ኦሪት ዘኍልቍ 13
13
ወደ ከነዓን የተላኩ ጕበኞች
(ዘዳ. 1፥19-33)
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“ይገዙአት ዘንድ እኔ ለእስራኤል ልጆች የምሰጣትን የከነዓንን ምድር የሚሰልሉ ሰዎችን ላክ፤ ከአባቶች ቤት ከእያንዳንዱ ነገድ ሁሉ በመካከላቸው አለቃ የሆነ አንድ አንድ ሰው ትልካላችሁ።” 3ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ ከፋራን ምድረ በዳ ላካቸው፤ እነርሱም ሁሉ የእስራኤል ልጆች አለቆች ነበሩ። 4ስማቸውም ይህ ነበረ፤ ከሮቤል ነገድ የዝኩር ልጅ ሰሙኤል፤ 5ከስምዖን ነገድ የሱሬ ልጅ ሰፈጥ ፤ 6ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፤ 7ከይሳኮር ነገድ የዮሴፍ ልጅ ኢጋል፤ 8ከኤፍሬም ነገድ የነዌ ልጅ አውሴ፤ 9ከብንያም ነገድ የራፋ ልጅ ፈልጢ፤ 10ከዛብሎን ነገድ የሶዲ ልጅ ጉዲኤል፤ 11ከዮሴፍ ነገድ ከምናሴ ልጆች የሱሲ ልጅ ጋዲ፤ 12ከዳን ነገድ የገማሊ ልጅ ዓሚሄል፤ 13ከአሴር ነገድ የሚካኤል ልጅ ሳቱር፤ 14ከንፍታሌም ነገድ የያቢ ልጅ ናቢ፤ 15ከጋድ ነገድ የማኪ ልጅ ጉዲኤል። 16ምድሪቱን ይሰልሉ ዘንድ ሙሴ የላካቸው ሰዎች ስሞች እነዚህ ናቸው። ሙሴም የነዌን ልጅ አውሴን ኢያሱ ብሎ ጠራው።
17ሙሴም የከነዓንን ምድር ይሰልሉ ዘንድ ላካቸው፤ አላቸውም፥ “ከዚህ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ፥ ወደ ተራሮችም ውጡ። 18ምድሪቱንም እንዴት እንደ ሆነች፥ በእርስዋም የሚኖሩ ሰዎች ብርቱዎች ወይም ደካሞች፥ ጥቂቶች ወይም ብዙዎች እንደ ሆኑ፥ 19የሚኖሩባትም ምድር መልካም ወይም ክፉ፥ የሚኖሩባቸውም ከተሞች ቅጥር ያላቸው ወይም የሌላቸው እንደ ሆኑ፥ 20ምድሪቱም ለም ወይም ጠፍ፥ ዛፍ ያለባት ወይም የሌለባት እንደ ሆነች አይታችሁ፥ ከምድሪቱ ፍሬ አምጡ፤” ወራቱም ወይኑ አስቀድሞ ፍሬ የሚያፈራበት ነበረ።
21ወጡም፤ ምድሪቱንም ከጺን ምድረ በዳ በኤማት ዳር እስካለችው እስከ ረአብ ድረስ ሰለሉ። 22ወደ ምድረ በዳም ወጡ፤ ወደ ኬብሮንም ደረሱ፤ በዚያም የዔናቅ ዘሮች አኪማን፥ ሴሲ፥ ተላሚ ነበሩ። ኬብሮንም በግብፅ ካለችው ከጣኔዎስ ከተማ በፊት ሰባት ዓመታት ተሠርታ ነበር። 23ወደ ወይን ዘለላ ሸለቆም መጡ፤ አዩኣትም፤ ከዚያም ከወይኑ አንድ ዘለላ የነበረበትን አረግ ቈረጡ፤ በመሎጊያም ተሸከሙት፤ ደግሞም ከሮማኑ ከበለሱም አመጡ። 24የእስራኤል ልጆች ከዚያ ስለ ቈረጡት ዘለላ የዚያን ስፍራ ስም የወይን ዘለላ ሸለቆ ብለው ጠሩት።
የጕበኞች ዘገባ አቀራረብ
25ምድሪቱንም ሰልለው ከአርባ ቀን በኋላ ከዚያ ተመለሱ። 26ገሥግሠውም በቃዴስ ፋራን ምድረ በዳ ወዳሉት ወደ ሙሴና ወደ አሮን፥ ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ደረሱ፤ ወሬውንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ነገሩአቸው፤ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው። 27እንዲህም ብለው ነገሩት፥ “ወደ ላክኸን ምድር ደረስን፤ እርስዋም ወተትና ማር ታፈስሳለች፤ ፍሬዋም ይህ ነው። 28ነገር ግን በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ኀያላን ናቸው፤ ከተሞቻቸውም የተመሸጉ፥ እጅግም የጸኑ ታላላቅ ናቸው። 29ደግሞም በዚያ የዔናቅን ዘሮች አየን፤ በአዜብ በኩል ዐማሌቅ ተቀምጦአል፤ በተራሮችዋም ኬጤዎናዊውና ኤዌዎናዊውም፥ ኢያቡሴዎናዊው፥ አሞሬዎናዊውም ተቀምጠዋል፤ ከነዓናዊውም በባሕር ዳርና በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ተቀምጦአል።”
30ካሌብም ሕዝቡን በሙሴ ፊት ዝም አሰኘና፥ “አይደለም! ማሸነፍን እንችላለንና እንውጣ፤ እንውረሳት” አለ። 31ከእርሱ ጋር የወጡ ሰዎች ግን ፥ “በኀይል ከእኛ ይበረታሉና በዚህ ሕዝብ ላይ መውጣት አንችልም” አሉ። 32ስለ ሰለሉአትም ምድር ለእስራኤል ልጆች እያወሩ፥ “እኛ ዞረን የሰለልናት ምድር የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ምድር ናት፤ በእርስዋም ዘንድ ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ረጃጅም ሰዎች ናቸው፤ 33በዚያም ግዙፋን#ዕብ. “ከኔፊሊም ወገን የሆኑትን ኔፊሊም የኤናቅን ልጆች” ይላል። የሆኑትን አየን፤ እኛም በእነርሱ ፊት#ዕብ. “በዐይናቸው ግምት እንደ አንበጣዎች ነበርን ፤ ደግሞም እኛ በዐይናቸው ዘንድ እንዲሁ ነበርን አሉ” ይላል። እንደ አንበጣዎች ሆን፤ እንዲሁም በፊታቸው ነበርን፤” እያሉ የሰለሉአትን ምድር ለእስራኤል ልጆች አስፈሪ አደረጓት።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 13: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ