መጽሐፈ ኢዮብ 21
21
የኢዮብ መልስ
1ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦
2“እኛ አጽናናነው እንዳትሉኝ፥
ስሙ፤ ቃሌን ስሙ።
3እናገር ዘንድ ዝም በሉ፤
ከተናገርሁ በኋላ ትስቁብኛላችሁና፤
4ሰው የሚዘልፈኝ አይደለም፤
ስለ ምንስ አልቈጣም?
5ወደ እኔ ተመልከቱ፥ ተደነቁም፤
እጃችሁንም በጕንጫችሁ ላይ አኑሩ።
6እኔ ባሰብሁ ቍጥር እጨነቃለሁ፤
ጻዕርም ሥጋዬን ይይዛል።
7ስለ ምን ኀጢኣተኞች በሕይወት ይኖራሉ?
በባለጠግነትስ ስለ ምን ያረጃሉ?
8ዘራቸው በፊታቸው ከእነርሱ ጋር ጸንቶ ይኖራል፤
ልጆቻቸውም በዐይናቸው ፊት ናቸው።
9ቤታቸው በብልፅግና የተሞላ ነው፤ የሚያስፈራቸውም የለም።
ከእግዚአብሔርም ዘንድ መቅሠፍት አይመጣባቸውም።
10በሬዎቻቸው አይመክኑም፤
ላሞቻቸውም አይጨነግፉም፤ በደኅናም ይወልዳሉ።
11እነርሱም እንደ በጎች ለዘለዓለም ይጠበቃሉ፤
ልጆቻቸውም በፊታቸው ይዘፍናሉ።
12በገናና መሰንቆ ይዘው ይዘምራሉ፤
በመዝሙራቸውም ደስ ይላቸዋል።
13ዕድሜያቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ፤
በሲኦል ማረፊያም ይጋደማሉ።
14እግዚአብሔርንም፦ እንዲህ ይሉታል፦ ከእኛ ዘንድ ራቅ፤
መንገድህንም እናውቅ ዘንድ አንወድድም።
15እንገዛለትስ ዘንድ እርሱ ምን ይችላል?
ወይስ ወደ እርሱ ብንቀርብ ምን ይጠቅመናል?
16“እነሆ፥ በጎነታቸው በእጃቸው ውስጥ አለች፤
የኃጥኣንን ሥራ አይመለከትም።
17የኃጥኣን መብራት ትጠፋለች፤
መቅሠፍትም ትመጣባቸዋለች።
የበቀል ቍጣም ይይዛቸዋል፤
18በነፋስም ፊት እንደ ገለባ፥
አውሎ ነፋስም እንደሚወስደው ትቢያ ይሆናሉ።
19ልጆቹ ሀብቱን አያገኙም።
እግዚአብሔር ብድራቱን ይከፍለዋል።
እርሱም ያንጊዜ ያውቃል።
20ዐይኖቹ ልጆቹ ሲወጉ ያያሉ፤
እግዚአብሔርም አያድናቸውም።
21የወደደውን በቤቱ ውስጥ ያደርጋል።
ወራቶቹም ከቍጥር ድንገት ይጐድላሉ።
22ጥንቱን ዕውቀትንና ምክርን የሚያስተምር እግዚአብሔር አይደለምን?
በነፍሰ ገዳዩስ የሚፈርድ እርሱ አይደለምን?
23አንድ ሰው በሰላም ተዘልሎ ሲቀመጥ፥
በሁሉም ፈጽሞ ደስ ብሎት ሳለ ይሞታል።
24በውስጡ ስብ ሞልቶአል፥
የአጥንቶቹም ቅልጥም ፈስሶአል።
25ሌላውም ሰው መልካምን ነገር ከቶ ሳይበላ
በተመረረች ነፍሱ ይሞታል።
26ሁሉም በአፈር ውስጥ በአንድ ላይ ይተኛሉ፤
ትሎችም ይሸፍኗቸዋል።
27እነሆ፥ ደፍራችሁ፥
በእኔ ላይ በጠላትነት እንደ ተነሣችሁ ዐውቄአለሁ።
28እናንተ፦ የአለቃው ቤት የት ነው?
ኀጢአተኛውም ያደረበት ድንኳን የት ነው? ብላችኋልና።
29መንገድ ዐላፊዎችን ጠይቋቸው፤
ምልክታቸውንም አታገኙም።
30ኀጢአተኛውን ክፉ ቀን ትጠብቀዋለች፤
በቍጣ ቀንም ይወስዱታል።
31መንገዱን በፊቱ የሚናገር ማን ነው?
እርሱ የሠራውንስ የሚመልስበት ማን ነው?
32እርሱን ግን ወደ መቃብር ይወስዱታል፤
በመቃብሩም ውስጥ ይጠበቃል።
33የሸለቆው ጓል ይጣፍጥለታል፤
በኋላውም ሰው ሁሉ ይወጣል፤
በፊቱም ቍጥር የሌለው ሰው አለ።
34ለምን በከንቱ ታጽናኑኛላችሁ?
በእናንተ ዘንድ ግን ዕረፍት የለኝም።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 21: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ