ኦሪት ዘኍልቍ 11
11
የቃጠሎው ቦታ
1ሕዝቡም በክፋት በእግዚአብሔር ፊት አጕረመረሙ፤ እግዚአብሔርም ሰምቶ ተቈጣ፤ እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ በእነርሱ ላይ ነደደች፤ ከሰፈሩም አንዱን ወገን በላች። 2ሕዝቡም ወደ ሙሴ ጮኹ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እሳቲቱም ጠፋች። 3ከእግዚአብሔርም ዘንድ በእነርሱ ላይ እሳት ስለ ነደደች የዚያ ስፍራ ስም “መካነ ውዕየት”#ዕብ. “ተቤራ” ይላል። ተብሎ ተጠራ።
ለእስራኤል ከሰማይ መና እንደ ወረደላቸው
4ከእነርሱም ጋር የተቀላቀሉ ሕዝብ እጅግ ጐመጁ፤ የእስራኤልም ልጆች ተቀምጠው እንዲህ እያሉ አለቀሱ፥ “ሥጋ ማን ያበላናል? 5በግብፅ ያለ ዋጋ እንበላው የነበረውን ዓሣ፥ ዳቦውንም፥ በጢኹንም፥ ኩራቱንም፥ ቀዩንም ሽንኩርት፥ ነጩንም ሽንኩርት ቍንዶ በርበሬውንም እናስባለን። 6አሁን ግን ሰውነታችን ደረቀች፤ ዐይናችንም ከዚህ መና በቀር ምንም አታይም” አሉ። 7መናውም እንደ ድንብላል ዘር ነበረ፤ መልኩም እንደ በረድ ነጭ ነበር። 8ሕዝቡም እየዞሩ ይለቅሙ ነበር፤ በወፍጮም ይፈጩት፥ ወይም በሙቀጫ ይወቅጡት፥ በምንቸትም ይቀቅሉት ነበር፤ እንጎቻም ያደርጉት ነበር፤ ጣዕሙም በዘይት እንደ ተለወሰ እንጎቻ ነበረ። 9ሌሊትም ጠል በሰፈሩ ላይ በወረደ ጊዜ መናው በላዩ ይወርድ ነበር።
10ሙሴም እያንዳንዳቸው በየወገናቸው በድንኳኑ ደጃፍ፥ ሲያለቅሱ ሰማ፤ እግዚአብሔርም እጅግ ተቈጣ፤ ነገሩም በሙሴ ፊት ክፉ ሆነ። 11ሙሴም እግዚአብሔርን አለው፥ “ለምን በአገልጋይህ ላይ ክፉ አደረግህ? ለምንስ በፊትህ ሞገስን አላገኘሁም? ለምንስ የዚህን ሁሉ ሕዝብ ሸክም በእኔ ላይ አደረግህ? 12አንተ ለአባቶቻቸው ወደ ማልህላቸው ምድር አደርሳቸው ዘንድ፦ ሞግዚት የሚጠባውን ልጅ እንድታቅፍ በብትህ እቀፋቸው የምትለኝ፥ በውኑ ይህን ሕዝብ ሁሉ እኔ ፀነስሁትን? ወይስ ወለድሁትን? 13በፊቴ ያለቅሳሉና፦ የምንበላውን ሥጋ ስጠን ይላሉና ለዚህ ሕዝብ ሁሉ የምሰጠው ሥጋ ከየት አለኝ? 14እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ብቻዬን ልሸከም አልችልም። 15እንዲህስ ከምታደርግብኝ፥ በፊትህ ይቅርታን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ በእኔ ላይ የሚሆነውን መከራ እንዳላይ፥ እባክህ፥ ፈጽሞ ግደለኝ።”
የሰብዓው ሊቃናት መመረጥ
16እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ከእስራኤል ሽማግሌዎች፥ ለሕዝቡ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ይሆኑ ዘንድ የምታውቃቸውን፥ ሰባ ሰዎች ሰብስብልኝ፤ ወደ ምስክሩም ድንኳን አምጣቸው፤ በዚያም ከአንተ ጋር አቁማቸው። 17እኔም እወርዳለሁ፤ በዚያም አነጋግርሃለሁ፤ በአንተ ካለውም መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርገዋለሁ፤ አንተም ብቻ እንዳትሸከም የሕዝቡን ሸክም ከአንተ ጋር ይሸከማሉ። 18ሕዝቡንም በላቸው፦ ሥጋ ማን ያበላናል? በግብፅ ደኅና ነበረልን እያላችሁ በእግዚአብሔር ፊት አልቅሳችኋልና ለነገ ተቀደሱ፤ ሥጋንም ትበላላችሁ፤ እግዚአብሔርም ሥጋን ይሰጣችኋል፤ ትበሉማላችሁ። 19አንድ ቀን፥ ወይም ሁለት ቀን፥ ወይም አምስት ቀን፥ ወይም ዐሥር ቀን ወይም ሃያ ቀን አትበሉም፤ 20ነገር ግን በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን ንቃችኋልና፥ በፊቱም፦ ለምን ከግብፅ አወጣኸን? ብላችሁ አልቅሳችኋልና በአፍንጫችሁ እስኪወጣ መርዝም እስኪሆንባችሁ ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ።” 21ሙሴም፥ “እኔ በመካከላቸው ያለሁ ሕዝብ ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ናቸው፤ አንተም፦ ሥጋን እሰጣቸዋለሁ፥ ወር ሙሉም ይበሉታል አልህ። 22የበሬና የበግ መንጋ ቢታረድ፥ የባሕር ዓሣ ሁሉ ቢሰበሰብ ይበቃቸዋልን?” አለ። 23እግዚአሔርም ሙሴን፥ “በውኑ የእግዚአብሔር እጅ አትችልምን? አሁን ቃሌ ይፈጸም ወይም አይፈጸም እንደ ሆነ እነሆ፥ አንተ ታያለህ” አለው።
24ሙሴም ወጣ፤ የእግዚአብሔርንም ቃሎች ለሕዝቡ ነገረ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችም ሰባውን ሰዎች ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። 25እግዚአብሔርም በደመናው ወረደ፤ ተናገረውም፤ በእርሱም ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አደረገ፤ መንፈሱም በላያቸው ባደረ ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልተጨመረላቸውም።
26ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በሰፈር ቀርተው ነበር፤ የአንዱም ስም ኤልዳድ የሁለተኛውም ሞዳድ ነበረ፤ መንፈስም ዐረፈባቸው፤ እነርሱም ከተጻፉት ጋር ነበሩ፤ ወደ ድንኳኑ ግን አልወጡም ነበር፤ በሰፈሩም ውስጥ ትንቢት ተናገሩ። 27አንድ ጐልማሳ ሰው እየሮጠ መጥቶ፥ “ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈር ትንቢት ይናገራሉ” ብሎ ለሙሴ ነገረው። 28የሙሴ ምርጥ ባለሟል የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፥ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ ፥ ከልክላቸው” አለው። 29ሙሴም “የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያሳድር አንተ ስለ እኔ ትቀናለህን?” አለው። 30ሙሴም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈር ተመለሰ።
ድርጭት እንደ ወረደላቸው
31ነፋስም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፤ ከባሕርም ድርጭቶችን አወጣ፤ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚህ፥ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚያ በሰፈሩ ላይ በተናቸው፤ በዚያም በሰፈሩ ዙሪያ ከፍታው ከምድር ወደ ላይ ሁለት ክንድ ነበረ። 32በዚያም ቀን ሁሉ፥ በሌሊትም ሁሉ፥ በነጋውም ሁሉ ሕዝቡ ተነሥተው ድርጭትን ሰበሰቡ፤ ከሁሉ ጥቂት የሰበሰበ ዐሥር የቆሮስ መስፈሪያ ያህል ሰበሰበ፤ በሰፈሩም ዙሪያ ሁሉ አስጥተው አደረቁት። 33ሥጋውም ገና በጥርሳቸው መካከል ሳለ ሳያኝኩትም፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን እጅግ ታላቅ በሆነ መቅሠፍት አጠፋቸው። 34የጐመጁ ሕዝብ በዚያ ተቀብረዋልና የዚያ ስፍራ ስም “መቃብረ ፍትወት” ተብሎ ተጠራ። 35ሕዝቡም ከመቃብረ ፍትወት ወደ አሴሮት ተጓዙ፤ በአሴሮትም ተቀመጡ።#በግእዙ ምዕ. 11 በቍ. 34 ያበቃል።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 11: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ