ፋሲካና የቂጣ በዓል ሊከበር ሁለት ቀን ሲቀረው፣ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ኢየሱስን የሚይዙበትና የሚገድሉበትን ዘዴ ይፈልጉ ነበር። ሆኖም፣ “ሕዝቡ ዐመፅ እንዳያነሣ በበዓሉ ሰሞን መሆን የለበትም” ይባባሉ ነበር። እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ ስምዖን ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ፣ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ የተሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፣ ቢልቃጡንም ሰብራ ሽቱውን በራሱ ላይ አፈሰሰችው። በዚያ ከነበሩት አንዳንዶቹ በድርጊቱ ተቈጥተው እንዲህ ይባባሉ ነበር፤ “ሽቱው ለምን በከንቱ ይባክናል? ከሦስት መቶ ዲናር በላይ ተሸጦ፣ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ይቻል ነበር።” ሴትዮዋንም ነቀፏት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ተዉአት፣ ለምን ታስቸግሯታላችሁ? መልካም ነገር አድርጋልኛለች። ድኾች ምንጊዜም ከእናንተ ጋር ናቸው፤ በፈለጋችሁ ጊዜ ልትረዷቸው ትችላላችሁ፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ እርሷ ማድረግ የምትችለውን ያህል አድርጋለች፤ ለመቃብሬ እንዲሆን ሰውነቴን አስቀድማ ቀብታለች። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በሚሰበክበት በማንኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።” ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። እነርሱም ይህን ሲሰሙ ደስ አላቸው፤ ገንዘብ ሊሰጡትም ቃል ገቡለት፤ ስለዚህ እርሱን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይጠባበቅ ነበር። የፋሲካ በግ በሚታረድበት በቂጣ በዓል የመጀመሪያው ቀን፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “የፋሲካ እራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እንስራ ውሃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤትም ተከተሉት፤ የቤቱንም ጌታ፣ ‘መምህሩ፣ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የትኛው ነው?’ ብሏል በሉት፤ እርሱም በሰገነቱ ላይ የተሰናዳና የተነጠፈ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ እዚያ አዘጋጁልን።” ደቀ መዛሙርቱም ወጥተው ወደ ከተማዪቱ ሄዱ፤ ማንኛውም ነገር ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካውንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። በማእድ ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከመካከላችሁ አንዱ፣ አብሮኝ የሚበላው እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። እነርሱም ዐዘኑ፤ እያንዳንዳቸውም፣ “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፣ ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ውስጥ የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ግን ወዮለት! ያ ሰው ባይወለድ ይሻለው ነበር።” ሲበሉም እንጀራ አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸውና፣ “ዕንኩ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው። ጽዋውንም አነሣ፤ አመስግኖም ሰጣቸው፤ ሁሉም ከዚያ ጠጡ። ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ እስከምጠጣበት እስከዚያች ቀን ድረስ ዳግም ይህን አልጠጣም።” ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ።
ማርቆስ 14 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 14
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 14:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos