ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን ያህል በኋላ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ሊጸልይ ወደ አንድ ተራራ ወጣ። በመጸለይ ላይ እንዳለም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም እጅግ የሚያንጸባርቅ ሆነ። እነሆም፤ ሁለት ሰዎች፣ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋራ ይነጋገሩ ነበር፤ በክብርም ተገልጠው፣ በኢየሩሳሌም ይፈጸም ዘንድ ስላለው ከዚህ ዓለም ስለ መለየቱ ይናገሩ ነበር። ጴጥሮስና ዐብረውት የነበሩት ግን እንቅልፍ ተጭኗቸው ነበር፤ ሲነቁ ግን ክብሩንና ከርሱ ጋራ የቆሙትን ሁለት ሰዎች አዩ። ሰዎቹም ከኢየሱስ ተለይተው ሲሄዱ፣ ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ እዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ ሦስት ዳሶች እንሥራ፤ አንዱ ለአንተ፣ አንዱ ለሙሴ፣ አንዱም ለኤልያስ ይሆናል” አለው፤ የሚናገረውንም አያውቅም ነበር። ይህንም እየተናገረ ሳለ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ፈሩ። ከደመናውም ውስጥ፣ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ። ድምፁም በተሰማ ጊዜ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ፤ ደቀ መዛሙርቱም ነገሩን በልባቸው ያዙ እንጂ ስላዩት ነገር በዚያ ወቅት ለማንም አልተናገሩም። በማግስቱም ከተራራው ከወረዱ በኋላ፣ ብዙ ሕዝብ መጥቶ ኢየሱስን አገኘው። በዚህ ጊዜ ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “መምህር ሆይ፤ ያለኝ ልጅ እርሱ ብቻ ስለ ሆነ፣ ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ። መንፈስ ሲይዘው በድንገት ይጮኻል፤ ዐረፋ እያስደፈቀው ያንፈራግጠዋል፤ ጕዳትም ካደረሰበት በኋላ በስንት መከራ ይተወዋል፤ ደቀ መዛሙርትህ እንዲያወጡለት ለመንኋቸው፤ ነገር ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም “የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋራ እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጅህን ወደዚህ አምጣው!” አለ። ልጁ በመምጣት ላይ ሳለም ጋኔኑ መሬት ላይ ጥሎ አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኩሱን መንፈስ ገሥጾ ልጁን ፈወሰው፤ ለአባቱም መልሶ ሰጠው። ሰዎቹም ሁሉ በእግዚአብሔር ታላቅነት ተገረሙ። እርሱ ባደረገው ሁሉ ሰዎች ሁሉ እየተገረሙ ሳሉ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ይህን የምነግራችሁን ነገር ልብ በሉ፤ የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ዐልፎ ይሰጣልና” አለ። እነርሱ ግን ይህን አባባል አልተረዱም፤ እንዳያስተውሉ ነገሩ ተሰውሮባቸው ነበር፤ ስለዚህ ነገር መልሰው እንዳይጠይቁትም ፈሩ። ከእነርሱ ማን እንደሚበልጥ በደቀ መዛሙርቱ መካከል ክርክር ተነሣ። ኢየሱስም የልባቸውን ሐሳብ ተረድቶ፣ አንድ ሕፃን ይዞ በአጠገቡ አቆመ፤ እንዲህም አላቸው፤ “ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል ማንም ቢኖር እኔን ይቀበላል፤ እኔን የሚቀበል ደግሞ የላከኝን ይቀበላል፤ ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ከሁሉ ይበልጣልና።” ዮሐንስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየነው፤ ከእኛ ጋራ ሆኖ ስለማይከተል ልንከለክለው ሞከርን” አለው። ኢየሱስም፣ “አትከልክሉት፤ የማይቃወማችሁ ሁሉ እርሱ ከእናንተ ጋራ ነውና” አለው። ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሚያርግበት ጊዜ በመቃረቡ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቈርጦ ተነሣ፤ አስቀድሞም መልእክተኞችን ወደዚያ ላከ። እነርሱም ሁኔታዎችን አስቀድመው ሊያመቻቹለት ወደ አንድ የሳምራውያን መንደር ገቡ። ሕዝቡ ግን ወደ ኢየሩሳሌም እያመራ መሆኑን ስላወቁ አልተቀበሉትም። ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ ይህን ሲያዩ፣ “ጌታ ሆይ፤ ኤልያስ እንዳደረገው ሁሉ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲያጠፋቸው እንድናዝዝ ትፈቅዳለህን?” አሉት። ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና፣ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ።
ሉቃስ 9 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 9
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 9:28-56
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች