መጽሐፈ ኢዮብ 24
24
1“እግዚአብሔር ዘመኖችን ለምን ረሳቸው?#ዕብራይስጥ ተጨማሪ አለው።
2ኃጥኣን የድንበሩን ምልክት አለፉ፤
እረኛውንም ከመንጋዎቹ ጋር ይነጥቃሉ።
3የድሃአደጎቹን አህያ ይነዳሉ
የመበለቲቱንም በሬ ስለ መያዣ ይወስዳሉ።
4ደካሞችን ከእውነት መንገድ ያወጣሉ፤
የምድርም የዋሃን ሁሉ በአንድነት ይሸሸጋሉ።
5እነሆ፥ በምድረ በዳ እንዳሉ እንደ ሜዳ አህዮች ሆኑ።
ስለ እኔም ሥራቸውን ትተው ይወጣሉ፤
መብል፦ ከልጅነታቸው ጀምሮ ይጥማቸዋል።
6“የራሳቸው ያልሆነውን እርሻ ያለ ሰዓቱ ያጭዳሉ።
ኃጥኣን ድሆችን በወይናቸው ቦታ ያለ ዋጋና ያለ ቀለብ ያሠሩአቸዋል።
7ብዙዎችን የተራቈቱትንም ያለ ልብስ ያሳድሩአቸዋል።
መጐናጸፊያቸውንም ይገፍፏቸዋል።
8በካፊያና ከተራሮች በሚወርድ ጠል ይረጥባሉ፤
መጠጊያም የላቸውምና ቋጥኙን ተተገኑ።
9ድሃአደጉን ልጅ ከጡቱ ይነጥላሉ፤
ችግረኛውንም ያሠቃያሉ።
10ችግረኞችን በደሉአቸው፥ ጣሉአቸውም፤
ከተራቡትም የሚጐርሱትን ነጠቋቸው።
11በጠባብ ቦታ በዐመፅ ይሸምቃሉ፥#በዕብራይስጥ ታላቅ ልዩነት አለው።
የጽድቅንም መንገድ አያውቁም።
12ድሆችን ከከተማውና ከገዛ ቤቶቻቸው አባረሩአቸው
የሕፃናትንም ነፍስ እጅግ አስጮሁ፤
13“እግዚአብሔር ግን እነዚህን ለምን አልገሠጻቸውም?
በምድር ላይ ሳሉ አላስተዋሉም፥
የቅንነት መንገድንም አላዩም።
በአደባባይዋም አልሄዱም።
14ሥራቸውንም ዐውቆ ለጨለማ ዳረጋቸው።
በሌሊትም እንደ ሌባ ናቸው።
15የአመንዝራም ዐይን ድግዝግዝታን ይጠብቃል፦
የማንም ዐይን አያየኝም ይላል፥
ፊቱንም ይሸፍናል።
16በጨለማ ቤቶችን ይነድላል፤
በቀን ይሸሸጋሉ፤ ብርሃንንም አያዩም።
17የጥዋት ብርሃን ለእነርሱ ሁሉ እንደ ሞት ጥላ ነው፤
የሚሆነውን ድንጋጤ ያውቃሉና።
ሞትንም ይጠራጠራሉና።
18እርሱ በውኃ ፊት ላይ በርሮ ያልፋል፤
እድል ፋንታውም በምድር ላይ የተረገመች ናት፤
19ተክላቸው በምድር ላይ ሲደርቅ ያያሉ።
ያላቸውም ድሀኣደጉን በዘበዙት።
20ከዚህም በኋላ ኀጢአቱን ያስባል።
እንደ ጤዛ ትነት ይጠፋል።
እንደ ሥራውም ይከፈለዋል።
ዐመፀኛም ሁሉ እንደ በሰበሰ ዛፍ ይሰበራል።
21ለማትወልደው ለመካኒቱ በጎነትን አላደረገላትም፤
ለምትወልደውም#ግሪኩ “ለደካማይቱ” ይላል። አልራራም።
22ነገር ግን ረዳት የሌላቸውን በቍጣው አጠፋቸው።
እርሱም በተነሣ ጊዜ ሰው በሕይወቱ አይታመንም።
23በታመመም ጊዜ መዳንን ተስፋ አያደርግም።
ነገር ግን እርሱ በሕማሙ ይሞታል።
24ከፍ ከፍ ባለ ጊዜም ብዙዎችን አስጨነቃቸው።
እንደ አመድማዶ በሙቀት ይጠወልጋል።
ከቃርሚያው እንደሚወድቅ እሸትም ይቈረጣል።
25እንዲህስ ባይሆን ሐሰተኛ ነህ የሚለኝ፥
ነገሬንስ እንደ ኢምንት የሚያደርገው ማን ነው?”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 24: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ