ከዚህም ነገር በኋላ በስምንተኛው ቀን ጌታችን ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞአቸው ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ነጭ ሆነ፤ እንደ መብረቅም አብለጨለጨ። እነሆም፥ ሁለት ሰዎች መጥተው ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር። እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ነበሩ። በክብርም ተገልጠው በኢየሩሳሌም ይደረግ ዘንድ ያለውን ክብሩንና መውጣቱን ተናገሩ፤ ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ፈዝዘው አገኘ፤ በነቁም ጊዜ ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ። ከዚህም በኋላ ከእርሱ ሲለዩ ጴጥሮስ ጌታችን ኢየሱስን፥ “መምህር፥ ሆይ፥ እዚህ ብንኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ሦስት ሰቀላዎችንም እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ፥ አንዱንም ለሙሴ፥ አንዱንም ለኤልያስ” አለው፤ የሚናገረውንም አያውቅም ነበር። ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም በገቡ ጊዜ ፈሩ። ከደመናውም ውስጥ፥ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ቃል መጣ። ቃሉም ከመጣ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ብቻውን ተገኘ፤ እነርሱ ግን ዝም አሉ፤ ያዩትንና የሰሙትንም በዚያ ጊዜ ለማንም አልተናገሩም። በሁለተኛውም ቀን ከተራራው ወረዱ፤ ብዙ ሕዝብም ተቀበሉት። አንድ ሰውም በሕዝቡ መካከል ጮኾ እንዲህ አለው፥ “መምህር ሆይ፥ እርሱ ለእኔ አንድ ነውና ልጄን ታይልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ። እነሆ፥ ጋኔን ሊነጥቀኝ ነው፤ ድንገትም ያስጮኸዋል፤ ጥሎም ያፈራግጠዋል፤ አረፋም ያስደፍቀዋል፤ ቀጥቅጦ በጭንቅ ይተወዋል። እንዲያወጡትም ደቀ መዛሙርትህን ለመንሁአቸው፤ ነገር ግን ማውጣት ተሳናቸው።” ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “የማታምን ከዳተኛ ትውልድ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጅህን ወደዚህ አምጣው” አለው። ሲያመጣውም ጋኔኑ ጣለውና አፈራገጠው፤ ጌታችን ኢየሱስም ያን ክፉ ጋኔን ገሠጸው፤ ልጁንም አዳነው፤ ለአባቱም ሰጠው። ሁሉም ከእግዚአብሔር ታላቅነት የተነሣ አደነቁ። እነርሱም ጌታችን ኢየሱስ ባደረገው ተአምራት ሁሉ ሲደነቁ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው። “እናንተስ ይህን ነገር በልባችሁ አኑሩት፤ የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጥ ዘንድ አለውና።” እነርሱ ግን ይህን ነገር አላስተዋሉትም፤ እንዳይመረምሩት ከእነርሱ የተሰወረ ነውና፤ ስለዚህ ነገርም እንዳይጠይቁት ይፈሩት ነበርና። እርስ በርሳቸውም ከእነርሱ ማን እንደሚበልጥ ዐሰቡ። ጌታችን ኢየሱስም በልቡናቸው የሚያስቡትን ዐወቀባቸውና አንድ ሕፃን ወስዶ በመካከላቸው አቆመው። እንዲህም አላቸው፥ “በስሜ እንደዚህ ያለውን ሕፃን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፤ ራሱን ከሁሉ ዝቅ የሚያደርግ እርሱ ታላቅ ይሆናል።” ዮሐንስም መልሶ፥ “መምህር ሆይ፥ በስምህ ጋኔን ሲያወጣ ያየነው አንድ ሰው አለ፤ ከእኛም ጋር አልተከተለህምና ከለከልነው፤” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “አትከልክሉት፤ ባለጋራችሁ ካልሆነ ባልንጀራችሁ ነውና” አላቸው። የመውጣቱ ወራትም በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና። በፊቱም መልእክተኞችን ላከ፤ ሄደውም ያዘጋጁለት ዘንድ ወደ ሰማርያ ከተማ ገቡ። ነገር ግን አልተቀበሉትም፤ ፊቱን ወደ ኢየሩሳሌም አቅንቶ ነበርና። ደቀ መዛሙርቱ ያዕቆብና ዮሐንስም ይህን ባዩ ጊዜ፥ “አቤቱ፥ ኤልያስ እንደ አደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንድንል ትፈቅዳለህን?” አሉት። እርሱ ግን ዘወር ብሎ፥ “ከምን መንፈስ እንደ ሆናችሁ አታውቁም” ብሎ ገሠጻቸው። የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም። ወደ ሌላም መንደር ሄዱ።
የሉቃስ ወንጌል 9 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 9
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 9:28-56
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች