ኦሪት ዘኍልቍ 12
12
አሮንና ማርያም ሙሴን እንደ ተቃወሙት
1ሙሴም ኢትዮጵያዊቱን ሴት አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያዊቱ ሴት ምክንያት ማርያምና አሮን አሙት። 2እነርሱም፥ “በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን?” አሉ፤ እግዚአብሔርም ሰማ። 3ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ የዋህ ሰው ነበረ።
4እግዚአብሔርም ወዲያው ሙሴንና አሮንን ማርያምንም፥ “ሦስታችሁ ወደ ምስክሩ ድንኳን ኑ ብሎ ተናገረ፤ ሦስቱም ወደ ምስክሩ ድንኳን ወጡ። 5እግዚአብሔርም በደመና ዐምድ ወረደ፤ በምስክሩም ድንኳን ደጃፍ ቆመ፤ አሮንንና ማርያምንም ጠራቸው፤ ሁለቱም ወጡ። 6እርሱም፥ “ቃሌን ስሙ፤ በመካከላችሁ ለእግዚአብሔር ነቢይ የሆነ ቢኖር በራእይ እገለጥለታለሁ፤ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ። 7አገልጋዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው። 8እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፤ በስውርም አይደለም፤ የእግዚአብሔርንም ክብር ያያል፤ አገልጋዬ ሙሴን ማማትን ስለ ምን አልፈራችሁም?” አለ።
9የእግዚአብሔርም ቍጣ በእነርሱ ላይ ወረደ፤ እርሱም ሄደ። 10ደመናውም ከድንኳኑ ተነሣ፤ እነሆም፥ ማርያም ለምጻም ሆነች፤ እንደ በረዶም ነጭ ሆነች፤ አሮንም ማርያምን ተመለከተ፤ እነሆም፥ ለምጻም ሆና ነበር። 11አሮንም ሙሴን፥ “ጌታዬ ሆይ፥ ስንፍና አድርገናልና፥ በድለንማልና እባክህ፥ ኀጢአት አታድርግብን። 12ከእናቱ ማኅፀን ሞቶ እንደ ተወለደ፥ ከተበላ ግማሽ ሥጋዋ ጋር ለሞት አትተዋት።” 13ሙሴም ወደ እግዚአብሔር እየጮኸ፥ “አቤቱ፥ እባክህ፥ አድናት” አለው። 14እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “አባቷ ምራቁን በፊቷ ቢተፋባት ስንኳ ሰባት ቀን ታፍር ዘንድ ይገባት ነበር፤ ሰባት ቀን ከሰፈር ውጭ ተዘግታ ትቀመጥ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ትመለስ” አለው። 15ማርያምም ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን ተለይታ ተቀመጠች፤ ማርያምም እስክትነጻ ድረስ ሕዝቡ አልተጓዙም።
16ከዚያም በኋላ ሕዝቡ ከአሴሮት ተጓዙ፤ በፋራንም ምድረ በዳ ሰፈሩ።#ግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 12 በቍ. 15 ያበቃል።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 12: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ