ሰቆቃወ ኤርምያስ ነቢይ 4
4
ምዕራፍ 4 ።
ኢየሩሳሌም ከውድቀት በኋላ
1አሌፍ። ወርቁ እንዴት ደበሰ! ጥሩው ብር እንዴት ተለወጠ!
የከበረው ዕንቍ በጎዳናው ሁሉ እንዴት ተበተነ!
2ቤት። ጥሩ ወርቅ የሚመስሉ የከበሩ የጽዮን ልጆች፥
የሸክላ ሠሪ እጅ እንደ ሠራው እንደ ሸክላ ዕቃ እንዴት ተቈጠሩ!
3ጋሜል። አራዊት እንኳ ጡታቸውን ገልጠው ግልገሎቻቸውን አጠቡ፤
የወገኔ ሴት ልጆች ግን እንደ ምድረ በዳ ሰጐን ጨካኞች#“ጨካኞች” የሚለው በግእዝ የለም። ሆኑ።
4ዳሌጥ። ጡት የሚጠባው የሕፃን ምላስ ከጥም የተነሣ ወደ ትናጋው ተጣበቀ፤
ሕፃናት እንጀራ ለመኑ፤ የሚቈርስላቸውም የለም።
5ሄ። የጣፈጠ ነገር ይበሉ የነበሩ በመንገድ ጠፉ፤
በቀይ ግምጃ ያድጉ የነበሩ የፍግ ክምር አቀፉ።
6ዋው። የማንም እጅ ሳይወድቅባት ድንገት ከተገለበጠች፥
ከሰዶም ኀጢአት ይልቅ የወገኔ ሴት ልጅ ኀጢአት በዛች።
7ዛይ። ቅዱሳኖችዋ ከበረድ ይልቅ ነጡ፤ ከወተትም ይልቅ ነጡ፤
በመውጣታቸውም ሰንፔር ከሚባል ዕንቍ ይልቅ ፈጽመው ቀሉ።
8ሔት። ፊታቸው ከጥቀርሻ ይልቅ ጠቍሮአል፤ በመንገድም አልታወቁም፤
ቍርበታቸው ወደ አጥንታቸው ተጣብቆአል፤ ደርቆአል፤ እንደ እንጨትም ሆኖአል።
9ጤት። በሰይፍ የሞቱት በራብ ከሞቱት ይሻላሉ፤
እነዚህ የምድርን ፍሬ አጥተው#ግእዝ “በትእዛዘ እግዚአብሔር” ይላል። ተወግተውም ዐልፈዋል።
10ዮድ። የርኅሩኆች ሴቶች እጆች ልጆቻቸውን ቀቅለዋል፤
የወገኔ ሴት ልጅ በመቀጥቀጥዋ መብል ሆኖአቸው።
11ካፍ። እግዚአብሔር መዓቱን ፈጽሞአል፤ ጽኑ ቍጣውንም አፍስሶአል፤
እሳትን በጽዮን ውስጥ አቃጠለ፤ መሠረቷንም በላች።
12ላሜድ። የምድር ነገሥታት፥ በዓለምም የሚኖሩ ሁሉ፥
አስጨናቂና ጠላት በኢየሩሳሌም በር እንደሚገባ አላመኑም።
13ሜም። የጻድቃንን ደም በውስጥዋ ስላፈሰሱ፥
ስለ ነቢያቷ ኀጢአትና ስለ ካህናቷ በደል ነው።
14ኖን። እነርሱ ታውረው#“እነርሱ” የተባሉት በግሪክ ሰባ. ሊ. “ጠባቂዎችዋ” ተብለዋል። በመንገድ ላይ ተቅበዘበዙ፤
ልብሳቸውም እንዳይዳሰስ በደም ረክሰዋል።
15ሳምኬት። እናንተ ከርኩሳን ራቁ፥ አስተምሩአቸው፤ ራቁ፥ ራቁ በሉአቸው፤ አትንኩአቸውም።
ታውከዋልና ዳግመኛ እንዳይኖሩባት ለአሕዛብ ንገሩአቸው።
16ዔ። የእግዚአብሔር ፊት ክፍላቸው ነበረ። ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ አይመለከታቸውም፤
የካህናቱን ፊት አላፈሩም፤ ሽማግሌዎቹንም አላከበሩም።
17ፌ። በማያድን ወገን እያመንን ረዳታችን ከንቱ ስለ ሆነ፥
እኛ ገና በሕይወት ሳለን ዐይኖቻችን ጠፉ።
18ጻዴ። ልጆቻችንን ወደ አደባባያችን እንዳይወጡ ከለከልን፤
የምንጠፋበት ጊዜ ደርሷልና ዘመናችን አለቀ፤ የምንጠፋበትም ጊዜ ቀረበ።
19ቆፍ። አሳዳጆቻችን ከሰማይ ንስር ይልቅ ፈጣኖች ሆኑ፤
በተራሮች ላይ አሳደዱን፤ በምድረ በዳም ሸመቁብን።
20ሬስ። ስለ እርሱ፥ “በአሕዛብ ውስጥ በጥላው በሕይወት እንኖራለን” ያልነው፥
በእግዚአብሔር የተቀባ፥ የሕይወታችን እስትንፋስ፥ በወጥመዳቸው ተያዘ።
21ሣን። በዖፅ ምድር የምትኖሪ የኤዶምያስ ሴት ልጅ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፥ ሐሤትም አድርጊ፤
የእግዚአብሔር ጽዋ ደግሞ ወደ አንቺ ያልፋልና፥ አንቺም ትሰክሪአለሽ፥ ትራቆቻለሽም።
22ታው። የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፥ በደልሽ ተፈጸመ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አያስማርክሽም።
የኤዶምያስ ሴት ልጅ ሆይ፥ በደልሽን ይጐበኘዋል፤ ኀጢአትሽንም ይገልጣል።
Currently Selected:
ሰቆቃወ ኤርምያስ ነቢይ 4: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ