ሰቆቃወ ኤርምያስ ነቢይ 3
3
ቅጣት፥ ንስሓና ተስፋ
1አሌፍ። በቍጣው በትር ችግር ያየ ሰው እኔ ነኝ።
2ብርሃን ወደሌለበት ወደ ጨለማ መርቶ ወሰደኝ።
3ዘወትር ቀኑን ሁሉ እጁን በላዬ መለሰ።
4ቤት። ሥጋዬንና ቁርበቴን አስረጀ፥ አጥንቴን ሰበረ።
5በዙሪያዬ ቅጥር ሠራብኝ፤ የመከራውንም ጎዳና በእኔ ላይ አቀና።
6እንደ ቀድሞ ሙታን በጨለማ አኖረኝ።
7ጋሜል። እንዳልወጣ በዙሪያዬ ቅጥር ሠራብኝ፤ ሰንሰለቴንም አከበደ።
8በጠራሁና በጮኽሁ ጊዜ ጸሎቴ ተከለከለ።
9መንገዴን በዓለት ላይ ሠራ፤ ጎዳናዬንም አጠረ።
10ዳሌጥ። እንደምትሸምቅ ድብ እንደ ተሸሸገም አንበሳ ሆነብኝ።
11ተከተለኝ፤ ጨረሰኝ፤ ባድማም አደረገኝ።
12ቀስቱን ገተረ፤ ለፍላጻውም እንደ ዒላማ አደረገኝ።
13ሄ። የሰገባውን ፍላጻዎች በኵላሊቴ ውስጥ ተከለ።
14ለወገኔ ሁሉ መሳቂያ ሆንሁ፤ ቀኑንም ሁሉ ዘፈኑብኝ።
15ምሬትን አጠገበኝ፤ በሐሞትም አሰከረኝ።
16ዋው። ጥርሴን በጭንጫ ሰበረ፤ አመድም አቃመኝ።
17ነፍሴን ከሰላም አራቀ፤ በጎ ነገርን ረሳሁ።
18እኔም፦ ኀይሌን፥ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ያለውን ተስፋዬን አጣሁ።
19ዛይ። ስደቴንና ችግሬን፥ እሬትንና ሐሞትን አስብ።
20ነፍሴ እያሰበችው በውስጤ ፈዘዘች።
21ይህችን በልቤ አኖራለሁ፤ ስለዚህ እታገሣለሁ።
22ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና።
23ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው።
24ነፍሴ፥ “እግዚአብሔር እድል ፋንታዬ ነው፤ ስለዚህ ጠበቅሁት” አለች።
25ጤት። እግዚአብሔር ለሚታገሡት ቸር ነው፤
26ለምትሻውና ለምትታገሥ፥ ዝም ብላም የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ለምታደርግ ነፍስ መልካም ነው።
27ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው።
28ዮድ። እርሱ አሸክሞታልና ዝም ብሎ ለብቻው ይቀመጥ።
29ተስፋ ይሆነው እንደ ሆነ አፉን በአፈር ውስጥ ያኑር።#ምዕ. 3 ቁ. 29 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
30ጕንጩን ለሚመታው ይሰጣል፤ ስድብንም ይጠግባል።
31ካፍ። ጌታ ለዘለዓለም አይጥልምና፤
32ያሳዘነውን ሰው እንደ ይቅርታው ብዛት ይምረዋልና፤
33ከልቡ አልተቈጣምና፥ የሰውንም ልጆች አላሳዘነምና፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የሰውን ልጆች ዝቅ አደረገ” ይላል።
34ላሜድ። በምድር የተጋዙትን ሁሉ ከእግሩ በታች ይረግጣቸው ዘንድ፥
35የሰውን ፍርድ በልዑል ፊት ይመልስ ዘንድ፥
36በሚፈርድበት ጊዜ የሰውን ፍርድ ያጣምም ዘንድ እግዚአብሔር አላዘዘም።
37ሜም። “እግዚአብሔር ያላዘዘው ይመጣል፥
38ከልዑል አፍም ያልወጣ መልካም ወይም ክፉ ይሆናል” የሚል ማን ነው?
39ሰው ሕያው ሲሆን ስለ ኀጢአቱ ለምን ያጕረመርማል?
40ኖን። መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትን፤ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ።
41ልባችንን ከእጃችን ጋር ወደ እግዚአብሔር ወደ ሰማይ እናንሣ።
42በድለናል፤ ዐምፀናልም፤ አንተም አልራራህልንም።
43ሳምኬት። በቍጣህ ከደንኸን፤ አሳደድኸንም፤ ገደልኸን፤ አልራራህልንም።
44ጸሎታችን እንዳያርግ ራስህን በደመና ከደንህ።
45እንድናዝንና እንዳናይም በአሕዛብ መካከል አስቀመጥኸን።
46ዔ። ጠላቶቻችን ሁሉ በእኛ ላይ አፋቸውን ከፈቱ።
47ፍርሀትና ቍጣ፥ ጥፋትና ቅጥቃጤ ያዘን።
48ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ከዐይኔ የውኃ ጐርፍ ፈሰሰ።
49ፌ። ዐይኔ ተደፈነች፤ እንግዲህ ከማንጋጠጥ ዝም አልልም።
50እግዚአብሔር ከሰማይ ሆኖ እስኪመለከት ድረስ።
51ስለ ከተማዬ ቈነጃጅት ሁሉ ዐይኔ ነፍሴን አሳዘነች።
52ጻዴ። በከንቱ ነገር ጠላቶች ሁሉ እንደ ወፍ ማደንን አደኑኝ።
53ጠላቶች ሕይወቴን በጕድጓድ አጠፉ፤ በላዬም ድንጋይ ገጠሙ።
54በራሴ ላይ ውኃ ተከነበለ፤ እኔም፥ “ጠፋሁ” ብዬ ነበር።
55ቆፍ። አቤቱ፥ በጥልቅ ጕድጓድ ውስጥ ሆኜ ስምህን ጠራሁ።
56አንተ ድምፄን ሰማህ፤ ጆሮህንም ከልመናዬ አትመልስ።
57በጠራሁህ ቀን ወደ እኔ ቅረብ፤ “አትፍራም” በለኝ።
58ሬስ። አቤቱ፥ የነፍሴን ፍርድ ፈረድህ፤ ሕይወቴንም ተቤዥህ።
59አቤቱ፥ ጭንቀቴን#ግእዝ “ዘይመክሩ ላዕሌየ” ይላል። አይተሃል፤ ፍርዴን ፍረድልኝ።
60በቀላቸውን ሁሉና በእኔ ላይ ያለውን ዐሳባቸውን ሁሉ አየህ።
61ሣን። አቤቱ፥ ስድባቸውንና በእኔ ላይ ያለውን ዐሳባቸውን ሁሉ ሰማህ።
62የተነሡብኝን ሰዎች ከንፈሮች ቀኑንም ሁሉ ያሰቡብኝን ዐሳባቸውን ሰማህ።
63መቀመጣቸውንና መነሣታቸውን ተመልከት፤ እኔ መዝፈኛቸው ነኝ።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “መዝፈኛቸው ነኝ” በማለት ፈንታ “ዐይናቸውን ተመልከት” ይላል።
64ታው። አቤቱ፥ እንደ እጃቸው ሥራ ፍዳቸውን ክፈላቸው።
65የልብ ሕማምንና ርግማንህን ስጣቸው።
66አቤቱ፥ እንደ ልባቸው ክፋት በቍጣህ ታሳድዳቸዋለህ፤ ከሰማይም በታች ታጠፋቸዋለህ።
Currently Selected:
ሰቆቃወ ኤርምያስ ነቢይ 3: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ