መጽሐፈ ኢዮብ 34
34
ኤልዩስ የእግዚአብሔርን እውነተኛ ፈራጅ መሆን እንደ ተናገረ
1ኤልዩስ ደግሞ መለሰ፥ እንዲህም አለ፦
2“እናንተ ጥበበኞች፥ ቃሌን ስሙ፤
እናንተም ዐዋቂዎች፥ መልካም ነገርን አድምጡ።
3ጆሮ ቃልን ትለያለችና፥
ጕሮሮም የመብልን ጣዕም ይለያል።
4ፍርድን ለራሳችን እንምረጥ፤
በመካከላችንም ምን እንደሚሻል እንወቅ።
5ኢዮብ እንዲህ ብሎአልና፦ እኔ ጻድቅ ነኝ፥
እግዚአብሔር ግን ፍርዴን አስወገደ፤
6ፍርዴን ሐሰተኛ አደረገብኝ፤ #በዕብራይስጥ ይለያል።
በደልም ሳይኖርብኝ በግፍዕ መከራን እቀበላለሁ።
7መሣለቅን እንደ ውኃ የሚጠጣት፥
እንደ ኢዮብ ያለ ሰው ማን ነው?
8ፈጽሞ ያልበደለ፥
ግፍን ከሚሠሩም ጋር ያልተባበረ፥
ከኃጥኣንም ጋር ያልሄደ፥ ማን ነው?
9ሰው ከእግዚአብሔር ጕብኝት ሲኖረው
እግዚአብሔር አይጐበኘውም አትበል።
10“ሰለዚህ እናንተ አእምሮ ያላቸሁ ሰዎች ስሙኝ፤
በእግዚአብሔርም ዘንድ ትበድሉ ዘንድ አትውደዱ።
ሁሉን በሚችል አምላክ ፊትም ጻድቁን አታውኩት።
11ለሰው ሁሉ እንደ ሥራው ይመልስለታል፥
ሰውንም እንደ መንገዱ ያገኘዋል።
12በእውነት እግዚአብሔርን ግፍ እንደሚሠራ ታደርገዋለህን?
ወይስ ምድርን የፈጠረ ሁሉን የሚችል አምላክ ፍርድን ያጣምማልን?
13ከሰማይ በታች ያለውን ዓለም፥
በውስጡም ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠረ ማን ነው?
14በእርሱ ያለ መንፈሱን፥
ሊያጸናና ሊይዝ ቢወድድ፥
15ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአንድነት ይሞታል፥
ሟችም ሁሉ ወደ ተፈጠረበት መሬት ይመለሳል።
16ያለዚያ ግን ተመከር፥ ይህንም ስማ፤
የንግግሬንም ቃል አድምጥ።
17ግፍን የሚጠላ፥ ክፉዎችንም የሚያጠፋ፥
ለዘለዓለም ጻድቅ ነው።
18ንጉሡን፦ በደለኛ ነህ የሚለው፥
መኳንንቱንም፦ ክፉዎች ናችሁ የሚላቸው ኀጢአተኛ ነው
19እርሱ ግን የክቡርን ሰው ፊት አያፍርም።#በዕብራይስጥ ይለያል።
ለታላቁም ክብር መስጠትን አያውቅም፥ ከፊታቸውም አይሸሽም።#በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
20የሚጮኸውንና ሰውን የማይሰማውን ከንቱ ነገር ያገኘዋል፥
በድሆች ላይ ክፉ አድርጎአልና።#በዕብራይስጥ ይለያል።
21እርሱ የሰዎችን ሥራ ይመረምራል፥
ከሚሠሩትም ሁሉ ከእርሱ የሚሰወር ምንም የለም።
22ኀጢአትን የሚሠሩ የሚሰወሩበት ቦታ የለም።
23ሁሉን ከሚያይ ከእግዚአብሔር አያመልጡምና።#ከግሪክ ሰብ. ሊ. እና ከዕብ. ይለያል።
24እግዚአብሔር ወደ ታች ወደ ሰዎች ይመለከታል፥
ሊመረመሩ የማይችሉ ነገሮችን ሁሉ፥
ቍጥር የሌላቸውን የተከበሩትንና ድንቆችንም ያስተውላል።
25ሥራቸውን ያውቃል፥
በእነርሱም ላይ ሌሊትን ያመጣል፥ መከራንም ያጸናባቸዋል።
26ኃጥኣንን ያጠፋቸዋል፥
ጻድቃን ግን በፊቱ ናቸው።
27ከእግዚአብሔር ሕግ ፈቀቅ ያሉ፥
ፍርዱን አያውቁም።
28እርሱም የድሆችን ጩኸት በእነርሱ ላይ ይመልሳል፥
የችግረኞችንም ልቅሶ ይሰማል።
29“እርሱ ዕረፍትን ይሰጣል፤
የሚፈርድስ ማን ነው?
በሕዝብ ወይም በሰው ዘንድ ፊቱን ቢሰውር የሚያየው ማን ነው?
30ስለ ሕዝቡም ክፋት፥
ግብዝ ሰውን ያነግሣል።
31“ኀያሉ እግዚአብሔርን፦ እንዲህ የሚል አለ፥
እኔ በረከትን ተቀበልሁ፥
መያዣውንም አልወስድም።
32እኔ ራሴ አያለሁ፥
ኀጢአትንም ሠርቼ እንደ ሆነ፥ ሐሰትንም ተናግሬ እንደ ሆነ፥#በዕብራይስጥ ይለያል።
ደግሜ እንዳልሠራ አንተ አሳየኝ።
33በውኑ አንተ ከእኔ ትርቅ ዘንድ፥
እኔ ከአንተ የተቀበልሁት አለን?
አንተ ትመርጣለህ እንጂ እኔ አይደለሁምና፤
ስለዚህ የምታውቀው ካለ ተናገር።
34የልብ ጥበበኞች እንዲህ ይላሉና፦
ጠቢብ ሰው ነገሬን ይሰማኛል።
35ኢዮብ እንደ ጠቢብ በዕውቀት አይናገርም፥
ቃሉም እንደ ምሁር አይደለም።
36ነገር ግን ኢዮብ ሆይ፥ ተማር።
እንደ ሰነፎችም አትመልስ፥
37በኀጢአቶችህ ላይ እንዳትጨምር፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. በብዙ።
በእግዚአብሔርም ፊት ብዙ መናገር በደል ይሆንብሃል።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 34: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ