የአይሁድ የፋሲካና የቂጣ በዓል ሊከበር ሁለት ቀን ቀርቶት ነበር፤ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ኢየሱስን በተንኰል ይዘው የሚገድሉበትን ዘዴ ይፈልጉ ነበር። ነገር ግን ሕዝቡ ሁከት ያነሣሣል በማለት “በበዓል ቀን ይህን አናደርግም፤” አሉ። ኢየሱስ በቢታንያ ለምጻም በነበረው በስምዖን ቤት ነበር። በገበታም ቀርቦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነና የከበረ የናርዶስ ሽቶ የሞላበት፥ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች፤ ብልቃጡን ሰብራ ሽቶውን በኢየሱስ ራስ ላይ አፈሰሰችው። እዚያ ከነበሩት አንዳንዶቹ በድርጊቱ ተቈጥተው፦ “ይህ ሽቶ በከንቱ መባከኑ ለምንድን ነው? ይህ ሽቶ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ ተሸጦ ገንዘቡ ለድኾች ሊሰጥ ይቻል ነበር!” ተባባሉ፤ ሴቲቱንም ነቀፉአት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ “ተዉአት! ስለምን ታስቸግሩአታላችሁ? እርስዋ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች፤ ድኾች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ስለ ሆኑ በፈለጋችሁ ጊዜ ልትረዱአቸው ትችላላችሁ፤ እኔን ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አታገኙኝም፤ ይህች ሴት የተቻላትን አድርጋለች፤ ሥጋዬም ከመቀበሩ በፊት አስቀድማ ለማዘጋጀት ሽቶ ቀባችው። በእውነት እላችኋለሁ፤ በዓለም ሁሉ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ ይህ እርስዋ ያደረገችው ለመታሰቢያ ይነገርላታል።” ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፥ አስቆሮታዊው ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። እነርሱም ይህን ባወቁ ጊዜ ደስ አላቸው፤ ገንዘብም ሊሰጡት ቃል ገቡለት። እርሱም ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። የፋሲካውን በግ በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን፥ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ “የፋሲካን ራት ለመብላት ወዴት ሄደን እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እዚያም የውሃ እንሥራ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ፤ እርሱን ተከተሉት፤ ወደሚገባበትም ቤት ሂዱና የቤቱን ጌታ፥ ‘መምህር፥ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት ለእኔ የሚሆን የእንግዳ ማረፊያ ቤት የት ነው?’ ይላል በሉት። እርሱም በሰገነት ላይ ያለውን የተዘጋጀውንና የተነጠፈውን ትልቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁልን።” ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከዚያ ወጥተው ወደ ከተማው ሄዱ፤ ልክ ኢየሱስ እንዳላቸውም አገኙ፤ የፋሲካንም ራት በዚያ አዘጋጁ። በመሸ ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ፤ በገበታ ቀርበው ሲበሉ ኢየሱስ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል፤ እርሱም አሁን ከእኔ ጋር ራት በመብላት ላይ የሚገኘው ነው፤” አለ። እነርሱም በዚህ ነገር አዝነው “እኔ እሆንን?” እያሉ ተራ በተራ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ያ ሰው ከዐሥራ ሁለታችሁ አንዱ የሆነው አሁን ከእኔ ጋር በዚህ ሳሕን ውስጥ ወጥ የሚያጠቅሰው ነው፤ የሰው ልጅ አስቀድሞ ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ወደ ሞት መሄዱ አይቀርም፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰውስ ቀድሞውኑ ባይወለድ ይሻለው ነበር!” እነርሱ በመብላት ላይ ሳሉ ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ፥ ይህ ሥጋዬ ነው” ብሎ ሰጣቸው። ጽዋውንም አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ ሰጣቸው፤ ሁሉም ከጽዋው ጠጡ። እንዲህም አላቸው፦ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የቃል ኪዳን ደሜ ነው፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ከአዲሱ ወይን እስክጠጣ ድረስ ከዚህ ወይን ፍሬ ጭማቂ ዳግመኛ አልጠጣም።” ከዚያም በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ።
የማርቆስ ወንጌል 14 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 14:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos