መዝሙረ ዳዊት 88
88
የይዝራኤላዊው የኤታን ትምህርት።
1አቤቱ፥ ምሕረትህን ለዘለዓለም እዘምራለሁ።
ጽድቅህንም በአፌ ለልጅ ልጅ እናገራለሁ።
2“ምሕረትን ለዘለዓለም አንጻለሁ” ብለሃልና፥
ጽድቅህ በሰማይ ጸና።
3ከመረጥኋቸው#ዕብ. “ከመረጥሁት” ይላል። ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ፥
ለባሪያዬም ለዳዊት ማልሁ፥
4ዘርህን ለዘለዓለም አዘጋጃለሁ፥
ዙፋንህንም ለልጅ ልጅ አጸናለሁ።
5አቤቱ፥ ሰማያት ክብርህን#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ተአምራትህን” ይላል።
ጽድቅህንም ደግሞ በቅዱሳን ማኅበር ያመሰግናሉ።
6እግዚአብሔርን በደመናት#ዕብ. “በሰማይ” ይላል። ማን ይተካከለዋል?
ከአማልክትስ ልጆች እግዚአብሔርን ማን ይመስለዋል?
7እግዚአብሔር በቅዱሳን ምክር ክቡር ነው፤
በዙሪያው ባሉት ሁሉ ላይ ታላቅና ግሩም ነው።
8አቤቱ የኀያላን አምላክ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?
አቤቱ፥ አንተ ብርቱ ነህ፥ እውነትም ይከብብሃል።
9የባሕርን ኀይል አንተ ትገዛለህ፥
የሞገዱንም መናወጥ አንተ ዝም ታሰኘዋለህ።
10አንተ ትዕቢተኛውን እንደ ተገደለ አዋረድኸው፥
በኀይልህም ክንድ ጠላቶችህን በተንሃቸው።
11ሰማያት የአንተ ናቸው፥ ምድርም የአንተ ናት፤
ዓለምን በሙሉ አንተ መሠረትህ።
12ባሕርንና መስዕን አንተ ፈጠርህ፤
ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል።
ስምህንም ያመሰግናሉ።
13ክንድህ ከኀይልህ ጋር ነው፤
እጅህ በረታች፥ ቀኝህም ከፍ ከፍ አለች።
14የዙፋንህ መሠረት ፍትሕና ርትዕ ነው፤
ምሕረትና እውነት በፊትህ ይሄዳሉ።
15እልልታን የሚያውቅ ሕዝብ ብፁዕ ነው፤
አቤቱ፥ በፊትህ ብርሃን ይሄዳሉ።
16በስምህ ቀኑን ሁሉ ደስ ይላቸዋል፥
በጽድቅህም ከፍ ከፍ ይላሉ፤
17የኀይላቸው ትምክሕት አንተ ነህና፥
በይቅርታህም ቀንዳችን ከፍ ከፍ ይላልና።
18ረድኤታችን ከእግዚአብሔር ነውና።
ንጉሣችንም የእስራኤል ቅዱስ ነውና።
19በዚያ ጊዜ ለልጆችህ በራእይ ተናገርህ፥
እንዲህም አልህ፥ “ረድኤትን በኀይል ላይ አኖርሁ፤
ከሕዝቤ የመረጥሁትን ከፍ ከፍ አደረግሁ።
20ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፥
የተቀደሰ ዘይትንም ቀባሁት።
21እጄም ትረዳዋለች፥
ክንዴም ታጸናዋለች፥
22ጠላት በእርሱ ላይ አይጠቀምም፥
የዐመፃ ልጅም መከራ አይጨምርበትም።
23ጠላቶቹን ከፊቱ አጠፋለሁ፥
የሚጠሉትንም አዋርዳቸዋለሁ።
24እውነቴና ምሕረቴም ከእርሱ ጋር ነው፥
በስሜም ቀንዱ ከፍ ከፍ ይላል።
25እጁን በባሕር ላይ
ቀኙንም በወንዞች ላይ አኖራለሁ።
26እርሱ “አባቴ አንተ ነህ፥
አምላኬ ረዳቴና መድኃኒቴም#ዕብ. “አምላኬ የመድኀኒቴ መጠጊያ” ይላል። ነህ” ይላል።
27እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለሁ፥
ከምድር ነገሥታትም ከፍ ይላል።
28ለዘለዓለም ይቅርታዬን ለእርሱ እጠብቃለሁ፥
ለኪዳኔም እርሱ የታመነ ነው።
29ዘሩንም ለዓለምና ለዘለዓለም፥
ዙፋኑንም እንደ ሰማይ ዘመን አደርጋለሁ።
30“ልጆቹ ግን ሕጌን ቢተዉ፥
በፍርዴም ባይሄዱ፤
31ሥርዐቴንም ቢያረክሱ፥
ትእዛዜንም ባይጠብቁ፤
32ኀጢአታቸውን በበትር፥
በደላቸውንም በመቅሠፍት እጐበኛታለሁ።
33ይቅርታዬን ግን ከእርሱ አላርቅም፥
በእውነቴም አልበድልም፤
34ኪዳኔንም አላረክስም፥
ከአፌም የወጣውን አልለውጥም።
35ዳዊትን እንዳልዋሸው
አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልሁ።
36ዘሩ ለዘለዓለም፥
ዙፋኑም በፊቴ እንደ ፀሐይ ይኖራል።
37ለዘለዓለም እንደ ጨረቃ ይጸናል።
ምስክርነቱም በሰማይ የታመነ ነው።”
38አንተ ግን ናቅኸው፥ ጣልኸውም፥
የቀባኸውንም አቃለልኸው።
39የባሪያህንም ኪዳን አፈረስህ፥
መቅደሱንም በምድር አረከስህ።
40ቅጥሩን ሁሉ አፈራረስህ፥
አምባዎቹንም የሚያስፈሩ አደረግህ።
41መንገድ አላፊም ሁሉ ተናጠቀው፥
ለጎረቤቶቹም ስድብ ሆነ።
42የጠላቶቹንም ቀኝ ከፍ ከፍ አደረግህ።
ጠላቶቹንም ሁሉ ደስ አሰኘህ።
43የሰይፉንም ረድኤት መለስህ፥
በሰልፍም ውስጥ አልደገፍኸውም።
44ከንጽሕናውም ሻርኸው፥
ዙፋኑንም በምድር ጣልህ።
45የዙፋኑንም ዘመን አሣነስህ፥
በላዩም እፍረትን ጨመርህ።
46አቤቱ፥ እስከ መቼ ለዘለዓለም ፊትህን ትመልሳለህ?
እስከ መቼስ ቍጣህ እንደ እሳት ይነድዳል?
47ኀይሌ ምን እንደ ሆነ ዐስብ፤
በውኑ የሰውን ልጅ ሁሉ ለከንቱ ፈጠርኸውን?
48ሕያው ሆኖ የሚኖር፥ ሞትንስ የማያይ ሰው ማን ነው?
ነፍሱንስ ከሲኦል እጅ የሚያድናት ማን ነው?
49አቤቱ፥ የቀድሞ ይቅርታህ ወዴት ነው?
ለባሪያህ ለዳዊት በእውነት የማልህ፥
50አቤቱ፦ ባሪያዎችህን የሰደቡአቸውን ስድብ፥
በብብቴ ብዙ አሕዛብን የተቀበልሁትን፥
51አቤቱ፥ ጠላቶችህ የሰደቡትን
የቀባኸውን ዘመን#ግእዝ “ዕቤራተ መሲሕከ” ይላል። የሰደቡትን ስድብ ዐስብ።
52እግዚአብሔር ለዘለዓለም ይመስገን። ይሁን ይሁን።
Currently Selected:
መዝሙረ ዳዊት 88: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ