ኦሪት ዘሌ​ዋ​ው​ያን 14:33-57

ኦሪት ዘሌ​ዋ​ው​ያን 14:33-57 አማ2000

እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሙሴ​ንና አሮ​ንን እን​ዲህ ብሎ ተና​ገ​ራ​ቸው፦ “ትወ​ር​ሱ​አት ዘንድ እኔ ወደ​ም​ሰ​ጣ​ችሁ ርስት ወደ ከነ​ዓን ምድር በገ​ባ​ችሁ ጊዜ፥ እኔም የለ​ምጽ ደዌ ምል​ክት በር​ስ​ታ​ችሁ ምድር ቤቶች ባደ​ረ​ግሁ ጊዜ፥ ባለ​ቤቱ መጥቶ ካህ​ኑን፦ ‘ደዌ በቤቴ ውስጥ እን​ዳለ አይ​ቻ​ለሁ’ ብሎ ይን​ገ​ረው። ካህ​ኑም በቤቱ ውስጥ ያለው ዕቃ ሁሉ እን​ዳ​ይ​ረ​ክስ፥ እርሱ የለ​ም​ጹን ምል​ክት ለማ​የት ወደ ቤት ሳይ​ገባ፥ ቤቱን ባዶ እን​ዲ​ያ​ደ​ር​ጉት ያዝ​ዛል፤ በኋ​ላም ካህኑ ቤቱን ለማ​የት ይገ​ባል። የለ​ም​ጹ​ንም ምል​ክት ያያል፤ እነ​ሆም፥ የለ​ምጹ ምል​ክት በግ​ንቡ ላይ በአ​ረ​ን​ጓ​ዴና በቀይ ቢዥ​ጐ​ረ​ጐር፥ መል​ኩም ወደ ግንቡ ውስጥ ቢጠ​ልቅ፥ ካህኑ ከቤቱ ውስጥ ወደ ቤቱ በር ወጥቶ ሰባት ቀን ቤቱን ይዘ​ጋ​ዋል። ካህ​ኑም በሰ​ባ​ተ​ኛው ቀን ተመ​ልሶ ቤቱን ያያል፤ እነ​ሆም፥ ደዌው በቤቱ ግንብ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ ደዌ ያለ​ባ​ቸ​ውን ድን​ጋ​ዮች እን​ዲ​ያ​ወጡ፥ ከከ​ተ​ማ​ውም ወደ ውጭ ወደ ረከ​ሰው ስፍራ እን​ዲ​ጥ​ሉ​አ​ቸው ያዝ​ዛል። ቤቱ​ንም በው​ስጡ በዙ​ሪ​ያው ያስ​ፍ​ቀ​ዋል፤ የፋ​ቁ​ት​ንም የም​ር​ጊ​ቱን አፈር ከከ​ተ​ማው ወደ ውጭ ወደ ረከሰ ስፍራ ያፈ​ስ​ሱ​ታል። በእ​ነ​ዚ​ያም ድን​ጋ​ዮች ስፍራ ሌሎች ድን​ጋ​ዮ​ችን ያገ​ባሉ፤ ሌላም ጭቃ ወስ​ደው ቤቱን ይመ​ር​ጉ​ታል። “ደዌ​ውም ዳግም ቢመ​ለስ፥ ድን​ጋ​ዮ​ቹም ከወጡ፥ ቤቱም ከተ​ፋ​ቀና ከተ​መ​ረገ በኋላ በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ፥ ካህኑ ገብቶ ያያል፤ እነ​ሆም፥ ደዌው በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ፥ በቤቱ ውስጥ ያለው እየ​ፋገ የሚ​ሄድ ለምጽ ነው፤ ርኩስ ነው። ቤቱ​ንም፥ ድን​ጋ​ዮ​ቹ​ንም፥ ዕን​ጨ​ቱ​ንም፥ የቤ​ቱ​ንም ምር​ጊት ሁሉ ያፈ​ር​ሳል፤ እነ​ር​ሱ​ንም ከከ​ተ​ማው ወደ ውጭ ወደ ርኩስ ስፍራ ያወ​ጣል። በተ​ዘ​ጋ​በ​ትም ጊዜ ሁሉ ወደ ቤቱ የሚ​ገባ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆ​ናል። በቤ​ቱም የሚ​ተኛ ልብ​ሱን ያጥ​ባል፤ እስከ ማታም ርኩስ ነው፤ በቤ​ቱም የሚ​በላ ልብ​ሱን ያጥ​ባል፤ እስከ ማታም ርኩስ ነው። “ካህ​ኑም ገብቶ ቢያ​የው፥ እነ​ሆም፥ ቤቱ ከተ​መ​ረገ በኋላ ደዌው በቤቱ ውስጥ ባይ​ሰፋ፥ ደዌው ስለ ሻረ ካህኑ ቤቱን፦ ንጹሕ ነው ይለ​ዋል። ካህ​ኑም ቤቱን ለማ​ን​ጻት ሁለት ዶሮ​ዎች፥ የዝ​ግባ ዕን​ጨት፥ ቀይ ግምጃ፥ ሂሶ​ጵም ይወ​ስ​ዳል። አን​ደ​ኛ​ዪ​ቱ​ንም ዶሮ በሸ​ክላ ዕቃ ውስጥ ከም​ንጩ ውኃ በላይ ያር​ዳል። የዝ​ግ​ባ​ውን ዕን​ጨት፥ ሂሶ​ጱ​ንም፥ ቀዩ​ንም ግምጃ፥ ደኅ​ነ​ኛ​ዪ​ቱ​ንም ዶሮ ወስዶ በታ​ረ​ደ​ችው ዶሮ ደምና በም​ንጩ ውኃ ውስጥ ይነ​ክ​ራ​ቸ​ዋል፥ ቤቱ​ንም ሰባት ጊዜ ይረ​ጨ​ዋል። ቤቱ​ንም በዶ​ሮ​ዪቱ ደም በም​ን​ጩም ውኃ፥ በደ​ኅ​ነ​ኛ​ዪ​ቱም ዶሮ፥ በዝ​ግ​ባ​ውም ዕን​ጨት፥ በሂ​ሶ​ጱም፥ በቀ​ዩም ግምጃ ያነ​ጻ​ዋል። ደኅ​ነ​ኛ​ዪ​ቱ​ንም ዶሮ ከከ​ተማ ወደ ሜዳ ይሰ​ድ​ዳ​ታል፤ ለቤ​ቱም ያስ​ተ​ሰ​ር​ይ​ለ​ታል፤ ንጹ​ሕም ይሆ​ናል። “ይህም ሕግ ነው፤ ለሁሉ ዓይ​ነት ለም​ጽና የቈ​ረ​ቈር ደዌ ሕጉ ይህ ነው፤ በል​ብ​ስና በቤ​ትም ላለ ለምጽ፥ ለዕ​ባ​ጭም፥ ለብ​ጕ​ርም፥ ለቋ​ቍ​ቻም፤ በሚ​ረ​ክ​ስና በሚ​ነጻ ጊዜ እን​ዲ​ያ​ስ​ታ​ውቅ ይህ የለ​ምጽ ሕግ ነው።”