ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካና የቂጣ በዓል ነበረ። የካህናት አለቆችም ጻፎችም እንዴት አድርገው በተንኰል እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት ይፈልጉ ነበር። “የሕዝብ ሁከት እንዳይሆን በበዓል አይሁን፤” ይሉ ነበርና። እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በነበረ ጊዜ፥ በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ የናርዶስ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች፤ ብልቃጡንም ሰብራ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። አንዳንዶችም “ይህ የሽቶ ጥፋት ለምንድር ነው? ይህ ሽቶ ከሦስት መቶ ዲናር በሚበልጥ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና፤” ብለው በራሳቸው ይቈጡ ነበር፤ እርስዋንም ነቀፉአት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ “ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች። ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፤ በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም። የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል።” ከዐሥራ ሁለቱም አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። ሲሰሙም ደስ አላቸው፤ ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት። በሚመች ጊዜም እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንዲሰጠው ይፈልግ ነበር። የፋሲካን በግ በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ “ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ?” አሉት። ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ፤ እንዲህም አላቸው “ወደ ከተማ ሂዱ፤ ማድጋ ውኀ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤ተከተሉት። የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ ‘መምህሩ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል፤’ በሉት። እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤በዚያም አሰናዱልን።” ደቀ መዛሙርቱም ወጡ፤ ወደከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፤ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል፤” አለ። እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም መልሶ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር፤” አላቸው። ሲበሉም ኢየሱስ ኅብስትን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸውና “እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው፤” አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፤ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ። እርሱም “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው። እውነት እላችኋለሁ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም፤” አላቸው። መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።
የማርቆስ ወንጌል 14 ያንብቡ
ያዳምጡ የማርቆስ ወንጌል 14
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 14:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos