መጽሐፈ ኢዮብ 11
11
የሶፋር ንግግር
1አሜናዊው#ዕብ. “ነዕማታዊው” ይላል። ሶፋር መለሰ፥ እንዲህም አለ፦
2“ብዙ እንደምትናገር እንዲሁ መስማት አለብህ።
ወይስ በንግግርህ ብዛት ጻድቅ የምትሆን ይመስልሃልን?
ከሴቶች የሚወለድ ዘመኑ ጥቂት የሆነ ቡሩክ ነው። #በዕብራይስጥ የለም።
3ንግግር አታብዛ፤
የሚከራከርህ የለምና።
4አንተ፦ በሥራዬ ንጹሕ ነኝ
በፊቱም ጻድቅ ነኝ አትበል።
5ምነው እግዚአብሔር ቢናገርህ!
በአንተም ላይ ከንፈሩን ቢከፍት!
6የጥበቡን ኀይል ቢገልጥልህ!
ባንተ ላይ ያለው እጥፍ ነውና።
ያንጊዜም ከእግዚአብሔር ዘንድ በበደልህ ያገኘህ ትክክል እንደ ሆነ ታውቃለህ።
7“የእግዚአብሔርን ፍለጋ ልትመረምር ትችላለህን?
ወይስ ሁሉን የሚችል አምላክ ወደ ፈጠረው ፍጥረት ፍጻሜ ትደርሳለህን?
8ሰማይ ከፍ ያለ ነው፤ ምን ልታደርግ ትችላለህ?
ከሲኦልም ይልቅ የጠለቁ ነገሮች አሉ፤ ምን ታውቃለህ?
9ርዝመቱ ከምድር ይልቅ ይረዝማል፥
ከባሕርም ይልቅ ይሰፋል።
10እርሱ ሁሉን ቢገለብጥ፥
ምን አደረግህ? የሚለው ማን ነው?
11እርሱ የኃጥኣን ሰዎች ሥራን ያውቃል፤
በደልንም ቢያይ ዝም ብሎ አይመለከትም፤
ይህንም አስተዋይ ሰው ያስተውላል።
12ነገር ግን በከንቱ ነገርን የሚፈልግ ሰው፥
ከሴትም የሚወለድ ሟች የሜዳ አህያን ይመስላል።
13አንተ ልብህን ንጹሕ ብታደርግ፥
እጆችህንም ወደ እርሱ ብትዘረጋ፥
14በእጆችህ በደል ቢኖር ካንተ አርቀው፤
በልብህም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በድንኳንህ” ይላል። ኀጢአት አይኑር፤
15በዚያን ጊዜ ፊትህ በንጹሕ ውኃ እንደ ታጠበ ያበራል፥
መተዳደፍህንም ታስወግዳለህ፥ አትፈራምም።
16መከራህንም እንዳለፈ ማዕበል ትረሳለህ፥
ከእንግዲህም ወዲያ አትደነግጥም።
17ጸሎትህ እንደ አጥቢያ ኮከብ ይሆናል።
ሕይወትህም እንደ ቀትር ብርሃን ያበራል።
18ተስፋህንም ታገኝ ዘንድ ተዘልለህ ትቀመጣለህ፤
ያለ ኀዘንና ጭንቀትም በደኅንነት ትኖራለህ።
19ታርፋለህ፥ የሚዋጋህም የለም፤
ብዙ ሰዎችም ይመጣሉ፤ ልመናም ያቀርቡልሃል።
20የኃጥኣን መድኀኒታቸው ታልቃለች።
ተስፋቸውንም ያጣሉ፥
የዝንጉዎች ዐይኖችም ይጠፋሉ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 11: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ