መዝሙረ ዳዊት 106
106
ሃሌ ሉያ።
1እግዚአብሔርን አመስግኑ፤
ቸር ነውና፥ ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና።
2እግዚአብሔር ያዳናቸው፥
ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳናቸው ይናገሩ።
3ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከመስዕና ከባሕር፥
ከየሀገሩ ሰበሰባቸው።
4ውኃ በሌለበት ምድረ በዳ ተቅበዘበዙ፤
የሚኖሩበትንም ከተማ መንገድ አላገኙም።
5ተራቡ፥ ተጠሙም፥
ሰውነታቸውም በላያቸው አለቀች።
6በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥
ከመከራቸውም አዳናቸው፤
7ወደሚኖሩበትም ሀገር ይሄዱ ዘንድ
የቀና መንገድን መራቸው።
8የእግዚአብሔርን ምሕረት
ለሰው ልጆችም ያደረገውን ድንቁን ንገሩ፤
9የተራበችን ነፍስ አጥግቦአልና፥
የተራቈተችንም ነፍስ በበረከት ሞልቶአልና።
10በጨለማና በሞትም ጥላ የተቀመጡ፥
በችግር በብረትም የታሰሩ፥
11የእግዚአብሔርን ቃል ስለ አማረሩ፥
የልዑልንም ምክር ስለ አስቈጡ፥
12ልባቸው በመከራ ደከመ፤
ታመሙ የሚረዳቸውንም#ግእዝ “የሚቀብራቸው” ይላል። አጡ።
13በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥
ከመከራቸውም አዳናቸው።
14ከጨለማና ከሞት ጥላ አወጣቸው፥
እግር ብረታቸውንም ሰበረ።
15የእግዚአብሔርን ምሕረት
ለሰው ልጆችም ያደረገውን ድንቁን ንገሩ፤
16የናሱን ደጆች ሰብሮአልና፥
የብረቱንም መወርወሪያ ቀጥቅጦአልና።
17ከበደላቸው ጎዳና ተቀበላቸው፥#ዕብ. “ስለ ዐመፃቸው ሰነፉ” ይላል።
በኀጢአታቸው ተሠቃይተዋልና።
18ሰውነታቸውም መብልን ሁሉ ተጸየፈች፥
ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ።
19በተጨነቁም ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥
ከመከራቸውም አዳናቸው።
20ቃሉን ልኮ ፈወሳቸው፥
ከጥፋታቸውም አዳናቸው።
21የእግዚአብሔርን ምሕረት
ለሰው ልጆችም ያደረገውን ድንቁን ንገሩ፤
22የምስጋና መሥዋዕትም ይሠዉለት፥
በደስታም ሥራውን ይንገሩ።
23በመርከቦች ወደ ባሕር የሚወርዱ፥
በብዙ ውኃ ሥራቸውን የሚሠሩ፥
24እነርሱ የእግዚአብሔርን ሥራ፥
በጥልቅም ያለችውን ድንቁን ዐወቁ።
25ተናገረ፥ ዐውሎ ነፋስም ተነሣ፥
ሞገድም ከፍ ከፍ አለ።
26ወደ ሰማይ ይወጣሉ፥ ወደ ጥልቅም ይወርዳሉ፤
ሰውነታቸውም በመከራ ቀለጠች።
27ደነገጡ፥ እንደ ሰካራምም ተንገዳገዱ፥
ጥበባቸውም ሁሉ ተዋጠ።
28በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥
ከመከራቸውም አዳናቸው።
29ዐውሎ ነፋሱንም ጸጥ አደረገ፥
ባሕሩም ዝም አለ።
30ማዕበሉም ዝም አለ፥ አርፈዋልና ደስ አላቸው።
ወደ ፈለጉትም ወደብ መራቸው።
31የእግዚአብሔርን ምሕረቱን
ለሰው ልጆችም ድንቁን ንገሩ።
32በአሕዛብ ጉባኤ ከፍ ከፍ ያደርጉታል፥
በሽማግሌዎችም ሸንጎ ያመሰግኑታል።
33ወንዞችን ምድረ በዳ አደረገ፥
የውኃውንም ምንጮች ደረቅ አደረጋቸው፤
34በተቀመጡባት ሰዎች ክፋት
ፍሬያማዋን ምድር ጨው አደረጋት።
35ምድረ በዳውን ለውኃ መውረጃ፥
ደረቁንም ምድር የውኃ ምንጮች አደረገ።
36በዚያም ራብተኞችን አስቀመጠ፥
የሚኖሩባቸውንም ከተሞች ሠሩ።
37እርሻዎችንም ዘሩ፥ ወይኖችንም ተከሉ፥
የእህልንም ሰብል አደረጉ።
38ባረካቸውም፥ እጅግም በዙ፤
እንስሶቻቸውንም አላሳነሰባቸውም።
39እነርሱ በክፉ መከራና በጭንቀት ተሠቃዩ፥ እያነሱም ሄዱ፤
40በአለቆችም ላይ ኀሣር ፈሰሰ፥
መንገድም በሌለበት በምድረ በዳ አሳታቸው።
41ችግረኛንም በችግሩ ረዳው፤
እንደ ሀገር በጎች አደረገው።#ዕብ. “እንደ በጎች መንጋ” ይላል።
42ቅኖች ይዩ፥ ደስም ይበላቸው፤
ዐመፃም ሁሉ አፍዋን ትዘጋለች።
43ይህን የሚጠብቅ ጥበበኛ ማን ነው?
እግዚአብሔር ይቅር ባይ እንደ ሆነ ያውቃል።
Currently Selected:
መዝሙረ ዳዊት 106: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ