እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “ትወርሱአት ዘንድ እኔ ወደምሰጣችሁ ርስት ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ እኔም የለምጽ ደዌ ምልክት በርስታችሁ ምድር ቤቶች ባደረግሁ ጊዜ፥ ባለቤቱ መጥቶ ካህኑን፦ ‘ደዌ በቤቴ ውስጥ እንዳለ አይቻለሁ’ ብሎ ይንገረው። ካህኑም በቤቱ ውስጥ ያለው ዕቃ ሁሉ እንዳይረክስ፥ እርሱ የለምጹን ምልክት ለማየት ወደ ቤት ሳይገባ፥ ቤቱን ባዶ እንዲያደርጉት ያዝዛል፤ በኋላም ካህኑ ቤቱን ለማየት ይገባል። የለምጹንም ምልክት ያያል፤ እነሆም፥ የለምጹ ምልክት በግንቡ ላይ በአረንጓዴና በቀይ ቢዥጐረጐር፥ መልኩም ወደ ግንቡ ውስጥ ቢጠልቅ፥ ካህኑ ከቤቱ ውስጥ ወደ ቤቱ በር ወጥቶ ሰባት ቀን ቤቱን ይዘጋዋል። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ተመልሶ ቤቱን ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ግንብ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ ደዌ ያለባቸውን ድንጋዮች እንዲያወጡ፥ ከከተማውም ወደ ውጭ ወደ ረከሰው ስፍራ እንዲጥሉአቸው ያዝዛል። ቤቱንም በውስጡ በዙሪያው ያስፍቀዋል፤ የፋቁትንም የምርጊቱን አፈር ከከተማው ወደ ውጭ ወደ ረከሰ ስፍራ ያፈስሱታል። በእነዚያም ድንጋዮች ስፍራ ሌሎች ድንጋዮችን ያገባሉ፤ ሌላም ጭቃ ወስደው ቤቱን ይመርጉታል። “ደዌውም ዳግም ቢመለስ፥ ድንጋዮቹም ከወጡ፥ ቤቱም ከተፋቀና ከተመረገ በኋላ በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ፥ ካህኑ ገብቶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ፥ በቤቱ ውስጥ ያለው እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነው፤ ርኩስ ነው። ቤቱንም፥ ድንጋዮቹንም፥ ዕንጨቱንም፥ የቤቱንም ምርጊት ሁሉ ያፈርሳል፤ እነርሱንም ከከተማው ወደ ውጭ ወደ ርኩስ ስፍራ ያወጣል። በተዘጋበትም ጊዜ ሁሉ ወደ ቤቱ የሚገባ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። በቤቱም የሚተኛ ልብሱን ያጥባል፤ እስከ ማታም ርኩስ ነው፤ በቤቱም የሚበላ ልብሱን ያጥባል፤ እስከ ማታም ርኩስ ነው። “ካህኑም ገብቶ ቢያየው፥ እነሆም፥ ቤቱ ከተመረገ በኋላ ደዌው በቤቱ ውስጥ ባይሰፋ፥ ደዌው ስለ ሻረ ካህኑ ቤቱን፦ ንጹሕ ነው ይለዋል። ካህኑም ቤቱን ለማንጻት ሁለት ዶሮዎች፥ የዝግባ ዕንጨት፥ ቀይ ግምጃ፥ ሂሶጵም ይወስዳል። አንደኛዪቱንም ዶሮ በሸክላ ዕቃ ውስጥ ከምንጩ ውኃ በላይ ያርዳል። የዝግባውን ዕንጨት፥ ሂሶጱንም፥ ቀዩንም ግምጃ፥ ደኅነኛዪቱንም ዶሮ ወስዶ በታረደችው ዶሮ ደምና በምንጩ ውኃ ውስጥ ይነክራቸዋል፥ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። ቤቱንም በዶሮዪቱ ደም በምንጩም ውኃ፥ በደኅነኛዪቱም ዶሮ፥ በዝግባውም ዕንጨት፥ በሂሶጱም፥ በቀዩም ግምጃ ያነጻዋል። ደኅነኛዪቱንም ዶሮ ከከተማ ወደ ሜዳ ይሰድዳታል፤ ለቤቱም ያስተሰርይለታል፤ ንጹሕም ይሆናል። “ይህም ሕግ ነው፤ ለሁሉ ዓይነት ለምጽና የቈረቈር ደዌ ሕጉ ይህ ነው፤ በልብስና በቤትም ላለ ለምጽ፥ ለዕባጭም፥ ለብጕርም፥ ለቋቍቻም፤ በሚረክስና በሚነጻ ጊዜ እንዲያስታውቅ ይህ የለምጽ ሕግ ነው።”
ኦሪት ዘሌዋውያን 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 14:33-57
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች