን እንጨት ወስዶ ሥራውን በማስተንተን ይጠርበዋል፥ ከዚህም በኋላ በቦዘነበት ቀን በሰው መልክ መስሎ ይቀርፀዋል። 14ወይም ከንቱ በሚሆን በእንስሳ ምስል ይሠራዋል፥ በቀይ ቀለምም ይቀባዋል፤ በጣቱም ቀለም አግብቶ ቀይ ያደርገዋል። ያለበትንም ጕድለት ይሞላል። 15ለእርሱም የሚገባ የውቅር ቤት ይሠራል፤ በሠራለት ቦታም ያኖረዋል፥ ከግድግዳውም አስጠግቶ በብረት ይቸነክረዋል። 16ምስል ነውና፥ የሚረዳውንም ይፈልጋልና ራሱን መርዳት እንደማይችል ዐውቆ እንዳይወድቅበት ይጠነቀቃል። 17ከዚህም በኋላ ስለ ገንዘቡና ስለ ሚስቱ፥ ስለ ልጆቹም ወደ እርሱ ይለምናል፤ ነፍስ ከሌለው ከጣዖቱ ጋርም ሲነጋገር አያፍርም። 18ስለ ፈውስ ወደ በሽተኛው ይለምናል፥ ስለ ሕይወትም መዋቲውን ይለምናል፥ ስለ ርዳታም መርዳት ወደማይችለው ደካማ ይማልዳል። 19ስለ መንገድም ነገር ይንቀሳቀስ ዘንድ ወደማይቻለውና አንዲት ርምጃን ወደማይራመደው ይለምናል። ስለ ብልጽግናና ስለ ሥራም፥ ስለ ማግኘትም፥ የእጅን ሥራም ስለ ማቅናት እጆቹ ምንም ወደማይሠሩ ይለምናል፥ ኀይልንና ሥራ ማፍጠንንም ይሰጠው ዘንድ ምንም ኀይል ከሌለው ከእርሱ ይፈልጋል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 13: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ