ማርቆስ 14:1-26
ማርቆስ 14:1-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ፋሲካና የቂጣ በዓል ሊከበር ሁለት ቀን ሲቀረው፣ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ኢየሱስን የሚይዙበትና የሚገድሉበትን ዘዴ ይፈልጉ ነበር። ሆኖም፣ “ሕዝቡ ዐመፅ እንዳያነሣ በበዓሉ ሰሞን መሆን የለበትም” ይባባሉ ነበር። እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ ስምዖን ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ፣ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ የተሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፣ ቢልቃጡንም ሰብራ ሽቱውን በራሱ ላይ አፈሰሰችው። በዚያ ከነበሩት አንዳንዶቹ በድርጊቱ ተቈጥተው እንዲህ ይባባሉ ነበር፤ “ሽቱው ለምን በከንቱ ይባክናል? ከሦስት መቶ ዲናር በላይ ተሸጦ፣ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ይቻል ነበር።” ሴትዮዋንም ነቀፏት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ተዉአት፣ ለምን ታስቸግሯታላችሁ? መልካም ነገር አድርጋልኛለች። ድኾች ምንጊዜም ከእናንተ ጋር ናቸው፤ በፈለጋችሁ ጊዜ ልትረዷቸው ትችላላችሁ፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ እርሷ ማድረግ የምትችለውን ያህል አድርጋለች፤ ለመቃብሬ እንዲሆን ሰውነቴን አስቀድማ ቀብታለች። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በሚሰበክበት በማንኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።” ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። እነርሱም ይህን ሲሰሙ ደስ አላቸው፤ ገንዘብ ሊሰጡትም ቃል ገቡለት፤ ስለዚህ እርሱን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይጠባበቅ ነበር። የፋሲካ በግ በሚታረድበት በቂጣ በዓል የመጀመሪያው ቀን፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “የፋሲካ እራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እንስራ ውሃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤትም ተከተሉት፤ የቤቱንም ጌታ፣ ‘መምህሩ፣ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የትኛው ነው?’ ብሏል በሉት፤ እርሱም በሰገነቱ ላይ የተሰናዳና የተነጠፈ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ እዚያ አዘጋጁልን።” ደቀ መዛሙርቱም ወጥተው ወደ ከተማዪቱ ሄዱ፤ ማንኛውም ነገር ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካውንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። በማእድ ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከመካከላችሁ አንዱ፣ አብሮኝ የሚበላው እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። እነርሱም ዐዘኑ፤ እያንዳንዳቸውም፣ “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፣ ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ውስጥ የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ግን ወዮለት! ያ ሰው ባይወለድ ይሻለው ነበር።” ሲበሉም እንጀራ አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸውና፣ “ዕንኩ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው። ጽዋውንም አነሣ፤ አመስግኖም ሰጣቸው፤ ሁሉም ከዚያ ጠጡ። ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ እስከምጠጣበት እስከዚያች ቀን ድረስ ዳግም ይህን አልጠጣም።” ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ።
ማርቆስ 14:1-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካና የቂጣ በዓል ነበረ። የካህናት አለቆችም ጻፎችም እንዴት አድርገው በተንኰል እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት ይፈልጉ ነበር። “የሕዝብ ሁከት እንዳይሆን በበዓል አይሁን፤” ይሉ ነበርና። እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በነበረ ጊዜ፥ በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ የናርዶስ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች፤ ብልቃጡንም ሰብራ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። አንዳንዶችም “ይህ የሽቶ ጥፋት ለምንድር ነው? ይህ ሽቶ ከሦስት መቶ ዲናር በሚበልጥ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና፤” ብለው በራሳቸው ይቈጡ ነበር፤ እርስዋንም ነቀፉአት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ “ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች። ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፤ በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም። የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል።” ከዐሥራ ሁለቱም አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። ሲሰሙም ደስ አላቸው፤ ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት። በሚመች ጊዜም እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንዲሰጠው ይፈልግ ነበር። የፋሲካን በግ በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ “ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ?” አሉት። ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ፤ እንዲህም አላቸው “ወደ ከተማ ሂዱ፤ ማድጋ ውኀ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤ተከተሉት። የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ ‘መምህሩ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል፤’ በሉት። እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤በዚያም አሰናዱልን።” ደቀ መዛሙርቱም ወጡ፤ ወደከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፤ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል፤” አለ። እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም መልሶ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር፤” አላቸው። ሲበሉም ኢየሱስ ኅብስትን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸውና “እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው፤” አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፤ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ። እርሱም “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው። እውነት እላችኋለሁ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም፤” አላቸው። መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።
ማርቆስ 14:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካና የቂጣ በዓል ነበረ። የካህናት አለቆችም ጻፎችም እንዴት አድርገው በተንኰል እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት ይፈልጉ ነበር። የሕዝብ ሁከት እንዳይሆን በበዓል አይሁን ይሉ ነበርና። እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በነበረ ጊዜ፥ በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ ናርዶስ ሽቱ የመላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፤ ቢልቃጡንም ሰብራ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። አንዳንዶችም፦ ይህ የሽቱ ጥፋት ለምንድር ነው? ይህ ሽቱ ከሦስት መቶ ዲናር በሚበልጥ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና ብለው በራሳቸው ይቈጡ ነበር፤ እርስዋንም ነቀፉአት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች። ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም። የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል። ከአሥራ ሁለቱም አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። ሲሰሙም ደስ አላቸው ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት። በሚመች ጊዜም እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንዲሰጠው ይፈልግ ነበር። ፋሲካን በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ፦ ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ? አሉት። ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እንዲህም አላቸው፦ ወደ ከተማ ሂዱ፥ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤ ተከተሉት፥ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ፦ መምህሩ፦ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል በሉት። እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፥ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል አለ። እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም፦ እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። እርሱም መልሶ፦ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አላቸው። ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና፦ እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ። እርሱም፦ ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው። እውነት እላችኋለሁ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም አላቸው። መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።
ማርቆስ 14:1-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የአይሁድ የፋሲካና የቂጣ በዓል ሊከበር ሁለት ቀን ቀርቶት ነበር፤ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ኢየሱስን በተንኰል ይዘው የሚገድሉበትን ዘዴ ይፈልጉ ነበር። ነገር ግን ሕዝቡ ሁከት ያነሣሣል በማለት “በበዓል ቀን ይህን አናደርግም፤” አሉ። ኢየሱስ በቢታንያ ለምጻም በነበረው በስምዖን ቤት ነበር። በገበታም ቀርቦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነና የከበረ የናርዶስ ሽቶ የሞላበት፥ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች፤ ብልቃጡን ሰብራ ሽቶውን በኢየሱስ ራስ ላይ አፈሰሰችው። እዚያ ከነበሩት አንዳንዶቹ በድርጊቱ ተቈጥተው፦ “ይህ ሽቶ በከንቱ መባከኑ ለምንድን ነው? ይህ ሽቶ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ ተሸጦ ገንዘቡ ለድኾች ሊሰጥ ይቻል ነበር!” ተባባሉ፤ ሴቲቱንም ነቀፉአት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ “ተዉአት! ስለምን ታስቸግሩአታላችሁ? እርስዋ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች፤ ድኾች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ስለ ሆኑ በፈለጋችሁ ጊዜ ልትረዱአቸው ትችላላችሁ፤ እኔን ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አታገኙኝም፤ ይህች ሴት የተቻላትን አድርጋለች፤ ሥጋዬም ከመቀበሩ በፊት አስቀድማ ለማዘጋጀት ሽቶ ቀባችው። በእውነት እላችኋለሁ፤ በዓለም ሁሉ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ ይህ እርስዋ ያደረገችው ለመታሰቢያ ይነገርላታል።” ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፥ አስቆሮታዊው ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። እነርሱም ይህን ባወቁ ጊዜ ደስ አላቸው፤ ገንዘብም ሊሰጡት ቃል ገቡለት። እርሱም ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። የፋሲካውን በግ በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን፥ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ “የፋሲካን ራት ለመብላት ወዴት ሄደን እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እዚያም የውሃ እንሥራ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ፤ እርሱን ተከተሉት፤ ወደሚገባበትም ቤት ሂዱና የቤቱን ጌታ፥ ‘መምህር፥ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት ለእኔ የሚሆን የእንግዳ ማረፊያ ቤት የት ነው?’ ይላል በሉት። እርሱም በሰገነት ላይ ያለውን የተዘጋጀውንና የተነጠፈውን ትልቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁልን።” ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከዚያ ወጥተው ወደ ከተማው ሄዱ፤ ልክ ኢየሱስ እንዳላቸውም አገኙ፤ የፋሲካንም ራት በዚያ አዘጋጁ። በመሸ ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ፤ በገበታ ቀርበው ሲበሉ ኢየሱስ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል፤ እርሱም አሁን ከእኔ ጋር ራት በመብላት ላይ የሚገኘው ነው፤” አለ። እነርሱም በዚህ ነገር አዝነው “እኔ እሆንን?” እያሉ ተራ በተራ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ያ ሰው ከዐሥራ ሁለታችሁ አንዱ የሆነው አሁን ከእኔ ጋር በዚህ ሳሕን ውስጥ ወጥ የሚያጠቅሰው ነው፤ የሰው ልጅ አስቀድሞ ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ወደ ሞት መሄዱ አይቀርም፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰውስ ቀድሞውኑ ባይወለድ ይሻለው ነበር!” እነርሱ በመብላት ላይ ሳሉ ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ፥ ይህ ሥጋዬ ነው” ብሎ ሰጣቸው። ጽዋውንም አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ ሰጣቸው፤ ሁሉም ከጽዋው ጠጡ። እንዲህም አላቸው፦ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የቃል ኪዳን ደሜ ነው፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ከአዲሱ ወይን እስክጠጣ ድረስ ከዚህ ወይን ፍሬ ጭማቂ ዳግመኛ አልጠጣም።” ከዚያም በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ።
ማርቆስ 14:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የፋሲካና የቂጣ በዓል ሊከበር ሁለት ቀን ሲቀረው፥ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ኢየሱስን የሚይዙበትና የሚገድሉበትን ዘዴ ይፈልጉ ነበር። ሆኖም፥ “ሕዝቡ ዐመፅ እንዳያነሣ በበዓሉ ሰሞን መሆን የለበትም” ይባባሉ ነበር። እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ ስምዖን ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ የተሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፥ ቢልቃጡንም ሰብራ ሽቱውን በራሱ ላይ አርከፈከፈችው። በዚያ ከነበሩት አንዳንዶቹ በድርጊቱ ተቆጥተው እንዲህ ይባባሉ ነበር፤ “ሽቱው ለምን በከንቱ ይባክናል? ከሦስት መቶ ዲናር በላይ ተሸጦ፥ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ይቻል ነበር።” ሴትዮዋንም ነቀፏት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ተዉአት፥ ለምን ታስቸግሯታላችሁ? መልካም ነገር አድርጋልኛለች። ድኾች ምንም ጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ በፈለጋችሁ ጊዜ ልትረዷቸው ትችላላችሁ፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ እርሷ ማድረግ የምትችለውን ያህል አድርጋለች፤ ለመቃብሬ እንዲሆን ሰውነቴን አስቀድማ ቀብታለች። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በሚሰበክበት በማንኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።” ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። እነርሱም ይህን ሲሰሙ ደስ አላቸው፤ ገንዘብ ሊሰጡትም ቃል ገቡለት፤ ስለዚህ እርሱን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይጠባበቅ ነበር። የፋሲካ በግ በሚታረድበት በቂጣ በዓል የመጀመሪያው ቀን፥ ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “የፋሲካ እራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እንስራ ውሃ የተሸከመ ሰው ያገኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤትም ተከተሉት፤ የቤቱንም ጌታ፥ መምህሩ፥ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የትኛው ነው?” ብሏል በሉት፤ እርሱም በሰገነቱ ላይ የተሰናዳና የተነጠፈ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ እዚያ አዘጋጁልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጥተው ወደ ከተማዪቱ ሄዱ፤ ማንኛውም ነገር ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካውንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። በማእድ ላይ ሳሉም፥ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከመካከላችሁ አንዱ፥ አብሮኝ የሚበላው እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። እነርሱም አዘኑ፤ እያንዳንዳቸውም፥ “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፥ ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ውስጥ የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደተጻፈው ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ግን ወዮለት፤ ያ ሰው ባይወለድ ይሻለው ነበር።” ሲበሉም እንጀራ አንሥቶ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸውና፥ “እንኩ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው፤ ጽዋውንም አነሣ፤ አመስግኖም ሰጣቸው፤ ሁሉም ከዚያ ጠጡ። ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ እስከምጠጣበት እስከዚያች ቀን ድረስ ዳግም ይህን አልጠጣም።” ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረዘይት ተራራ ወጡ።