ኦሪት ዘሌዋውያን 24
24
ስለ ተቅዋመ ማኅቶት
(ዘፀ. 27፥1-21)
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“መብራቱን ሁል ጊዜ እንድታበራበት ለመብራት ጥሩ ተወቅጦ የተጠለለ የወይራ ዘይት ያመጡልህ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው። 3በምስክሩ ድንኳን ከመጋረጃው ውጭ አሮንና ልጆቹ ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ሁል ጊዜ ያበሩታል፤ ለዘለዓለም ለልጅ ልጃችሁ ሥርዐት ይሁን። 4በእግዚአብሔር ፊት በጥሩ መቅረዝ ላይ መብራቶቹን ሁል ጊዜ እስኪነጋ አብሩአቸው።
ስለ ኅብስተ ገጽ
5“የስንዴ ዱቄት ወስደህ ዐሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ በእያንዳንዱ ኅብስት ውስጥ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ ይሁን። 6እነዚህንም ስድስት ስድስቱን በሁለት ተርታ አድርገህ በእግዚአብሔር ፊት በንጹሕ ገበታ ላይ አኑራቸው። 7በሁለቱም ተራ ንጹሕ ዕጣንና ጨው ታደርጋለህ፤ እነዚህም ነገሮች በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ ለተዘጋጁት ኅብስቶች ይሁኑ። 8በእግዚአብሔር ፊት ሁል ጊዜ በሰንበት ቀን ሁሉ ያድርጉት፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘለዓለም ቃል ኪዳን ነው። 9ለአሮንና ለልጆቹም ይሁን፤ በእሳት ከተደረገው ከእግዚአብሔር ቍርባን ለዘለዓለም ሥርዐት ለእርሱ ቅዱሰ ቅዱሳን ነውና በተቀደሰ ስፍራ ይብሉት።”
በእግዚአብሔር ላይ ስለሚደረግ ፅርፈት ቅጣት
10አባቱ ግብፃዊ የነበረ የእስራኤላዊት ሴት ልጅ በእስራኤል ልጆች መካከል ወጣ፤ የእስራኤላዊቱ ሴት ልጅና አንድ እስራኤላዊ ሰው በሰፈር ውስጥ ተጣሉ፤ 11የእስራኤላዊቱም ሴት ልጅ የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ ሰደበ፤ ወደ ሙሴም አመጡት። እናቱም ከዳን ነገድ የዳቤር ልጅ ነበረች፤ ስምዋም ሰሎሚት ነበረ። 12በእግዚአብሔርም ትእዛዝ እስኪፈርዱበት ድረስ በግዞት አኖሩት።
13እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 14“ተሳዳቢውን ከሰፈር ወደ ውጭ አውጣው፤ የሰሙትም ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ በድንጋይ ይውገሩት።” 15ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ትነግራለህ፥ “ማናቸውም ሰው አምላኩን ቢሰድብ ኀጢአቱን ይሸከማል። 16የእግዚአብሔርንም ስም ጠርቶ የሚሰድብ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል፤ ማኅበሩም ሁሉ በድንጋይ ይውገሩት፤ መጻተኛ ወይም የሀገር ልጅ ቢሆን፥ የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ ቢሳደብ ይገደል። 17ሰውን የገደለ ሰው ሁሉ ፈጽሞ ይገደል። 18እንስሳንም ቢገድል በነፍስ ፋንታ ነፍስ ይክፈል። 19ሰውም ባልንጀራውን ቢጎዳ፥ እርሱ እንዳደረገ እንዲሁ ይደረግበት። 20ስብራት በስብራት ፋንታ፥ ዐይን በዐይን ፋንታ፥ ጥርስ በጥርስ ፋንታ፥ ሰውን እንደ ጎዳ እንዲሁ ይደረግበት። 21ሰውንም የመታና የገደለ ፈጽሞ ይገደል። 22እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ለመጻተኛና ለሀገር ልጅ አንድ ዐይነት ሕግ ይሁንላችሁ።” 23ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገራቸው፤ ተሳዳቢውንም ከሰፈር ወደ ውጭ አወጡት፤ በድንጋይም ወገሩት። የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 24: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ